Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳፋሪኮም ኤምፔሳን ለማስጀመር ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝ ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከወር በፊት በይፋ ፈቃድ ያገኘበትን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት (M-PESA) ወደ ደንበኞቹ ከመድረሱ በፊት፣ ተፈላጊውን ሙከራ በራሱ ተቋም ውስጥ እያደረገ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡

ሪፖርተር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኤምፔሳ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ እየፈተሸ እንደሚገኝ ከአንድ የተቋሙ የሥራ ኃላፊ ያረጋገጠ ሲሆን፣ በራሱ ተቋም ውስጥ የተጀመረው የሙከራ አገልግሎት በቅርቡ ወደ ደንበኞቹ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኤምፔሳ የሥራ ክፍል ሠራተኞች፣ ኤምፔሳን በመጠቀም የተለያዩ የቅድመ ምርት አገልግሎቶችን እየተገለገሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ስምንት ወራት የተሻገረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በግንቦት ወር መጀመሪያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት (M-PESA) ፈቃድ ማግኘቱን ይታወሳል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተቀጥላ ሆኖ የተቋቋመው ኤምፔሳ ሞባይል ፋይናንሺያል ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሲያገኝ፣ ሳፋሪኮም ለመንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር የፈቃድ ክፍያ እንደከፈለ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

የሳፋሪኮም ኬንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒተር ንዴግዋ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የተቋማቸውን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት ሲያቀርቡ፣ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሰባት ወራትን ያስቆጠረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ‹‹ሞባይል መኒ›› ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን አስታውቀው፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቁመው ነበር።

የቴሌኮም ኩባንያው የኢትዮጵያ መንግሥት ለቴሌኮም ኩባንያዎች ያወጣውን ጨረታ በግንቦት 2013 ዓ.ም. ሲያሸንፍ ለፈቃድ 850 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ለመስጠት የከፈለው 150 ሚሊዮን ዶላር ለአገልግሎቱ የተከፈለ ተጨማሪ የፈቃድ ክፍያ ነው፡፡

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተቀጥላ ሆኖ የተቋቋመው ኤምፔሳ ሞባይል ፋይናንሺያል ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ ሲጀምር፣ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ሆኖ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሚያቀርብ ሁለተኛው ተቋም ያደርገዋል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በጀመረ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳፈራ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ደንበኞቹን ቁጥር እ.ኤ.አ በ2024 ወደ አሥር ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ እንዳለው ከዚህ ቀደም መግለጹ አይዘነጋም። የቴሌኮም ኩባንያው በተመሳሳይ ጊዜ በኢትዮጵያ 562.4 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ከዚህ ቀደም ከባንክ ውጪ የሆኑ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎችን፣ ፊንቴክና የክፍያ ኤጀንቶችን የመሳሰሉ ተቋማት በክፍያ አገልግሎት ዘርፉ እንዲሳተፉ መደረጉን አስታውሰው፣ በአገሪቱ የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢነት ፈቃድ አግኝቶ ሥራ የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችለውን ፈቃድ በቅርቡ እንደሚያገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች