Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበምድር ቀጥ ብላ የተራመደችው ሉሲ

በምድር ቀጥ ብላ የተራመደችው ሉሲ

ቀን:

በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ክብረ በዓል ዋዜማ ወደ አሜሪካ ለመጀመርያ ጊዜ የተጓዘችው የ3.2 ሚሊዮን ዕድሜ ያስቆጠረችው የሉሲ ቅሪተ አካል፣ ቆይታዋን ከዓመት በላይ በዚያው ማድረጓ ለተመራማሪዎች መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡

የሉሲ ቅሪተ አካል በ1999 ዓ.ም. አሜሪካ ገብታ፣ የአምስት ዓመት ቆይታ በማድረጓ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ተመራማሪዎች፣ በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የሲቲ ስካን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ፍተሻ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ጥናት ትኩረታቸውም ሉሲ ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላ ግኝቶቻቸውን ይፋ ማድረጋቸውን በየጊዜው ተገልጿል፡፡ አንዱ ከሰባት ዓመት በፊት የሉሲ አሟሟትን በተመለከተ ይፋ የሆነው ግኝት ነው፡፡

የቅድመ ሰው ዝርያዋ ሉሲ ለኅልፈት የተዳረገችው ከዛፍ ወድቃ መሆኑን፣ በአጥንቶቿ የውስጥ ስብራቶች ላይ የሲቲ ስካን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማረጋገጣቸው በኔቸር መጽሔት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በምድር ቀጥ ብላ የተራመደችው ሉሲ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሰሞኑን ደግሞ ሉሲ ቀጥ ብላ ትራመድ እንደነበር የሚገልጽ አዲስ ጥናት ይፋ ሆኗል፡፡ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የሠሩትና በሮያል ሶሳይቲ ኦፕን ሳይንስ ጆርናል ታትሞ ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ግኝት እንደሚገልጸው፣ በዛፍ ላይ ትኖር የነበረው ሉሲ፣ በመሬት ላይ ቆማ ትራመድ ነበር፡፡

ቅሪተ አካሏ ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም. ሀዳር በሚባለው የአፋር አካባቢ የተገኘው ሉሲ፣ ቀጥ ብላ ከመራመዷ በተጨማሪ በዚህ ዘመን እንዳሉ የጦጣ ዝርያዎች በዛፎች ላይ መኖር ትችል እንደነበር ቅሪተ አካሉን መርምረው እንደደረሱበት ገልጸዋል፡፡

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ እንዳስታወቀው፣ ተመራማሪው አሽሌይ ዊስማን (ዶ/ር) የሉሲ ቅሪተ አካል ስካንን በመጠቀም የሆሚኒን አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ የእግርና የዳሌ ጡንቻዎችን በስሪዲ (3D) አምሳያ ቀርፀዋል፡፡

በዲጂታል መንገድ ዳግም የተቃኘው የሉሲ ቅሪተ አካል እንደዛሬው ቀጥ ብሎ የመቆም አቅም እንደነበረው፣ እንዲሁም የጉልበት መገጣጠሚያ መዘርጋት እንደሚችል ያሳያል፡፡ ቀጥ ብላ ትቆም እንደነበር የተነገረላት ሉሲ ቁጥቋጦ በሚበቅልበት ሜዳማ አካባቢ ትኖር እንደነበር፣ ዛፍ ለዛፍም ትንጠላጠል እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

በሳይንሳዊ ስሟ አውስትራሎፒቲከስ አፋራንሲስ በመባል የምትታወቀውና የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ባለዕድሜዋ ሉሲ፣ በአዋሽ ወንዝ አቅራቢያ ሀዳር በተሰኘ ቦታ የተገኘው ቅሪተ አካሏ፣ አንድ ሜትር ከ10 ሳንቲ ሜትር ቁመት ነበረው። 40 በመቶውን አካል የሚሸፍኑ ቁርጥራጭ ቅሪተ አካላቷም አብረዋት ነበር  የተገኙት።

ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት አሜሪካዊው ዶናልድ ጆንሰንና ፈረንሣዊው ማውረስ ታይብ ቅሪተ አካሏን ካገኙ ከሰዓታት በኋላ፣ በምሽቱ አረፍ ብለው ካዳመጡት የ1960ዎቹ የቢትልሶች ዘፈን ‹‹Lucy in the Sky with Diamond›› (በግርድፉ ሲመለስ ሉሲ ባለአልማዛዊው ሰማይ) መጠርያውን ሉሲ እንዳገኘች ይነገርላታል፡፡

ማንይንገረው ሸንቁጥ  ‹‹ባለ አከርካሪዎች›› በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ በአገርኛ አጠራር ‹‹ድንቅነሽ›› የተባለችው ሉሲን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡ ሉሲ በቀላል አማርኛ በሁለት እግሯ የምትሄድ ኤፕ (ቺምፓንዚ) መሰል አካል ነች፡፡ የጭንቅላቷ መጠን ከኤፕ ያልተሻለ ሆኖ ሲገኝ በሁለት እግሯ መንቀሳቀሷ ደግሞ ለሰው የተሻለ ቅርብ ያደርጋታል፡፡

የሉሲን ቅሪተ አካል የተለየ ያደረገው በጊዜው ከተገኙትም ሆነ አሁን ከሚገኙት አንፃር ሲታይ 40 በመቶ የሚሆነው የአካል ክፍሏም መገኘት ነው፡፡ ሉሲ ጾታዋ ታውቆ በሴት ስም የምትጠራው የዳሌዋ አጥንት በመገኘቱ ነው፡፡

ከዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት ሉሲ መሣሪያ ትጠቀም እንደነበረ በመረጋገጡ ከዚህ በፊት ይታሰብ የነበረውና መሣሪያ መጠቀም የተጀመረው በሆሞ ሀቢለስ (Homo habilus) ዘመን (ከ1.5 ሚሊዮን ዓመት በፊት) የሚለውን መረጃ ወደ ኋላ 3.2 ሚሊዮን ዓመት በፊት ይወስደዋል መባሉ ይታወሳል፡፡

ሉሲ እንዴት ሞተች?

ለአምስት አሠርታት ግድም ለዘርፉ ተመራማሪዎች የሉሲ የአሟሟት ሁኔታ፣ የቅሪተ አካሏ 40 በመቶ ያህል ተሟልቶ መገኘት እንዴትነት ጥያቄ ነበር፡፡

በ1999 ዓ.ም. የሉሲ ወደ አሜሪካ መሄድና የአምስት ዓመት ቆይታ ማድረግ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ተመራማሪዎች፣ በሉሲ አጥንቶች የውስጥ ስብራቶች ላይ በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የሲቲ ስካን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በማጥናት ነበር ሉሲ ለኅልፈት የተዳረገችው ከዛፍ ወድቃ መሆኑን ያረጋገጡት፡፡

ከሉሲ አካል፣ ከሲቲ ስካን ምርመራ፣ ሉሲ የተገኘችበት የድሮ ሥነ ምኅዳርና የአየር ንብረት መረጃዎች ጥቅል ትርጓሜ መሠረት ሉሲ ለሞት የተዳረገችው ከ12 ሜትር በላይ ከሆነ ረዥም ዛፍ ላይ በመውደቋና ወዲያውም በወንዝ ዳርቻ በሚገኝ ደለል ውስጥ መቀበሯን ግኝቱ አመልክቷል፡፡

ይኸው በአውስቲን ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ጥናት የተገኘው ግኝት በኔቸር (Nature) መጽሔት  ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...