በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማት የሚለካበት ብዙ መለኪያዎች አሉ፣ እነዚህ መለኪያዎች እንደየተፈለጉበት አግባብ ልኬታቸው ይወሰዳል፣ ለማጣቀሻነትም ይውላል፡፡ ነገር ግን ልማት ፈርጀ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ እያንዳንዱ ልማት የሚለካበት መመዘኛ ከሞላ ጎደል ቢኖርም፣ በቂና የተሟላ ግን አይደለም ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ለአብነትም በአንድ አገር በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ምርትና አገልግሎት ቀርቦ ምን ውጤት ተገኘ? የሚለውን ለመመዘን ጥቅም ላይ ከሚውሉ መመዘኛዎች መካከል ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) በዋነኛነት ይጠቀሳል፣ በኢትዮጵያም ጂዲፒ ዋናው መመዘኛ ነው፡፡ ነገር ግን መመዘኛው የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖችና ድክመቶች እንዳሉበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ምሁራን ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) የማያካትታቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይም የሚሰጡት ምስል ጥቅል እንደመሆኑ መጠን፣ በተናጠል ክልሎችና ከዚያም በታች ባለው የአስተዳደር እርከን ያለው አጠቃላይ የልማት ደረጃ ምን እንደሚመስል ፍንተው አድርጎ የማሳየት ውስንነት እንዳለበት እንዲሁ ይገለጻል፡፡
ልማትም ሆነ ሌሎች ቁልፍ ማኅበራዊ ነክ ዕድገቶች በጥቅሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ከመጠናታቸው ውጪ በተናጥል ተለይተው እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ ያላቸው የዕድገት ሁኔታና ደረጃ አይመዘንም። ይህንን ማድረግ በአገሪቱ የተገኘውን መልካም ውጤትም ሆነ ክፍተት ከሥረ መሠረቱ ለማወቅና ብሎም ሊተገበሩ የሚገባቸውን የፖሊሲ ማስተካካያዎች ለማመላከት መሆኑ አሻሚ አይደለም፡፡
ይህንን ዕርምጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በመተግበር የኦሮሚያ ክልል ቀዳሚ የሆነ ሲሆን፣ የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ጋር በመሆን አራት የተለዩ ዘርፎችን በማስጠናት ግኝቱን ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢኮኖሚክስ አሶሼሽን ይፋ ሆኖ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከአራቱ ጥናቶች ውስጥ በአገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ላይ የተጠናው የሰብዓዊ ልማት ምዘና (Human Development Inde-HDI) ይጠቀሳል፡፡
ጥናቱ በኦሮሚያ ክልል መደረጉ በክልሉ ያለው የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ዕድገት በተናጠል ምን ይመስላል? የሚለውን በማሳያነትና የፖሊሲ መፍትሔዎችን በማቅረብ የክልሉን አቅም ለማሳደግ ጥቅም ላይ እንደሚውል ታምኖበታል፡፡
በተጨማሪም አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ ዕቅዶችን ለማዘጋጀት እንዲሁም ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ እንደሚያግዝና የተቀረጹትን ዕቅዶች መሠረት በማድረግም ሕዝብ ተኮር ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች እንዲዋሰኑ ያስችላል ተብሏል፡፡
ለተደረገው ጥናትም ከ11 ዓመት በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፣ ከኦሮሚያ ፕላንና ልማት ኮሚሽንና ከሌሎች ርዕሰ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልል ተቋማት የተገኙ መረጃዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ የሆኑት አደም ፈቶ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፣ በኦሮሚያ ክልል ፕላንና ልማት ኮሚሽን ጥያቄ አቅራቢነት አሶሴሽኑ የሰብዓዊ ልማት ምዘናን እንደ አንድ የዕድገት መለኪያ በመለየት ጥናት ተደርጓል፡፡
የሰብዓዊ ልማት ምዘና (መለኪያ) ከዚህ ቀደም ዕድገት ለመለካት ጥቅም ላይ ከሚውሉት ጂዲፒና ሌሎች ዕድገት መለኪያዎች የተሻለ መሆኑን የሚያስረዱት አደም (ዶ/ር)፣ ለአብነትም ጂዲፒ ኢኮኖሚን ወይም ገቢን ለመለካት ብቻ የሚውል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በአንፃሩ የሰብዓዊ ልማት ምዘና (HDI) ከኢኮኖሚ በተጨማሪ የትምህርትና ጤና ተግባራትን የሚያመላክት በመሆኑ የተሻለ እንደሚያስብለው ተመራማሪው አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው ይህ መለኪያ ሦስት ዘርፎችን በመለየት በክልሉ ያለውን ሁኔታ የመዘነ ሲሆን በዚህም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና ሰው ተኮር ተብለው የተለዩትን ዘርፎች (ትምህርትና ጤና) የሚያጠቃልል ነው፡፡
በጥናቱ እንደተረጋገጠው ከ2008 እስከ 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ያለው የዜጎች ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዚ እየጨመረ መምጣቱን ምዘናው ያሳያል፡፡ የምዘና ውጤቱ እንደሚያመለክተውም በክልሉ የሰብዓዊ ልማት ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2018 ከነበረበት 0.492 ወደ 0.45 መሻሻል አሳይቷል (አኃዙ መቀነስ መሻሻልን ያመለክታል)፡፡
አደም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከጂዲፒ በበለጠ ባለፉት ስድስት ዓመታት የጤናውን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች በድምሩ የአሥር በመቶ መሻሻል አለ፡፡ ለተገኘው የአሥር በመቶ የዜጎች ዕድገት መሻሻል ምክንያቱ የጤና አገልግሎት መሻሻል ያበረከተው አስተዋፅኦ ሲሆን፣ በአንፃሩ የጎልማሶች ትምህርትና ጂዲፒ አነስተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መመታት፣ እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት (Hyper Inflation)፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንዲሁ አለመረጋጋቶች ነበሩት፡፡
የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ሌላው የሚጠቀስ ጉዳይ ሆኖ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ አልፎ የተገኘው (አሥር በመቶ) መሻሻል፣ በበጎ የሚታይ ነው ይላሉ አጥኚዎቹ፡፡
የሰብዓዊ ልማት ምዘና አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያመለክት እንጂ በፆታ መካከል ያለውን ሁናቴ የማያሳይ በመሆኑ፣ የማኅበሩ አጥኚዎች የፆታ ዕድገት ኢንዴክስ (Gender Development Index) የሚለውንም አስልተዋል፡፡
ግኝቱ እንደሚሳየው በኦሮሚያ ውስጥ በሴቶችና ወንዶች መካከል ያለው ልዩነት በዕድገት መለኪያ ሲታይ ልዩነቱ እምብዛም ቢሆንም የበለጠ መሠራት እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡ በአንፃሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የፆታ ልዩነት ሲታይ ከኦሮሚያ ክልል በጣም የተሻለ ነው ሊባል የሚችል ነው፡፡
የሰብዓዊ ልማት ምዘና ኢንዴክሱ ደረጃ ሲቀመጥ በአራት ጎራ የሚከፈል ሲሆን፣ በጣም ዝቅተኛ፣ ዝቅተኛ፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ የሚሉት ናቸው፡፡ ከአራቱ መለኪያዎች የኦሮሚያ ዝቅተኛ የሚባለው ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ዝቅተኛ ሆኖ ወደ መካከለኛው ጠርዝ የሚወስደው ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡ ይህም በቀጣይ ብዙ መሻሻልና መስተካከል የሚገባቸው አገሮች እንዳሉ ያሳያል፡፡
ከትምህርት አንፃር በኦሮሚያ ክልል የክፍል ተማሪ ጥመርታው ሲታይ በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ እ.ኤ.አ. እስከ 2019 በክፍል 50 ተማሪ የነበረ ሲሆን፣ በ2022 ግን ወደ 48 ዝቅ ብሏል፡፡ በአንጻሩ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2022 ያለው አማካይ ቁጥር 28 ነው፡፡ ስለሆነም የዜጎች ዕድገት መለኪያ የሚባለው ይህ መለኪያ እንዲሻሻል የግድ ይላል፡፡
ከጤና ዘርፍ አኳያ ሲታይ ምን ያህል ሐኪሞች፣ ነርሶችና የጤና ቴክኒሻኖች ለአንድ ሺሕ ሰዎች አሉ በሚለው መመመዘኛ በኦሮሚያ ክልል 1.73 የሚል አኃዝ ይገኛል፡፡ ይህም የዓለም የጤና ድርጅት ካወጣውና 2.3 ከሚለው ዝቅ ያለና በቀጣይ በርካታ የጤና ባለሙያዎች በስፋት መቀጠር እንዳለባቸው፣ የጤናው ዘርፉ አሁን ካለበት መሻሻል እንዳለበት፣ የዜጎች ዕድገት መሥፈርቱም አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ እንዲሸጋገር ካሁን ማሰብ የሚጠይቅ መሆኑን ያመላክታል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የአንድ ሰው አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ (Gross National Income Per Capita – GNI)) ሁለት ሺሕ ዶላር አካባቢ መሆኑን የሚያመላክተው ጥናቱ፣ ይህ 60 ሺሕና 80 ሺሕ ዶላር ካላቸው አገሮች ጋር ሲወዳደር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በክልሉ ያለውን አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻል እንዳለበት ይታመናል፡፡
በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለው የዕድገት ልዩነት በአገር ደረጃ 2.3 በመቶ መሆኑንና ይህም እመርታን የሚያሳይ እንደሆነ የጠቀሰው ጥናቱ፣ በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ ያልተሻሻለ (ባለበት የቀጠለ) ነው ተብሏል፡፡ በአገሪቱና በክልሉ መካከል ያለው የፆታ ዕድገት ሲተያይ በአማካይ 2.9 በመቶ ክፍተት (ልዩነት) እንዳለው ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ያለው የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ሲታይ፣ በተለይም የዜጎች ዕድገት መለኪያ በሆኑት አመለካከቶች አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ ድኅነትና የማኅበራዊ ኑሮ ደረጃ አለመመጣጠን ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፍ በሆነ መመዘኛው የኦሮሚያ ክልል የሚገኝበት ደረጃ ዜጎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው፣ ንፁህ ውኃ ለማግኘት ያላቸው ተደራሽነት አነስተኛ እንደሆነ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት መኖሩንም ያሳያል፡፡
በክልሉ ያለው የሥራ አጥ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ ከሆኑት ውስጥ የቡራዩ ከተማ ዋነኛው እንደሆነ፣ የዚህ አካባቢ የሥራ አጥነት ደረጃም 27.8 በመቶ መሆኑን አመላክቷል። በአጠቃላይ በኦሮሚያ ከተሞች ያለው የሥራአጥ ቁጥር ደግሞ በአማካይ 18.2 ከመቶ ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የጤና ዘርፉ ከፍተኛ መሻሻል የታየበት እንደሆነ ቁጥሮቹ አመላክተዋል፡፡ በአጠቃላይ የኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ ዕደግት እ.ኤ.አ ከ2012 አንስቶ ተከታታይ የሆነና ከሰባት በመቶ በላይ ጥቅል ዕድገት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ የተመዘገበው ዕድገት በግብርና ዘርፉ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ በዝናብ ላይ የተንጠለጠለውን የኢኮኖሚ ጥገኝነትን መቀነስ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
በዘርፎች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ ዕድገት ማስተካከል የሚገባ ሲሆን፣ ለአብነትም ከ15 በመቶ በታች ድርሻ ያለውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ መመልከት እንደሚገባ ያመለክታል፡፡
በትምህርት ዘርፉ ላይ የተገኙ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በትምህርት ጥራት ላይ መሠራት ይገባቸዋል የተባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቁና ተወዳዳሪ መምህራንን መቅጠር፣ የግሉ ዘርፍ በትምህርት ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፍ ማበረታታት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አሰናጅነት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረቡት ጥናቶችን መሠረት አድርጎ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
ከአማራ ክልል ልማትና ፕላን ቢሮ የመጡት አቶ አንሙት በለጠ በሰጡት አስተያየት በተለይም የሰብዓዊ ልማት ምዘና አስመልክቶ በተደረገው ጥናት ላይ ያለውን የመረጃ ጥራትና አስተዳደር (Data Quality and Management) ጠይቀዋል፡፡
በተለይም ትምህርትን የተመለከተ መረጃ ሲሰበሰብ በሚገኘው ጥሬ መረጃና በገጠርም ሆነ የከተማ አካባቢዎች ሲኬድ ያለው መረጃ ሲመሳከር ብዙ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ መኖሩን በማስታወስ ይህ እንዴት ይታያል? የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዜጎች ገቢ በተገናኘ ኦሮሚያ እያደገበት ያለውና የተገኘው አኃዝ እንደተጠቀሰ ሆኖ ክልሉ በድህነት ቅነሳ ላይ ያለው ተግባር (ኢንቨስትምንት) ምን ላይ ነው? ምልከታ ተደርጎበትም ከሆነ ቢገለፅ የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡
ከኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የመጡት ሰይፈዲን መሃሊ ኢትዮጵያ በጂዲፒ ልኬት በአፍሪካ ከሚገኙ አምስት ትልልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች መድረሷ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ወደ ኤችዲአይ ሲመጣ ያሉት ውጤቶች ዝቅተኛ እንደሆኑና በተለይም የዜጎች የኑሮ መሻሻል (Quality of life) እንዳለበት በመግልጽ እንዴት ነው ይህ ክፍተት መሸፈን ያለበት የሚለውንም አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ ፕላንና ልማት ኮሚሽነር አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በቀረበው የጥናት ውጤትና ውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የኦሮሚያ ልማት በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከኢኮኖሚክ አሶሴሽን ጋር በመሆን የተጠኑት ጥናቶች፣ የቀረቡት ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ውይይቱ በቀጣይ እንዴት የክልሉ ዕቅድ አካል አድርገው ይጠቀሟቸዋል የሚለውንም ለመመካከር ወርክሾፑ እንደተዘጋጀ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወሉ አብዱ በበኩላቸው፣ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግር ውስጥ ሆና የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት አገሮች አንዷ ሆናለች ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቁልፍ የኢኮኖሚ አመላካቾች በሚባሉት የዜጎች ዕድገት መለኪያዎች፣ ቁጠባ፣ ኢንቨስትመንት፣ ትምህርትና ጤና በመሳሰሉት ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው እንደሚገኝ አቶ አወሉ አክለው፣ በኢኮኖሚክስ አሶሴሽንስ አሁን ላይና ወደ ፊት የሚደረጉ ጥናቶችን በግብዓትነት ለመውሰድ ክልሉ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡