Tuesday, October 3, 2023

የኢትዮጵያን ገጽታ ያጨፈገገው የዕርዳታ ዘረፋ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት (ተመድ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር አንድ አስደንጋጭ ዜና ለዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች ያረዱት፡፡ የሰውየውን ደብዳቤ ዋቢ ያደረጉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች፣ ‹‹በኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ ዘረፋ ተስፋፍቷል›› የሚል ተከታታይ ዘገባዎች ማራገብ ጀመሩ፡፡ እነሆ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ኢትዮጵያ ለተራቡ ዜጎች የሚላክ የምግብ ዕርዳታን ቀርጥፋ የምትበላ አገር ሆነች እየተባለ ስሟ በየመገናኛ ብዙኃኑ መብጠልጠል ቀጥሏል፡፡

ክላውድ ጂቢዳር በዚህ ደብዳቤያቸው በኢትዮጵያ የዕርዳታ እህል ዘረፋ በሰፊው መካሄዱ ድርጅታቸውን እንዳሠጋው ገልጸው ነበር፡፡ ድርቅና ግጭት ወደ 20 ሚሊዮን ዜጎቿን ለሰብዓዊ ረድኤት ፈላጊነት የዳረጉባት ኢትዮጵያ፣ ይህን መሰሉ የዕርዳታ እህል ዘረፋ መከሰቱ ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው ነበር፡፡ ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ረድኤት የሚያቀርቡ አጋር አካላት የገጠማቸው ተመሳሳይ ችግር ካለ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቀው ነበር፡፡

የክላውድ ጂቢዳር ደብዳቤ ጉዳዩ ተጨማሪ ማጣራት እንደሚካሄድበት ከመግለጽ ውጪ ዕርዳታ መዘረፉን የሚያሳዩ አጋጣሚዎችን አልጠቀሰም፡፡ ደብዳቤውን አጣቅሰው ዜና ሲሠሩ ከነበሩት አንዱ አሶሼትድ ፕሬስ ግን፣ በትግራይ ክልል በሽራሮ ከተማ ለ100 ሺሕ ሰዎች በሚበቃ የምግብ ዕርዳታ ስለመዘረፉ መረጃ አለኝ ብሎ ዘግቦ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ከተራቡ ሰዎች ነጥቆ መብላት አዲስ አይደለም ይባላል፡፡ የዕርዳታ እህልን ሸጦ መክበር የቆየ ታሪክ ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡ ከ1977 ዓ.ም. ድርቅ ጀምሮ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ተከስተው በነበሩ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች አስገዳጅነት፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት በሚጠይቁ ወቅቶች ዕርዳታ መዘረፉ በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያጋጠሙ የሰብዓዊ ረድኤት ዝርፊያዎች በርካታ መሆናቸው ተደጋግሞ ይወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 19 ቀን 2022 በወጣ ሪፖርት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመቀሌ ያከማቸው 12 ታንከር ወይም ግማሽ ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በሕወሓት ኃይሎች መዘረፉን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ይህ የነዳጅ ዘረፉ ደግሞ በክልሉ የሚካሄደውን የረድኤት አቅርቦት ሥራ የሚያደናቅፍ መሆኑን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡

ከነዳጅ ዘረፋው ቀደም ብሎ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማትና ተራድኦ ድርጀት (USAID) የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሺን ጆንስ፣ የድርጅታቸው መጋዘን መዘረፉን ተናግረው ነበር፡፡ ሺን ጆንስ የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል በወረሯቸው አካባቢዎች የድርጅቱን መጋዘኖች ሰብረው ሰብዓዊ ዕርዳታ መዝረፋቸውን አረጋግጠው ነበር፡፡ ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የሕወሓት ኃይሎች ከሕዝቡ መዝረፋቸውን ባናረጋግጥም፣ ነገር ግን መጋዘኖቻችንን በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብረው ሙልጭ አድርገው ዘርፈዋል፤›› በማለት ነበር የመሰከሩት፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይ በትግራይ ሲካሄድ በነበረው ውጊያ ወቅት፣ ከዕርዳታ እህል አቅርቦትና ሥርጭት ጋር ይነሳ የነበረው መወነጃጀል እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ነበር፡፡ ሕወሓት ተሸንፎ ከመቀሌ ወጥቶ ተምቤን በረሃ በነበረበት ወቅት፣ መንግሥትና የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የረድኤት አቅርቦት ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የአካባቢው የዕርዳታ ማከማቻና ማሰራጫ ጣቢያዎችም ተከፍተው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የረድኤት አቅርቦት ሥራ በጦርነቱ ዳግም ማገርሸት ብቻ ሳይሆን በጥቃትና በዘረፋ መስተጓጎሉ በመንግሥት ተደጋግሞ ሪፖርት ይደረግ ነበር፡፡ የረድኤት አቅርቦቱ ለተዋጊዎች እየዋለ ነው የሚል ቅሬታም መንግሥት ያሰማ ነበር፡፡ በሕወሓት በኩል ደግሞ በቂ የዕርዳታ አቅርቦት የለም የሚል ሪፖርት ነበር ሲቀርብ የቆየው፡፡ የዕርዳታ አቅራቢዎች በሚፈለገው ልክ እንዳይንቀሳቀሱ መንግሥት እንቅፋት ይፈጥራል የሚል ውንጀላም ሕወሓት ያቀርብ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በኩል ተጠንቶ መቅረቡ የሚነገርለት የሰብዓዊ ረድኤት ፈላጊዎች ቁጥር ሪፖርት (Food Security Phase Classification IPC) ከፍተኛ አለመግባባት የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡ በወቅቱ ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ዜጎች እየተባለ ይቀርብ የነበረው አኃዝ ወደ አምስት ሚሊዮን እንደሚጠጋ መነገሩ፣ በመንግሥትና በአንዳንድ ወገኖች በኩል አሳማኝነት አላገኘም ነበር፡፡

የተጋነነ የዕርዳታ ፍላጎት አኃዝ በማቅረብ ከውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች የበዛ ዕርዳታ ለማግኘት የተጎነጎነ ሴራ አለ ያሉ ወገኖች ጉዳዩን ሲተቹት ተስተውለዋል፡፡ የዕርዳታ እህል በገፍ በማስገባት ሕወሓትን የበለጠ ለማጠናከር የሚደረግ ጥረት ስለመኖሩ ግምታቸውን ሲያሰሙም ነበር፡፡

በ1977 ዓ.ም. በረሃብ ለተጠቁ ወገኖች የገባ የዕርዳታ አቅርቦትን በመቸብቸብና በመሣሪያ በመለወጥ ሕወሓት የቀደመ ታሪክ እንዳለው ያጣቀሱ ወገኖች፣ በአዲሱ ጦርነትም ይኼው እንዳይደገም መወትወታቸውን ቀጥለው ነበር፡፡

እንደ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ ግደይ ዘርዓ ጽዮን ገብረ መድኅን አርዓያ የመሳሰሉ ነባርና መሥራች የሕወሓት ታጋዮች ጭምር በ77 ድርቅ ወቅት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ይላክ የነበረ የሰብዓዊ ረድኤት በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ለጦር መሣሪያና ለጦርነት መጠቀሚያነት ይውል እንደነበር በተለያዩ መንገዶች አረጋግጠዋል፡፡

ይህን የምግብ ዕርዳታ ለጦርነት የማዋል ሴራ ደግሞ ቢቢሲ በምርመራ ዘገባ ያጋለጠ ሲሆን፣ የአሜሪካው ስለላ ድርጅች ሲአይኤም ይህንን ጉዳይ በሪፖርት አጠናቅሮ በሰነድ ለታሪክ አቆይቶታል፡፡ በ2013 ዓ.ም. በጀመረው የትግራይ ጦርነትም ይህ ታሪክ እንዳይደገም ያሳሰቡ ወገኖች በረድኤት አቅርቦቱ ሥርዓት ላይ ጥብቅ ክትትል እንዲካሄድ ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የዕርዳታ አቅርቦት ጉዳይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረትን እንደሳበና ከባድ መወዛገቢያ እንደሆነ ነው የቀጠለው፡፡

የዕርዳታ አቅርቦትን ለጦርነት ይጠቀማል የሚለው ውንጀላ መንግሥትንም ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎችን በማስራብ በሚል ውንጀላዎች ተደጋግሞ ሲከሰስና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ላይ ጭምር ስሙ ሲብጠለጠል የታየበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች የወጡ መረጃዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች የተጋነኑና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ያልተመረኮዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ተወካይ ማውሪን አቼንግ በትግራይ በረድኤት አቅርቦት ስም ስለሚሠራው አሻጥር መረጃ ማውጣታቸውን ተከትሎ ከሥራ መባረራቸው፣ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጎ ነበር፡፡ ሴትየዋ ከአንዲት የተመድ የረድኤት ድርጅት ባልደረባ ጋር ሆነው የሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በካናዳዊው ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርስ በኩል አፈትልኮ መውጣቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ሁለቱ ሴቶች ከዕርዳታ ፈላጊዎችና ከዕርዳታ አቅርቦት ጀምሮ፣ በጅምላ አስገድዶ መድፈር ወንጀል ጉዳይ ላይ የሰጡት መረጃ በሰብዓዊ ረድኤት ስም መንግሥት ላይ ሲቀርቡ የነበሩ ውንጀላዎች የተጋነኑ እንደነበሩ ጠቋሚ ነው ተብሎም ነበር፡፡ በትግራይ ክልል የረድኤት አቅርቦት ጉዳይን ለጦርነት እያዋለ ነው መንግሥት መባሉ አሳማኝነት እንደሌለው፣ የሕወሓት ኃይሎችም ይህንኑ የዕርዳታ አቅርቦት አጀንዳ ይጠቀሙበታል የሚል ሐሳብን ያጠናከረ ነበር፡፡

በጦርነቱ ወቅት የዕርዳታ አቅርቦትና ሥርጭት ጉዳይ የቃላት ጦርነት፣ የሚዲያ ፍጭትና የመግለጫ ውዝግብ መካፈቻ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄው የሰብዓዊ ረድኤት ሥርጭት ለሥርዓት አልበኝነትና ለሕገወጥ ድርጊቶች እየተጋለጠ ይገኛል የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ ይሰማም ነበር፡፡ አንደ ሰሞን በአጣዬ ከተማ ደርሶ በነበረው ግጭት ሲቀርብ የነበረው ዕርዳታ ለተገቢው ተረጂ ኅብረተሰብ በአግባቡ መቅረብ አልቻለም የሚል ሪፖርት መውጣቱ፣ ጉዳዩ ትኩረት እንደሚፈልግ አመላካች ሲባል ቆይቷል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ከመቼውም ጊዜ በላይ የዕርዳታ ጥያቄን ያስከተሉ ችግሮች በአገሪቱ መጨመራቸው፣ የዕርዳታ አሰባሰብ ሥርዓቱን በአግባቡ ለመምራት ፈታኝ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በጦርነትና በግጭት ተጎጂ ለሆኑ ብቻ ሳይሆን በቦረናና በሶማሌ ክልል ላጋጠሙ የድርቅ አደጋዎችም በየአቅጣጫው የሚሰበሰበውና የሚሠራጨው ዕርዳታ ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ በርካታ ጉተጎታ የሚጋብዝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለሥልጣናት እስር ሲጨመር ደግሞ በጉዳዩ ላይ ትኩረቱ ጨምሮ ነበር፡፡

ይህ ጉዳይ በይደር እንዳለ ደግሞ ካለፈው ወር ጀምሮ የዕርዳታ እህል ዘረፋ ከባድ የፖለቲካ ውዝግብ የሚያስነሳ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ዋሽንግተን ፖስት በተለይ ያወጣው የምግብ ረድኤት እየተዘረፈ ለገበያ እንደሚቀርብ እንደተደረሰበት የሚያረጋግጥ ሪፖርት የውዝግቡ ዋና ማዕከል ሆኗል፡፡

በሰባት ክልሎች የዕርዳታ እህል እንደሚዘረፍ ደረስኩበት ያለው ሪፖርቱ፣ በአንዳንድ ክልሎች የዕርዳታ እህልን እየተረከቡ የሚያቀናብሩ የዱቄት ፋብሪካዎች ሁሉ ስለመከፈታቸው በሰፊው አትቷል፡፡ በሶማሌና በትግራይ ክልሎች የተገኙ ማሳያዎችን የሚያነሳው ሪፖርቱ፣ የምግብ እህል የሚፈልጉ 20 ሚሊዮን ተረጂዎች ባሉባት ኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ በሰፊው መዘረፉን በጥልቀት ያቀርባል፡፡

ይህ ሪፖርት ሰፊ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረ መልሶችም እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማትና ተራድኦ ድርጅት ዕርዳታ ማቋረጡን በይፋ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ለ12 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ዕርዳታ በማቅረብ የምትጠቀሰዋ አሜሪካ ይህን ዕርምጃ መውሰዷ፣ የአገሪቱን ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያከፋ በስፋት ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡

በሌላ በኩል የአሜሪካኖችን ዕርምጃ የተከተለ ተመሳሳይ ውሳኔ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መውሰዱን ይፋ አድርጓል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀትም ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የምግብ ዕርዳታ ማቋረጡን ይፋ አድርጓል፡፡

ሰሞነኛው የዕርዳታ እህል ዘረፋ ሪፖርት በዓለም ምግብ ፕሮግራም ውስጥ ቀውስ ሲፈጥር ታይቷል፡፡ ከሁሉ ቀድመው የእህል ዘረፋ እያጋጠመ ስለመሆኑ ለተመድ የረድኤት ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ ይፋ ያደረጉት፣ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳርና ምክትላቸው ጄኒፈር ቢቶንዴ ከሥራ ለቀቁ መባሉ ጉዳዩ ተጨማሪ ትኩረት እንዲስብ ያደረገ ነበር፡፡

ከቀናት በፊት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ለዚህ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ክስ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ ‹‹መንግሥት ዕርዳታን ከታለመው ዓላማ ውጪ የሚያውሉ አካላት ካሉ በሕግ እንዲጠየቁ ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ (የዓለም ምግብ ፕሮግራም) ደረስኩበት ብሎ የሚያቀርበው ሪፖርት ከየትኛውም የመንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ጋር በጋራ ያልተሠራና ያልተጠና፣ በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

ለገሰ (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹አጋር አካላቱ ዘረፋው ተፈጸመ በሚሉባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች የዕርዳታ ሥራዎችን አቅርቦትና ሥርጭት በራሳቸው ብቻ እንደሚመራ ረስተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ጥፋት እንኳ ቢኖር በጋራ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እየተቻለ፣ መንግሥትን ብቻ ጥፋተኛ በማድረግ ሚሊዮኖችን በረሃብ ለመቅጣት ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢነት የሌለው ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡

ከሰሞኑ የተፈጠረው የምግብ እህል ዘረፋ ሪፖርትን የተከተለው ችግር የመንግሥትና የዕርዳታ ድርጅቶች መወዛገቢያ ብቻ ሆኖ አልቆመም፡፡ ለወትሮም ከረሃብ፣ ከጦርነት፣ ከድርቅና ከችግር ተላቆ የማያውቀውን የኢትዮጵያን ስም በክፉ እንዲነሳ ነው ያደረገው፡፡ ኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት አደረገች በተባለ ማግሥት ይህ ጉዳይ ገዝፎ መምጣቱ አጀንዳው የማን ነው የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

ለሁለት አሥርት ዓመታት በአንፃራዊነት በልማት ስኬቶችና በዕድገት ስሟ ሲጠራ የቆየችው፣ ኢትዮጵያ ዳግም በዕርዳታ ዘረፋ ስሟ መጠራት መጀመሩ የአገሪቱን በጎ ገጽታ ወደ 1977 ዓ.ም. እንዳይመልሰው እየተሠጋ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -