በአበበ ፍቅር
በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁ ልጆችን ለማፍራት ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት አስተዳደር ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋል ሲል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ተማሪዎች ዘመኑ ካፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በምን መልኩ ተዋደውና ተላምደው መሄድ አለባቸው የሚለው ጉዳይም በተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችና ተሞክሮዎችም በመታገዝ ቀርቧል፡፡
ተማሪዎች ሳይንስን መሠረት አድርገው ችሎታቸውን እንዴትና በምን መልኩ ማሳደግ እንዳለባቸው፣ ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር የተግባር ልምምድ ማድረግ ይችሉ ዘንድ አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጠርላቸው ይገባለ ተብሏል፡፡
ለአንድ አገር ዕድገት መሠረት የሆነው ትምህርት በአግባቡና ወቅቱ በሚፈቅደው ሁኔታ እንዳያድግ የሚያደርጉ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በኩል ተማሪዎች በመልካም ሥነ ምግባር ታንፀው፣ ባህልና ወጋቸውን ከሳይንሱ ጋር አዛምደው እንዳያልፉ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን፣ በየጊዜው በማስረጃ አስደግፎ ሲያቀርብ መቆየቱን ትምህርት ቢሮው አብራርቷል፡፡
ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ እንቅፋት ከሚሆኑ ምክንያቶች መካከል፣ በትምህርት ቤት አካባቢ የሚከሰቱ አዋኪ ድርጊቶች እንደሆኑ ይገልጻል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በሰኔ ወር መግቢያ፣ ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር ቀይረው ያሳዩበትን ዓውደ ርዕይ ለዕይታ አብቅቶ ነበር፡፡
የዓውደ ርዕዩ አንዱ አካል የነበረው ደግሞ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ነበር፡፡ ጥናቱም በዋናነት የተማሪዎችን የሥነ ምግባር ጉድለቶች የሚዳስስ፣ ችግሮቹ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚለውን ለመጠቆም የሚያግዝ ሲሆን፣ በጥናቱ የታዩ ክፍተቶች ደግሞ ትምህርት ቢሮው በቀጣይ ለመፍታት እንደ ግብዓት የሚጠቀምባቸው እንደሆነ ተነስቷል፡፡
በጥናቱም የተማሪዎች ሥነ ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸና በተለያዩ ተፅዕኖዎች እየተገፋ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ለተማሪዎች የትምህርት አቀባበል መቀነስና ለሚያሳዩት ያፈነገጠ ሥነ ምግባር፣ መምህራን ወላጆችና ራሳቸው ተማሪዎች ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዙ ታይቷል፡፡
ከመምህሮቻቸው ጋር አላስፈላጊ እሰጣ ገባ የሚፈጥሩ ተማሪዎች እንዳሉ የተነሳ ሲሆን፣ ለዚህ እንደ ምክንያት የጠቀሱት ደግሞ ተማሪዎች አርፍደው ወደ ትምህርት ቤት መግባት፣ ከወላጆቻቸውና ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር አለመግባባትን ፈጥረው መሄድ፣ እንዲሁም አላስፈላጊና የተከለከሉ ነገሮችን ተጠቅመው ወደ ትምህርት ቤት መግባት ከመምህሮቻቸው ጋር ለመጋጨታቸው እንደ መንስዔ የተነሱ ናቸው፡፡
አስተማሪዎችም አማራጭ መፍትሔን ከመፈለግ ይልቅ አላስፈላጊና ተገቢ ያልሆኑ ቅጣቶችን መስጠት ችግሩን የበለጠ እንደሚያባብሰው ተገልጿል፡፡
የተማሪዎችን ቅጣት ተከትሎ ወላጆችም በአስተማሪዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ መልስን መስጠታቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም ሥነ ምግባር ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠታቸው የተነሳ ልጆች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ቴክኖሎጂን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ አላስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ብዙ ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
አስተማሪዎችም ለሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት በቂ ዝግጅትን ሳያደርጉ እንደሚገቡ የታየ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት በመቀነሱ ‹‹የትኛውን ተማሪ ለማስተማር እንልፋ›› የሚል አንድምታ እንዳሳዩ በቀረበው ጥናት ታይቷል፡፡
በእነዚህና በሌሎች ችግሮች ተማሪዎች አስተማሪዎችን መጥላት፣ አስተማሪዎቻቸውን ሲጠሉ አብረው የትምህርት ዓይነቱን መጥላት ሲታይባቸው፣ በሌላ በኩል አላግባብ የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በስፋት በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው እንደሆነ ታይቷል፡፡
የተማሪዎችን ዕውቀትና ሥነ ምግባር ለማሻሻል፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ይጠይቃል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓሊ ከማል ናቸው፡፡ በጥናቱ የታዩ ችግሮችንም ተባብሮ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጥሩ የተባለ ዕውቀት ቢኖራቸው፣ ሥነ ምግባር ከሌላቸው ያላቸው ዕውቀት በትክክል ሊተገበር አይችልም ያሉት ኃላፊው፣ ተማሪዎች የሚፈልገው ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አንዱ ማሳያ ብለው ያነሱት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ የሞራል ትምህርት የሚባል እንዲተገበር መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የሞራል ትምህርቱም እየተተገበረ ሲመጣ አንጻራዊ መሻሻል እንደሚያሳይ፣ ውድቀት በአንድ ጊዜ እንደማይመጣ ሁሉ፣ መሻሻል በተመሳሳይ ጊዜ አይመጣም ብለዋል፡፡ ለዚህ ቀጣይነት ለሚኖረው መሻሻል ደግሞ የወላጅና የአስተማሪ የትምህርት ቤት አስተዳደርና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ክትትል ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
‹‹ጠቅለል ብሎ ሲታይ ሁሉም ተማሪዎች ብልሹ የሆነ ሥነ ምግባር አላቸው ልንል አንችልም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ተማሪዎችን ለብልሹ ሥነ ምግባር የሚገፋፉ ሁነቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በጥናቱ ላይ የተማሪዎች ሥነ ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ ገጽታውን እየቀያየረ በመምጣት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሲያመለክት፣ የከተማዋ ትምህርት ቢሮ በበኩል ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
የተማሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለት በመማር ማስተማሩ ሒደት ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ተመላክቷል፡፡ ለችግሩ መፈጠር እንደ አንድ ምክንያት ያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በክፍል ውስጥ የመምህራን ዝግጅት ማነስን ነው፡፡
ይህንን ለመቅረፍም የመምህራን የማስተማር ክህሎትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ችግር የተነሱት የትምህርት ቤት አስተዳደር ዕርምጃዎች ቀጣይነት አለመኖሩ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡