Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹ክበብ ዳር ዳሩን ክበብ…››

‹‹ክበብ ዳር ዳሩን ክበብ…››

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ድሮ ጥንት፣ እንዲህ እንደ ዛሬ ለሰው ልጅ ከማደራቸውና ከሰው ጋር እቤት ውስጥ መኖር ከመጀመራቸው ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት ድመቶችና አይጦች ‹‹ግራጵያ›› በተባለ ክፍለ ዓለም ጥሩ ጎረቤቶች ሆነው አብረው ይኖሩ ነበር ይባላል። እንደዚያ ሲኖሩ፣ ሲኖሩ፣ ሲኖሩ በመላው ዓለም አሰሳ የሚያደርግ ሸለመጥማጥ ‹‹ኤርጵያ›› ከተባለ ክፍለ ዓለም ተነስቶ በመርከብ ሲጓዝ ባህር ላይ በተነሳ ማዕበል መርከቡ ተገፍትሮ ወደ ዓለማቸው መጣ።

እርሱ ከባህር ተገፍትሮ እንደመጣም በባህሩ ወደብ በርካታ ድመቶችና አይጦችን አየ። ሆኖም አይጦች ዓይን አፋሮች ስለነበሩ በፍጥነት ወደየጉድጓዶቻቼው ገቡ። እሱ በመጣበት ዘመንም በ‹‹ግራጵያ›› ረሃብ ሰፍኖ ነበር። ስለሆነም ምግብ ይዞ እንደሆነ ጠየቁት።

በዚህ ጊዜ ሸለመጥማጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሳቀና ‹‹እና ይህ ሁሉ አይጥ ሞልቶ በረሃብ ልታልቁ ነዋ!›› አላቸው እየተደነቀ። ድመቶችም አይጥ የድመት ምግብ መሆኗን አያውቁም ነበርና ‹‹ምን ይደረግ፣ ምግብ ካለገኘንማ ከኛ ቀድመው እንደሞቱት ወገኖቻችን ተርበን መሞት ነው እንጂ ምን አማራጭ አለ?›› ሲሉ እያዘኑ መለሱለት።

ሸለመጥማጥም ‹‹ለጊዜው የተወሰኑ ዓሳዎች ስላሉ እነሱን ውሰዱ፤›› አለና ትንሽ ካሰበ በኋላ ‹‹እኔ የምለው፣ በሌላው ክፍለ ዓለማት ድመቶች የሚመገቡት አይጥን ነው። ስለዚህ እናንተስ እንደዚያ አታደርጉምና ሕይወታችሁን አታድኑም?›› በማለት ጠየቃቸው።

ድመቶች በአካባቢያቸው አይጦችን የመብላት ባህል አለመኖሩንና በጣም ፈጣኖች በመሆናቸው ሊይዟቸው እንደማይቻሉ ገልጸው እንዴት ሊበሏቸው እንደሚችሉ ጠየቁት። ሸለመጥማጥም ‹‹ይህ በእውነቱ ቀላል ነገር ነው። በመጀመርያ ‹‹እንጋባ›› ብላችሁ ጠይቋቸው። ከዚያ እየያዛችሁ መብላት ነው፤›› ሲል ነገራቸው። ዕቅዱንም ነደፈላቸው። አደፋፈራቸው። የሠርግ ዘፈንም ደረሰላቸው። እሱም ሽማግሌ ሊሆን እንደሚችል አብራራላቸው።

በዚህ ተስማምተውም ሸለመጥማት ሽምግልና ተላከ። አይጦችም ትንሽ ተግደርድረው ይሁንታቸውን ገለጹ። የጋብቻው ቀን ተወሰና በዓይጦች ቤት ድግሥ መደገሥ ተጀመረ።

ሆኖም የአይጦች ወዳጅ የሆነችው ‹‹ድንቢጥ›› የተባለችው ወፍ ደረሰችና ‹‹ክቡራን አይጦች። እኔ ምን እንደሚዶለትባችሁ በሚገባ ሰምቻለሁ። ስለዚህ የድግሥ ሥራችሁን ትታችሁ ከሞት የሚያድናችሁን ማሳ ቆፈሩ። በየጉድጓዶቻቸው በርም ቆሙ፤›› በማለት መከረቻቸው። እነሱም በተሰጣቸው ምክር መሠረት ድመቶችን ሊያስገባ የሚችል ጉድጓድ ቆፈሩ። በየመግቢያቸው ሆነውም በጥንቃቄ መጠበቅ ጀመሩ።

ከዚያም ድመቶች የሠርጉን ቀን ጠብቀው ሆ! እያሉ መጡ።

አውጭ – ክበብ ዳርዳረን ክበብ፤

ተቀባይ – ዳርዳሩን ክበብ

አውጭ – ክበብ አንድም አንዳይቀር

ተቀባያ – ዳር ዳሩን ክበብ

አውጭ – ክበብ ከእንግዲህ ወዲያ፣

ተቀባይ – ዳር ዳሩን ክበብ፣

አውጭ – ክበብ ረሃብ አይኖርም

ተቀባይ – ዳርዳሩን ክበብ

አውጭ – ክበብ እየያዝክ ቆርጥም

እያሉ መጡ። ድንቢጥም የሚሉትን እየበረረች ትከተላቸው ነበርና ወደ አይጦች በመሄድ ‹‹በሉ እየመጡባችሁ ነውና ‹እኛም አውቀናል ድንኳን ምሰናል› እያላችሁ እስከሚቀርብ ዝፈኑላቸው ከዚያም ወደየጉድጓዶቻችሁ በፍጥነት ግቡ፤›› በማለት መከረቻቸው።

በዚህም መሠረት ድመቶች

‹‹ክበብ ዳር ዳሩን ክበብ

እንዳትለቃት›› እያሉ ሲመጡ

አይጦችም ‹‹እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል›› በማለት ድመቶች ሊበሏቸው ሲሉ በየጉድጓዶቻቸው ጥልቅ አሉ። ይባላል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከኤርጵያ በመጣችው ሸለመጥማጥ ምክንያት አይጦችና ድመቶች ባላጋራ ሆነው ቀሩ ይባላል።

ማስታወሻ ‹‹እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል›› የሚለው የቆየና በሁለት ዓረፍ ተነገር የሚገለጽ ተረት ሲሆን፣ ሸለመጥማጥንና ወፍን የጨመርኩትና ተረቱን ያሳደግኩት እኔ ነኝ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...