Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለድንገተኛ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ለድንገተኛ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን የሚያጠናክርና በሦስት ክልሎችና አንድ ከተማ መስተዳደር በሚገኙና በተመረጡ 45 ወረዳዎች ውስጥ የሚተገበር የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች፣ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር በሚገኙ 45 ወረዳዎች ውስጥ ለሚተገበረው ፕሮጀክት ድጋፉን ያደረገው የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የመጀመርያ ትኩረቱ ከ45 ወረዳዎች መካከል በ12 ወረዳዎች ውስጥ የማይበገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት መገንባትና የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት የልህቀት ማዕከላትን ማቋቋም ነው፡፡ በ20 ወረዳዎች የልህቀት ማዕከላትን የማቋቋም ሥራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሰው ኃይል ግንባታ ጀምሮ መረጃ ሥርዓቱን የተሻለ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን የማገዝ፣ በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንደ አገር እየተተገበሩ ያሉ ጥረቶችን የመደገፍና ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርሱ የማድረግ እንቅስቃሴም የፕሮጀክቱ አካል ናቸው፡፡

የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሲከሰቱ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎችም ዘርፍ ብዙ ሴክተሮች እንደየሥራ ባህሪያቸው ፈጣን ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን የሚያካሂዱትን እንቅስቃሴ የመደገፍና የማቀናጀት ሥራ በፕሮጀክቱ ውስጥ ተካቷል፡፡

የማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሔልዝ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዳንኤል ገመቹ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ጥገኝነት የማላቀቅ፣ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት እንዲያስችል በአገር ውስጥ የሚካሄደው የሥራ ፈጠራ ዕውን መሆን ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ሀብት የማሰባሰብን ተነሳሽነት እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ጣሃ፣ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው ወረዳዎች ሁሉ አቅም ግንባታ ከመፍጠር ጀምሮ ሞትንና ሕመምን የመቀነስ አቅም እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

የዩኤስኤአይዲ ሚሲዮን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሚስተር ቲሞቲ ስቲን፣ በፕሮጀክቱ በሚደገፉ አካባቢዎች 90 በመቶ በወረርሽኝ የሚከሰቱ ሞቶች ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው፣ ከኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችንና ሞትን 90 በመቶ ለመቀነስና የጤና ተቋማት በድንገተኛ አደጋ ጊዜ አስፈላጊ አገልግሎቶች መስጠት እንዲችሉ ተናግረዋል፡፡

ዩኤስኤአይዲ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለመደገፍና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን ለማጠናከር 12 ሚሊዮን ዶላር የለገሰ ሲሆን፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽም በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት የጤና ባለሙያዎችንና የየአካባቢውን ማኅበረሰብ አቅም በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የድንገተኛ ጤና ችግሮች ዝግጁነትና ምላሽ አቅም ለማዳበር እንደሚያስችልና ልጃገረዶችን፣ ሴቶችንና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችንም ተደራሽ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በጋራ የሚተገብሩት ማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሔልዝ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከየክልሉ ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...