Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ 23 በመቶ ሕፃናት የሚሰቃዩበት ጉልበት ብዝበዛ

በኢትዮጵያ 23 በመቶ ሕፃናት የሚሰቃዩበት ጉልበት ብዝበዛ

ቀን:

ሕፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው በተለያዩ ሥራዎች መሰማራታቸው ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል፡፡ ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢሆንም፣ በማደግ ላይ ባሉና ባላደጉ አገሮች ደግሞ በስፋት ይታያል፡፡ በጦርነት፣ በግብርና፣ በሴተኛ አዳሪነት፣ በሽመናና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሕፃናት ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ገና ሰውነታቸው ሳይጠነክር በለጋ ዕድሜያቸው ለከባድ ሥራ መጋበዛቸው አስደንጋጭ ቢሆንም፣ በማናለብኝነት የተሰማሩ ደላሎች የሕፃናት ልጆችን ንግድ እያጣጧፉት ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም ለዚህ ዓላማ ብቻ የተሰማሩ ሰዎች እንዳሉ ከተማዋ ጎዳና ላይ የሚታዩ ሥራዎች ምስክር ናቸው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት እየሠራ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ውኃ ቅዳ ኃው መልስ ሆኗል፡፡

የሥራና ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመግታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ሰላም ደኅንነትና ጤና ዳይሬክተር አቶ ካሳ ሥዩም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕፃናት ልጆች ላይ የሚደርሰው የጉልበት ብዝበዛ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ 168 ሚሊዮን ሕፃናት ልጆች ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆናችውን፣ ከዚህ ውስጥም 85 በመቶ የሚሆኑት ልጆች በጣም ጠንቀኛ የሚባሉ የሥራ ዘርፎች ውስጥ መሰማራታቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በዋናነት አፍሪካውያን የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን የተናገሩትት ዳይሬክተሩ፣ አብዛኛው ሕፃናት ልጆች ወደ ችግሩ ውስጥ እንዲገቡ ከሚያደርጋቸው ምክንያት አንዱ ድህነት መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ችግሩ እንደሚታይ ገልጸው፣ በደቡብ እስያ አገሮች፣ በህንድ፣ በባንግላዴሽ፣ በፓኪስታንና በሌሎች አገሮች ውስጥ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሚባሉ ሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ለሴተኛ አዳሪነት፣ ለዕፅ አዘዋዋሪነት፣ ለጦርነት፣ ለቤት ሠራተኝነትና ለሌሎች ሥራዎች ሕፃናትን ተጠቅመው የሚሠሩ ደላሎች መኖራቸውን፣ ችግሩም በኢትዮጵያ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያም 23 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት በከባድ ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙና እነዚህም ሕፃናት አካላዊ ደኅንነታቸው በከፋ ሁኔታ በመቁሰሉ ላልታወቀ ጤና ችግር መጋለጣቸውን አቶ ካሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ አስከፊ የሕፃናት ሥራና የጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 የወጣት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታን በተመለከተ ሰፊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመፈተሽና ፍትሕ ለመስጠት መመርያ ወጥቶ እየተሠራ ቢሆንም፣ አሁንም በዘርፉ ሰፊ ክፍተት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

ሕገወጥ ደላሎች ከገጠራማ አካባቢ ሕፃናት ልጆችን ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚያገኙባቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ እነዚህን ሕገወጥ ደላሎች በመቆጣጠር ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም ከገጠራማ አካባቢ የሚፈልሱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ አንዱ የዚህ ችግር ማሳያ እንደሆነ፣ ይህንንም መቆጣጠር ለመንግሥት ብቻ የሚተው አለመሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን አውጥቶ እየሠራ መሆኑን፣ ተቋሙም ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ወጣቶችን ‹‹በምን ዓይነት ሥራዎች ተሰማርተዋል?›› የሚለውን የሚፈትሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ15 እስከ 17 የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚቀጠሩበት ሥራ ጉልበት የማይበዘብዝ፣ እንዲሁም ጎጂ ያልሆነ መሆን እንዳለበት የተቀመጠው አዋጅ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የወጣውን መመርያ ከማስፈጸም አኳያ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ቦታዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ግን ትክክለኛ የሆነ የልደት ካርድ ስለሌላቸው ዕድሜያቸውን ለማወቅ መቸገራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻም፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ የሥራ ቅጥር የሚፈጽሙ ድርጅቶች የራሳቸውን አሠራር በመዘርጋት የጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በተለይም በከተማዋ የሕፃናት እንክብካቤ ተቋማት ውስን በመሆናቸው፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ችግር እየጨመረ መምጣቱንና ይህንንም ለመረዳት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆኑ ባለሀብቶች ጭምር በዘርፉ በመሰማራት መሥራት እንደሚኖርባቸው አቶ ካሳ አክለዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መመርያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የሕፃናት ልጆችን መብት ማስከበር እንደሚገባ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሕፃናት ከመደበኛ የሥራ ሰዓት በተጨማሪ እየሠሩ ጉልበታቸው እየተበዘበዘ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

በአዋጁ ሕፃናት ልጆች ከሰባት ሰዓት በላይ መሥራት፣ ትርፍ ሥራ መሥራትና በአደገኛና በጠንቀኛ ሥራዎች መቀጠር እንደሌለባቸው የሚያሳይ ቢሆንም፣ በርካታ ሕፃናት ግን ለከፋ ችግር እየተጋጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአዋጅ ላይ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ ተቀጥረው መሥራት እንደሌለባቸው የሚያሳይ መሆኑን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ሕፃናት ገና አካላቸው ሳይዳብር ወደ ሥራ ዓለሙ ገብተው በሰውነታቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥማቸውና ለሥነ ልቦና ጉዳት እንደሚዳረጉ አስታውሰዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ 168 ሚሊዮን ሕፃናት ልጆች በጉልበት ብዝበዛ ሥራ መሰማራታቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 11 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዓለም ውስጥ ከፍተኛ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚበዛባቸው አገሮች እስያና ህንድ መሆናቸውን ገልጸው፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ246 ሚሊዮን ከነበረው አኃዝ ወደ 168 ሚሊዮን መድረሱንና ይህም በከፊልም ቢሆን ችግሩ መቀነሱን እንደሚያሳይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካም 72 ሚሊዮን ሕፃናት ልጆች በጉልበት ብዝበዛ ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከእነዚህም ውስጥ 31 ሚሊዮኑ በአደገኛ የሥራ ሁኔታዎች የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕፃናት በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ጉልበታቸው እየተበዘበዘ እንደሚገኝ፣ ይህ በመቶኛ ሲታይ 85 በመቶ ያህሉ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

11 በመቶ ልጆች ደግሞ በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች የሚሠሩ ሲሆን፣ አራት በመቶ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡  

ማዕከላለዊ ስታትስቲክስ የ2015 ዓ.ም. ያደረገውን ጥናት ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ 42.7 በመቶ ሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ዕድሜያቸው ስምንት ዓመት ከሞላቸው ሕፃናት ውስጥ 90 በመቶው የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡

48.8 በመቶ የሚሆነው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በከተሞች ውስጥ ሲሆን፣ 18.7 በመቶ ደግሞ በገጠር አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ በየትኛው ዘርፍ ላይ ነው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚደርሰው? የሚለው የተለየ መሆኑንና አብዛኛውን ጊዜም በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ የቤት ሠራተኛ፣ በግብርና፣ በሽመና፣ በታክሲ ረዳትነት፣ በሆቴሎች፣ በየጠጅ ቤቱና በተለያዩ አካባቢዎች ችግሩ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተለያዩ ቦታዎች ፈልሰው የመጡ ሕፃናት ልጆች በተለያየ የሥራ መስክ መሰማራታቸውን፣ በተለይም ከደቡብ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች የሚፈልሱ ሕፃናት ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማዋ 5.6 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ልጆች ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥም 90 በመቶ በአደገኛ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃም የሕፃናት ለጉልበት ብዝበዛ ለመቀነስ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንደሚኖርባቸው፣ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ችግሩን በተወሰነ መልኩም መቅረፍ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡   

በአገሪቱ በሽመና፣ በቆዳ ሥራ፣ በቤት ውስጥ ሥራ፣ በሴት አዳሪነትና በመስተንግዶ የተሰማሩ ሕፃናት ከፍተኛ የሆነ የጉልበት ብዝበዛ እንደሚደርስባቸውም ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን በተመለከተ የሃይማኖት አባቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርቶች፣ ባለሀብቶችና የሕፃናት ፓርላማ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን፣ ይህንን በመረዳት ሰፊ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በደቡብ እስያ አገሮች ውስጥ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ 17 ዓመት የሚደርሱ ሕፃናት ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ተዳርገዋል፡፡ ለአብነት በህንድ 5.8 ሚሊዮን፣ ባንግላዴሽ አምስት ሚሊዮን፣ በፓኪስታን 3.4 ሚሊዮንና ኔፓል ሁለት ሚሊዮን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚካሄድባቸው አገሮች መሆናቸው በመድረኩ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...