Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተማሪዎች እውን እንዲሆን የሚጓጉለት የፈጠራ ሥራ

ተማሪዎች እውን እንዲሆን የሚጓጉለት የፈጠራ ሥራ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 8ኛውን ከተማ አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ዓውደ ርዕይ ከሰኔ 1 እስከ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በወዳጅነት ፓርክ አካሂዷል፡፡

‹‹በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የዳበረ ትውልድ ለአገር ብልፅግና›› በሚል በተከናወነው ዓውደ ርዕይ ከ11ዱ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡

ከ100 በላይ የፈጠራ ሥራዎች በቀረቡበት ዓውደ ርዕይ ከ11ዱ ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤትና ገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡

የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ተማሪዎች ውስጥ በሃርመኒ ሂልስ አካዴሚ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አናንያ ነብዩ ይገኝበታል፡፡ ተማሪ አናንያ ይዞ የቀረበው ‹‹ኢት ሜትሮይድ›› የተባለና በሙከራ ሒደት ያለ ሮኬት ሲሆን፣ ሥራው ተጠናቆ መወንጨፍ ቢችል በየ12 ሰዓቱ መረጃ የመልቀቅና በአካባቢው ያሉ ዘመናዊ ሚሳይሎችን የመለየት አቅም ይኖረዋል፡፡

ፈጠራው በተለይ ለኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ወቅታዊ መረጃዎችን በመልቀቅ ድጋፍ ማድረግ ያስችላል ያለው ተማሪ አናንያ፣ ሥራውን በእንጦጦ የስፔስ ሳይንስ ምልከታና ምርምር ማዕከል እየካሄደ ሲሆን፣ የጀመረው ፈጠራ እንዲሳካለት ምኞቱ መሆኑን ገልጿል፡፡

ተማሪ ቢኒያስ ወንዶሰን፣ ደኅንነት ላይ የምትሠራ ሮቦት ይዞ የቀረበ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ኢንሳ ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች ከሰጠው ዕድል ተጠቃሚ ሲሆን፣ ‹‹ናፍቆት›› የተባለች የሮቦት ፈጠራውን በተማሪዎች ዓውደ ርዕይ አቅርቧል፡፡

ተማሪ ቢኒያስ እንደሚለው፣ ‹‹ናፍቆት›› በተለይ የምትሠራው ሳይበር ሴኩሪቲ ላይ ነው፡፡ የሳይበር ጥቃት ማንኛውንም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሊገጥመው የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም፣ ሮቦቷን ይህንን ለመከላከል አልሞ ሠርቷታል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ከመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት በትምህርት ቤቶች ለመዘርጋትና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ነባሩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት የማደስና የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

 በአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እየተዘረጋ ሲሆን፣ የትምህርት ሥርዓቱን የሚያዘምነው የኢስኩል ፕሮጀክትም እየተሠራበት ይገኛል፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ቤተ ሙከራዎችና የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከላት በሮዎቻቸውን ከፍተው ተማሪዎች ተግባራዊ ምርምር የሚያደርጉበትና የሚያበለፅጉበት ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ለሦስት ቀናት በተካሄደው በከተማ አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርታዊ ዓውደ ርዕይ ላይ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት አመራሮችና የትምህርት ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡ የተሻለ ፈጠራ ያቀረቡ ተማሪዎችና መምህራን እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ከቀረቡት ውስጥ በመንገድ ደኅንነት አጠባበቅ፣ በግብርና፣ በጽዳት ቴክኖሎጂ፣ በሮኬት ሳይንስ፣ በሳይበር ደኅንነት የተሠሩ ይገኝበታል፡፡ አንዳንድ በፈጠራ ሥራ የተሳተፉ ተማሪዎች እንደነገሩንም፣ ሥራቸው ተሞክሮና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ብሎ ጥቅም ላይ ሲውል ማየት ጓጉተው የሚጠብቁት ነው፡፡

ከመደበኛ ትምህርት ጋር የፈጠራ ሥራን ለማስኬድ በሰዓት አጠቃቀም በኩል አብቃቅቶ ለመጠቀም እንደሚጠቀሙ፣ በፈጠራ ሥራ ብቻ ወይም በሳይንስና ቴክኖሎጂው የተለየ ችሎታና ዕውቀት ኖሮ በመደበኛው ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ቢኖር የተለየ ችሎታ ያለውን ሊያስተናግድ የሚችል ከፍተኛ ተቋም አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ለስምም ጥሩ አለመሆኑ የፈጠራ ሥራቸውን የበለጠ ለማስኬድ እክል እንደሆነባቸው የገለጹም አሉ፡፡

በዓውደ ርዕዩ መዝጊያ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ በበኩላቸው፣ በተማሪዎችና መምህራን የሚቀርቡ የፈጠራ ሥራዎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት መሠረት በመሆናቸው፣ ቢሯቸው የፈጠራ ሥራዎቹን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...