Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ብቻውን የነዳጅ ጥቁር ገበያን አይገታምና ይታሰብበት!

በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎቶችን ለማዘመን እየተካሄዱ ካሉ ተግባራት መካከል ዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሥርዓትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ በተለይ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግን ግብይትን ለመቀነስ የተጀመሩ ጥረቶች ለውጥ እያመጡ ነው፡፡ የተጠቃሚዎችም ቁጥር እየበዛ ነው፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 63 በመቶ የሚሆነውን የገንዘብ እንቅስቃሴ በዲጂታል አማራጮች ማከናወኑን መግለጹ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት የዘርፉ አንድ መወዳደሪያ እየሆነ መምጣቱም ልብ ይሏል፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መተግበር የጀመረው የዲጂታል የነዳጅ የክፍያ ሥርዓት ደግሞ በተጓዳኝ ሕጋዊ አሠራሮችን ከመከወን አንፃር ሲታይ ጠቀሜታው በተለያየ መንገድ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ በዓመት ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት የሚፈጸምበትን የነዳጅ ምርት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ብቻ እንዲሳለጥ ለማድረግ መነሳት በራሱ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመተግበር ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ አንዳንድ ባንኮች ተሳታፊ በማድረግ በጥሬ ገንዘብ ብቻ ይካሄድ የነበረውን የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ማስገባት እየተቻለ ነው፡፡

አገልግሎቱ አስገዳጅ በመሆኑ ነዳጅ ለመቅዳት ጥሬ ገንዘብ ይዞ መቅረብ አሁን ላይ ቀርቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግብይቱን አስመልክቶ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

ዲጂታል የነዳጅ ክፍያ አገልግሎት መጀመሩ የጥሬ ገንዘብ ግብይቱን ከማስቀረት ባሻገር እጅግ የበዛ ሻጥር ሲሠራበት የቆየውን የነዳጅ ሥርጭት አደብ በሕጋዊ መንገድ እንዲጓዝ የሚችል መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ የተወሰነ ውሳኔ ነው፡፡

አንድ የነዳጅ ኩባንያ ነዳጁን ለማን እንደሸጠ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራርን ስለሚፈጥርም ጠቀሜታው የጥሬ ገንዘብ ግብይት ለማክሰም ብቻ ያለመ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመከራ ከሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ተገምሶ የሚገዛ ነዳጅ ከወደብ ወደ ጎረቤት አገሮች እንዳይጫን፣ በየመንገዱ የሚደረግን ቅሸባ ለማስቀረት ወይም እንዲህ ያሉ ሕገወጥ ተግባራትን በቀላሉ ለመቆጣጠር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል፡፡

የነዳጅ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መጀመርን አስመልክቶ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ እንዳመላከቱትም፣ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቱ በነዳጅ ግብይትና ሥርጭት ውስጥ ይታይ የነበረውን ሕገወጥነት ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም የአገር ሀብት ያላግባብ እንዳይባክን እንደሚያግዝ በመረጋገጡ አሠራሩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል እንዲተገበር ተደርጓል፡፡ ነዳጅ በመቀሸብና ከነዳጅ ማደያዎች ከተሽከርካሪዎች ውጭ በበርሜልና በመሰል መያዣዎች የሚሻገር ነዳጅ እንዳይኖር የሚያደርግ ሕገወጥ ተግባራትን ለመቀነሰም የሚረዳ በመሆኑ፣ ይህንን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ግድ ስለመሆኑም ሰጥተው ከነበረው ማብራሪያ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሁንና በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ካሉ የተለያዩ ከተሞች በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ የነዳጅ ግብይት በግልጽ እየተካሄደ መሆኑ ግን አሁንም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያመለክታል፡፡

በነዳጅ ማደያዎች የለም የተባለ ነዳጅ በጀሪካን ተሞልቶ በአዲስ አበባ ከተማ ይበልጡኑ በአንዳንድ የክልል ከተሞች በሕገወጥ መንገድ እየተቸበቸበ ከሆነ ደግሞ የዲጂታል ክፍያው ሥጋት ጎን ለጎን ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ገና የሚቀረው እንደሆነ ያሳየናል፡፡ 

ከሰሞኑ እንደሰማነው ጉምሩክ በቁጥጥር ሥር አዋልኳቸው ብሎ ከገለጻቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ ነዳጅ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይቱ አሁንም ደርቷል ወደሚል አመለካከት ይወስደናል፡፡ ነገሬን በምሳሌ ለማዋዛት ከሰሞኑ ከውጭ የመጣ ጓደኛዬ የገጠመው ልጥቀስ፡፡ ጓደኛዬ ቤተሰቡን ይዞ አዳማ ቆይቶ ሲመለስ በቂ ነዳጅ ስላልነበረው አዳማ ከተማ ከሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች በአንዱ ሠልፍ ይይዛል፡፡ ከቆይታዎች በኋላ ማደያው ሠራተኞች ነዳጅ ማለቁን ይገልጹና ተሠልፈው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ሌላ ነዳጅ ማደያ ፍለጋ ይሄዳሉ፡፡ ጓደኛዬም ይህንኑ ማድረግ ግድ ይለው ነበርና በአቅራቢያው ወዳለው ወደ ሌላው ነዳጅ ማደያ አመራ፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚያጠፋውን ጊዜ መቋቋም እስኪያቅተው ድረስ ጠበቀ፡፡ እዚህም ነዳጅ አለቀ ተባለ፡፡ በወቅቱ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ነበረበትና ለመመለሻ የሚሆነውን ያህል ነዳጅ ለማግኘት እዚያ ያሉ ዘመዶቹን አማራጭ ካለ ብሎ ይጠይቃል፡፡

ዋጋው ውድ ይሆናል እንጂ እንደሚገኝ ይነገረዋል፡፡ በጀሪካን ነዳጅ ሞልተው ይሸጣሉ የሚባሉ ሰዎች አሉበት የተባሉ ቦታዎችንም ይጠቀሙበታል፡፡

እዚያ መሄድ ሳያስፈልገው ያለበት ድረስ የሚያመጡ አሉ ይባልና የነዳጅ ሻጮች ስልክ ተፈላልጎ ይደወላል፣ እንደተባለውም የሚፈልገውን ያክል ነዳጅ እንደሚያመጡለት ይነግሩትና ይህንኑ ያደርጋሉ።

ሻጮቹም የጠየቀውን ያክል ቤንዚን ያመጡና ሊትር 150 ብር መሆኑን ያሳውቁታል፡፡ ወዳጄም አማራጭ ስላልነበረው በጀሪካን የመጣለትን ቤንዚን በተባለው ዋጋ ለመሸመት ተገዷል፡፡ እዚህ ላይ የሚገርመው እነዚህ ሕገወጥ የነዳጅ ሻጮች ሲጠየቁ በፍጥነት መድረሳቸው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ሲያደርጉ የሚቆጣጠራቸው አለመኖሩ ነው፡፡ ጓደኛዬ ነዳጁን የገዛው ከነዳጅ ማደያዎች ከሚሸጥበት እጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ መግዛቱን ልብ በሉ፡፡

ነዳጅ ከነዳጅ ማደያዎች ውጭ መሸጥ እንደማይቻል በግልጽ የተደነገገና በተለይም በዚህ ወቅት ነዳጅ ለመቅዳት የግድ ተሽከርካሪው ማደያ መገኘት አለበት፡፡ ከዚህም ሌላ ግብይቱ የሞባይል ስልክን በመጠቀም የሚፈጸም ነው፡፡ በዚህ ግብይት ሥርዓት ነዳጁን የሚያቀርብለት ተሽከርካሪ ታርጋው ይያዛል፣ ማንነቱም ይመዘገባል፡፡ አሠራሩ ይህ ከሆነ እንዲህ ያሉትን አሠራሮች ተላልፎ ነዳጅ መሸጥ አይቻልም ማለት ነው፡፡ በሕገወጥ መንገድ እንደ ልብ የሚሸጥ ነዳጅ ከየት የመጣ ነው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ እንዲያስነሳ ያደርጋል፡፡

ምናልባትም ባለፈው ሳምንት በአዳማ ጓደኛዬ ነዳጅ ለመቅዳት ተሠልፎ አለቀ የተባለበት ዋና ምክንያት እነዚህ ነዳጅ ማደያዎች በለመደ እጃቸው እንደ ቀድሞው ለሕገወጦች ነዳጅ ቸርቻሪዎች አሻግረው የሚሰጡበት ቀዳዳ አግኝተዋል ማለት ነው፡፡ 

ስለዚህ አሁን እየተተገበረ ያለው የዲጂታል የነዳጅ ግብይት አገልግሎት ነዳጅን በዲጂታል መንገድ መገብየት ያስቻለ ቢሆንም፣ በሕገወጥ መንገድ በውጭ የሚሸጠውን ነዳጅ እያስቀረ አይደለም ማለት ነው፡፡

እንደተባለው የነዳጅ ማደያዎች ምን ያህል ነዳጅ አስገብተው ምን ያህሉን ነዳጅ በሕጋዊ መንገድ ለተጠቃሚዎች እየሸጡ ነው? የሚለውን ለማረጋገጥ የሚያስችለው አሠራር ገና ያልፀና መሆኑን የሚጠቁምም ነው፡፡ በመሆኑም በርካታ ብልሹ አሠራሮችን ጭምር ማስተካከል ያስችላል የተባለው የክፍያ ሥርዓት አሁንም መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቱ የተበጀው ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠርና ግድፈት ከተገኘም ዕርምት ለመውሰድ፣ ገፋ ሲልም ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ታልሞ በመሆኑ፣ ከማደያዎች ውጪ እየተቸበቸበ ያለው ነዳጅ የት ነው? ብሎ መቃኘትም ግድ ይላል፡፡

ማን ምን ያህል ተረክቦ ምን ያህሉን ሸጠ? የሚለውን ለመለየትም የዲጂታል አገልግሎት ደግሞ ትልቅ ዕገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ማደያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ነዳጅ ወደ ጥቁር ገበያ እየተሻገረ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ዘረጋን ብቻ ማለቱ ስኬት ሊሆን አይችልም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት