Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኮንዶም እየቀረበ ያለው ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ኮንዶም እየቀረበ ያለው ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በአገር አቀፍ ደረጃ ኮንዶም እየቀረበ ያለው ለኤችአይቪ/ኤድስ ይበልጥ ተጋላጭ  ተብለው ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መሆኑን፣ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኮንዶም አቅርቦትና ሥርጭት ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ እንደ በፊቱ አይደለም፡፡

በዓለም ገበያ የፕላስቲክ ግብዓቶች መጥፋት ለሥርጭቱ መቀነስ እንደ ምክንያት ያነሱት አቶ ፈቃዱ፣ በተለያዩ መንገዶች የሚገዛው ኮንዶም ጥራት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮንዶም አቅርቦትን በተሻለ ሁኔታ ለማዳረስ የሥርጭት ስትራቴጂ በሦስት ክፍሎች እየተሠራ እንደሚገኝ ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡

የኮንዶም አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ዲኬቲ ኢትዮጵያ ከሚያቀርበው በተጨማሪ፣ በመንግሥት ግዥ ተፈጽሞ የሚገባና ድጎማ የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡

በሦስቱም አማራጮች የኮንዶም ሥርጭትን ለማስፋት ጥረት ቢደረግም፣ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ በአሁኑ ጊዜ እየቀረበ ያለው በኤችአይቪ/ኤድስ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እነዚህም ሴተኛ አዳሪዎች፣ ባል ወይም ሚስት የሞቱባቸውና የከባድ ጭነት  አሽከርካሪዎች ኮንዶም ከሚቀርብላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ይገኙበታል፡፡

 ከእነዚህ ኅብረተሰብ ክፍሎች ውጪ እንደ ከዚህ ቀደሙ በተለያዩ ቦታዎች፣ ማለትም በትምህርት ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች ኮንዶም ማስቀመጥ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒታቸውን ያቋረጡ ወገኖች እንዳሉ፣ ከተደረገው የሰላም ስምምነት በኋላ ግን 95 በመቶ የሚሆኑትን መድኃኒታቸውን እንዲጀምሩ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎች ከ65,000 ዜጎች በጦርነቱ ሳቢያ መድኃኒታቸውን ያቋረጡ ቢሆኑም፣ አካባቢው ሰላም ከሆነ በኋላ 95 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒታቸውን እንዲጀምሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡  

በትግራይ ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ 141 የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት የሚሰጡ ተቋማት ሥራቸውን አቋርጠው እንደነበር፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ 85 በመቶ ያህሉ አገልግሎት የጀመሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ ከጦርነት በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት መውሰድ የነበረባቸው 4,000 ሰዎች አሁንም እንዳልጀመሩ ተናግረዋል፡፡

 በአሁኑ ጊዜ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማት በትግራይ ክልል መኖራቸውን ጠቁመው፣ ከክልሉ ጤና ቢሮና ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን መድኃኒት ያቋረጡ ሰዎችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ሲወስዱ የነበሩ ዜጎች ማቋረጣቸውን የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማፈላለግ መድኃኒት እንዲጀምሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡  

በኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ የግብዓትና የሀብት እጥረት ምክንያት በትኩረት እየተሠራ ያለው፣ የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ በሆኑበት አካባቢዎች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በይበልጥ በሽታው ከፍተኛና ዝቅተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎች የሚሠራበት፣ ስትራቴጂና የሀብት አጠቃቀም እንደ በሽታው ሥርጭት እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በዓመት የሚገዛው የኤችአይቪ መመርመሪያ ኪት ዘጠኝ ሚሊዮን መሆኑን፣ አራት ሚሊዮን ያህሉ ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚውል ነው ተብሏል፡፡

ከዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉንም ማኅበረሰቦች ያቀፈ የግንዛቤ ማስጨበጫና  የሕክምናና የምርመራ አገልግሎት አናሳ መሆኑን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ትኩረት የሚሹ ዜጎችና አካባቢዎች መሠረት ያደረገ አሠራር እንደሚከተሉ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...