Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሕግ ማስከበር ራሱ ሕግ አለው እኮ!

ሕግ ማስከበር ራሱ ሕግ አለው እኮ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሕግ የማስከበር ሕግ አለ ብቻ ሳይሆን አምስት ዓመታት ያለፈው፣ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ደፋ ቀና እያለ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ የሚገኘው ለውጥና ሽግግር ዋና ዓላማ ወይም አደራ የሕግ ማስከበርን ሕግ በፀና መሠረት ላይ ማደላደልና ማቋቋም ነው ወይም እንደየሰው ምልክታ ‹‹ነበር››፡፡ ይህንን ጉዳይ ከሥር ከመሠረቱና በተቻለ መጠን በዝርዝር ለማስረዳት ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣን ለመንግሥት፣ መንግሥት ለተባለው ተቋም ብቻና ለብቻው የተከለለው ለሌላው ግን ጨርሶ የተከለከለው የጉልበት ወይም የኃይል ወይም የጉልበት ኃይል ብቸኛ የመንግሥት ባለቤትነትና ባለመብትነት አንዱ/ከፊሉ አካል ነው፡፡ የመንግሥት በኃይል፣ በጉልበት፣ በአመፅ መሣሪያዎች ላይ ያለው ብቸኛ የሞኖፖል መብትና ሥልጣን ማለት ትርጉምና ሚስጥር ይኼው ነው፡፡

ብዙዎቻችን፣ ከዚህ ይልቅ ስለኢኮኖሚው የአገራችን ሥርዓት ሕግ የደነገገውን፣ ወይም በተለያዩ ዘመናት ሕግ ሲደነግግ የኖረውን የግድና ይበልጥ የምናስታውስ ይመስለኛል፡፡ የሀብት ማፍሪያ መሣሪያዎችን ወደ መንግሥት (ብቸኛ) ባለቤትነት ለማዛወርና በቁጥጥር ሥር ለማድረግ አዋጅ ሲወጣ ያየንና የሰማን አሁንም በሕይወት አለን፡፡ የመኖሪያም ሆነ የሥራ ቦታ ሠርቶ ማከራየት፣ ለመንግሥት የተከለለ፣ ለግለሰብ ወይም ለሌላ ድርጅት/ቤተሰብ የተከለከለ ሥራ ሆኖ ለብዙ ጊዜ መቆየቱን የተረሳ ነገር አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የምርት መገልገያ ባለቤትነት (Means of Production) ሶሻሊስት ነው፣ ማለትም የመንግሥት ነው፣ የመንግሥት ብቻ ማለት እንደነበር ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ጭምር ነበሩ፡፡

አሁን የምንነጋገረው ኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ ስላለው የማምረቻ መሣሪያዎች ባለቤትነት አይደለም፡፡ ኃይልና ጉልበት፣ የነውጥ መሣሪያዎች (Means of Violence) ብቸኛ ባለቤትነት፣ እንዲሁም ሕግና ሥርዓት የአገርና የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም የማስከበርና የማረጋገጥ ሥልጣን የመንግሥት ብቻ ስለሆነበት አሁን የምንገኝበት ገሃዳዊው ዓለም ነው፡፡ ዛሬም ግሎባላይዜሽን የሚባል አዲስ ዕሳቤና ገሃድ ነገር ሉዓላዊነት ማለት ነገር ላይ ‹‹ማስተካከያ›› እና ‹‹ማሻሻያ›› ቢጤ ነገር ያዞ በተከሰተበት ዓለም ውስጥ የነውጥ/የኃይልና የጉልበት መሣሪያዎች ባለቤትነት ከራሱ ከሉዓላዊነት ህልውና ጋር የመንግሥትና የመንግሥት ብቻ ሆኖ ፀንቶ ቀጥሏል፡፡ ይህ፣ ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሰከንድ አመንድመንት የሚባል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለኝ ለምትል/ባላት በአሜሪካም ጭምር የሚሠራ እውነት ነው፡፡ ኃይልና ጉልበት የመጠቀም ሥልጣን የመንግሥት የሞኖፖል ሥልጣን ነው፡፡ መንግሥትነቱን፣ የመንግሥት ሥልጣኑን ራሱን ገፍፎ፣ ተገፍፎ፣ አውልቆ ጥሎ ሥልጣን አልባ ካልሆነ በስተቀር፣ ወይም መንግሥትነቱን ሳይማረክ፣ መንግሥትነቱን ሳያጣና የመንግሥት ሥልጣኑን ሳይሰለብ በዚህ ረገድ ያለውን የሞኖፖል መብት ከፍሎም፣ ቆርሶም፣ ቀንሶም አሳልፎ ሊሰጥ አይችልም፡፡

የነውጥ መሣሪያዎችን የመታጠቅ፣ ባለቤት የመሆን፣ ይህን ሁሉ ከምርቱ ጀምሮ ሁሉንምና ነቂስ ዝርዝር ጉዳዮችን ጭምር የመቆጣጠር ብቸኛ ሥልጣን ለመንግሥት የተሰጠው፣ ይህ ሥልጣን፣ ይህ ባለመብትነት ለመንግሥት ብቻ የተከለለ፣ ለሌላው ግን ፈጽሞ የተከለከለ የሆነው መንግሥት የዚህ ‹‹ልዩ ጥቅም›› አጣማጅ አቻ የሆነውን ሕግና ሥርዓት የሕዝብና የአገር ደኅንነትና ሰላም እንዲያረጋግጥ ነው፡፡ የዚህ የመንግሥት ልዩና ብቸኛ የሞኖፖል ሥልጣን መሸርሸርም ሆነ መድበስበስ፣ ከልክ በላይ መፍርጠምም ሆነ መጠበቂያና መቆጣጠሪያ ማጣት ደግሞ ሌላ መዘዝ ያመጣል፣ የጭቆና መሣሪያ ሆኖ ያርፋል፡፡ ይህን የመሰለ፣ በስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎና በዕቅድ ብቸኛ የሞኖፖል ሥልጣን የተሰጠው መንግሥት የታጠቀውን ኃይልና ጉልበት የታወቀው ዓይነት የጭቆና መሣሪያ እንዳያደርገው ግን፣ በአጠቃላይ መንግሥት ሕዝብን የሚፈራ፣ የሚያፍር በሕዝብ ዓይንና ጆሮ ቁጥጥር ሥር እንዲያድር የመንግሥት ዓምዶች፣ ከሁሉም በላይ ደግም የደኅንትና የመከላከያ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው መቋቋም፣ ከየትኛውም ፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ ሆነው መቋቋምና መደራጀት አለባቸው፡፡ ሕግ የማስከበር የመንግሥት ተግባር ራሱ ሕግ አለው ብለን የጀመርነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕግ ማስከበርን የመሰለ በሕግ መገዛት ያለበት ነገር የለም፡፡ ሕግ ማስከበርን ከሕግ ውጪ አድርጎ ሕግ አስከብራለሁ ማለትን የመሰለ የእንቧይ ካብ ጨዋታ የለም፡፡

እናም ሕግ ማስከበር ራሱ ሕግ አለው፣ በሕግ መገዛት አለበት ብዬ የጀመርኩትን ጉዳይ እንዳልኩትና እንደ ሞከርኩት በዝርዝርና ከተቻለም ከእነ ዝርዝር ነቂስ ጉዳዮቹ አኳያ ለማስረዳት መጀመርያ ‹‹የሕግ ማስከበር›› የሚባለውን ጉዳይ ተግባሮችና ኃላፊነቶች በአጭሩ ላመላክት፡፡ ዛሬ እዚህ የደረሰው፣ ሥልጣኔ ያካበተውና ያበለፀገው አሠራር ሕግ እንዲሁም መሠረታዊ መርህ፣ ወንጀልን መከላከልና ፈልፍሎ ማውጣት፣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ፣ እንዲሁም ለተቸገሩና ይህንኑ የግድ ለሚሹ ሰዎች ከለላና ድጋፍ መስጠት የሕግ ማስከበር ዋና ዋና ተግባቦትና ኃላፊነቶች መሆናቸውን ይበይናል፡፡ በኢትዮጵያም የአገሪቱ የወንጀል ሕጎች፣ የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና የ1997 የወንጀል ሕግ ሁለቱም በአንቀጽ አንድ ላይ የሕጉን ‹‹ጉዳይና ግብ›› ወይም ‹‹ዓላማና ግብ የሚደነግጉት በዚሁ መንፈስ ነው፡፡ ‹‹የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ግብ ስለጠቅላላው ጥቅም ሥርዓትን፣ ሰላምን፣ የመንግሥትንና የዜጎችን ፀጥታ መጠበቅና ማረጋገጥ ነው›› ይላል የ1949 ዓ.ም. ሕግ፡፡ የ1996 ዓ.ም. ሕግም ‹‹የወንጀል ሕግ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪቹን፣ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው›› ይላል፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስኩት ሥልጣኔ ራሱ አምጦ ወልዶ፣ አሳድጎና ኮትኩቶ እያበለፀገም እዚህ አሁን የደረስንበት ደረጃ ያደረሰው በጦርነት ሕግ፣ (የቀይ መስቀል ሕግ ጭምር በሚባለው) በሰብዓዊ መብቶች ሕግም የጎላና ከፍ ያለ ቦታ ባለው የዳበረ አሠራር መሠረት የሕግ ማስከበር ሥልጣን ወይም (LAW ENFORCE MENT POWERS የሚባሉት የሚከተሉት ሦስት ጉዳዮች መሆናቸውን ይዘረዝራል፡፡ አንደኛው ኃይል/ጉልበትና የጦር መሣሪያ (ፋየር አርምስ) የመጠቀም ሥልጣን፣ ሁለተኛው የመያዝና የማሰር ሥልጣን፣ ሦስተኛው ደግሞ የመፈተሽ/የመበርበርና ንብረት የመያዝ ተግባርና ሥልጣን ናቸው፡፡ እነዚህ ልዩ ልዩነታቸው በዝርዝርና ተለይተው የተመደቡት ሕግ የማስከበር ሥልጣኖች ተቋምም ሕግም አላቸው፡ ተቋሞችን ለማቋቋም፣ ለማደራጀት፣ የእነሱንም ሥራ አካሄድ ለመምራት፣ በየአጋጣሚና በዕድሜያችን ጭምር እንደተመሰከረው ደግሞ ‹‹አፍርሶ ለመገንባት፣ ቀድዶ ለመስፋት›› ወይም ‹‹አፍስሶ ለመልቀም›› በርካታ፣ ህልቆ መሳፍርት ሀብት ተከስክሶባቸዋል፡፡ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ተምረው፣ በሥራ ላይም በልምድ በልፅገው አገር ማገልገል በሚችሉበት ዋነኛውና አፍላ ሰዓት ድንገት ለውጥ ሲመጣ የሚራገፉ የተማሩ/ልምድ ያካበቱ ሰዎች ሥራ ፈቶች፣ ስደተኞች፣ በአጠቃላይ የአገር ኪሳራዎች የሆኑበት ጥፋትና ዕልቂት አከል ጉዳት ገና የአገር ‹‹ኦዲት›› አጀንዳ አልሆነም፡፡ አሁንም ያሉት ሕጎችና ተቋሞች ሲወጡም፣ ሲሻሻሉም፣ ሲሠሩምና እየሠሩ ናቸው ወይ ተብሎ ሲፈተሽ ዋና መነሻ ጥቄያችን ተቋሞቹ ገለልተኛ ሆነው ተቋቁመዋል ወይ? ከፓርቲ ወይም ከቡድን ፖለቲካ የፀዱ ሆነው የተቋቋሙ ናቸው? ሕጎቻቸውስ ይህንን ነፃነት እየተነፈሰ ይህ ነፃነት የፈቀደለትን ያህል እየተላወሰ ያደገና የበለፀገ ነው ወይ? ዋናው ችግራችን ይህ ነው፡፡

የብዙዎቹ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የሕግ ማስከበር ሥልጣኖች የመቆጣጠሪያ/የገደብ መነሻ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ስል አሁን ሥራ ላይ ያለው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ብቻ የሚመስላቸውና ስለእሱ እየተወራና በእሱ ላይ ስለተመሠረተ ነፃነትና መብት መስማት አንፈልግም የሚሉ ካሉ የሁሉንም የኢትዮጵያን ያለፉት ዘመናት በተለይም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀል ወዲህ ሕገ መንግሥቶችን የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎች ሁሉ መመልከት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ (ለማነፃፀር እንዲመቸንና የሁሉም ሕገ መንግሥቶች ግብ ይህ መሆኑን ለማሳየት) ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምዕራፍ ድንጋጌዎች የመግቢያ አንቀጾች እንጀምር፡፡ የአንቀጽ 15 የሕይወት መብት ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም ይላል፡፡ የዚህ ትርጉም፣ ለዚያውም የሞት ቅጣት ባለበት አገር እንኳን መንግሥት ዝም ብሎ አይገድልም፡፡ አንቀጽ 17 የነፃነት መብት ይደነግጋል፡፡ ማናቸውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ነፃነቱን/ነፃነቷን አያጡም ይላል፡፡ ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 እንዲሁም የተያዙ ሰዎች የአንቀጽ 19 ዝርዝር እንዲሁም የተከሰሱ ሰዎች መብት (አንቀጽ 20)፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት፣ ወዘተ ዝርዝርነትና የይዘታቸው ነቂስነት ጉዳይ ይህ ሰነድ ሕገ መንግሥት ነው ወይስ ‹‹የፖሊስ ማንዋል››? የሚያሰኝ ነው፡፡ እነዚህ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ (የአገር አስተዳደር ወይም የሰላም ወይም የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣው የፖሊስ የአሠራር ማኑዋል ሳይሆን) በሕገ መንግሥቱ በሰብዓዊ መብቶች ምዕራፍ ውስጥ የተመሸጉት የሥነ ሥርዓት ዋስትናዎችና መተማመኛ ድንጋጌዎች ዓላማና መነሻ የመንግሥትን የአሠራር ዘዴ/ሥልት፣ የሕግ ማስከበር ሥልጣንን የመገደብ፣ ልክና መልክ የማስያዝ ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡ ዜጋው ወይም ማንኛውም ሰው ለምሳሌ፣ ውሸት/ሐሰት ነው ብሎ የካደውን፣ የዚህ ሰው መብትና ነፃነትም የሚመሠረትበትን ፍሬ ነገር ወይም ቁምነገር መንግሥት የሚያገኝበትን፣ የሚያወጣበትን፣ ‹‹የሚያውጣጣበትን››፣ የሚያቀርብበትን፣ መንገድ የሚገድቡ፣ የሚከለክሉ ሕጎች ናቸው የሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ‹‹ምዕራፍ›› አካል ሆነው የኖሩት ከመስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ጀምሮ በፀናው ትዕዛዝ ቁጥር 6 መሠረት ነው፡፡ ‹‹የፌዴራል አዋጅና የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በእነዚህም መሠረት የታሰሩ የፌዴራል ሕጎች ሁሉ፣ እንዲሁም ደግም የንጉሠ ነገሥት መንግሥታችን የኢንተርናሽናል ውሎች ስምምነቶችና ግዴታዎች… በመላው በፌዴራል ንጉሠ ነገሥታችን ጠቅላላ የበላይ ሕግ ይሆናሉ›› ተብሎ ተደነገገ፡፡ በዚህ መሠረት ለምሳሌ ‹‹ንብረት የመያዝና የመልቀቅ መብት፣ ማንም ሰው ቢሆን ያለ ሕግና በሚገባ ዋጋ ሳይከፈለው ንብረቱን ወይም የኮንትራት መብቱን አያጣም፡፡››፣ ‹‹የመቆመውን ሕግ በመጣስ ወንጀል በመሥራት ላይ ካልተገኘ በቀር፣ ደንበኛ ባለሥልጣን ካላዘዘ ማንኛውም ሰው መያዝ ወይም መታሰር የለበትም፡፡›› የመሳሰሉት ‹‹የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች›› ድንጋጌዎች የአገር የበላይ ሕግ ሆነው ከእኛ ጋር አብረው የኖሩት (መኗኗሪያችን ባይሆኑም) ከ1945 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ እግረ መንገዴን አንድ ተጨማሪ ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ላክልበት፡፡ ብዙ ጊዜ ስለእነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲነሳ አብዛኛው ‹‹ክርክሩ›› መብቶች ፍፁም አይደሉም የሚል ‹‹አቋም›› መከራከሪያና መከላከያ ሆኖ ጎልቶ ይነሳል፡፡ ዋናው የክርክር ጭብጥ ግን መብቶችና ነፃነቶች ፍም ናቸው አይደሉም ሳይሆን፣ በመብቶችና በነፃነቶች ላይ ገደብ የሚጣለው ያለ ገደብ ነው ወይ? ማለትም በመብቶችና ነፃነቶች ላይ የሚጣለው ገደብ የለውም ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች የገደብ ድንጋጌ (ሊሚቴሽን ክሎዝ – Limitation Clause) የ1945 እና የ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች አሁንም ድረስ አምሳያ የሌላቸው ናቸው፡፡ የፌዴራል አክት የመስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ሕግ በአንቀጽ 7 (ተ) ‹‹… ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን መብቶች የሚወስኑ፣ የሌሎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና በጠቅላላውም ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል እንዲፈጸሙ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብቻ ናቸው›› የተሻሻለው የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ደግሞ በምዕራፍ ሦስት (ስለሕዝብ መብቶችና ተግባሮች›› ከአንቀጽ 37 – 65) ድንጋጌዎች ማሳረጊያ አንቀጹ፣ በአንቀጽ 65 ‹‹የሌሎችን ሰዎች ነፃነትና መብት ለማክበር፣ ደግሞም የሚያስፈልገውን የሕዝብ ፀጥታና ጠቅላላ ደኅንነት ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር በዚህ ምዕራፍ ከዚህ በላይ ባሉ አንቀጾች ውስጥ መተማመኛ የተሰጣቸው መብቶች በሌላ በማንኛውም ምክንያት አይቀነሱም፡፡›› ሲል ይደነግጋል፡፡ አሁንም ድረስ አምሳያ የሌላቸው ድንጋጌዎች ናቸው የሚለውን ቃሌን ደጋግሜ እያረጋገጥኩ አጣማጅ አቻ (ማለትም የተመጣጠኑና ትይዩ የሆነ) በዕውቀትም በብቃትም በሠለጠነ የሰው ኃይልና የተቋም ግንባታ፣ እንዲሁም ዘርዘር ባለ ሕግ መታገዝና መጠናከር አለባቸው፡፡

በተለይም ዴሞክራሲን መኗኗሪያ አደርጋለሁ፣ የዚህንም መሠረት አደላድላለሁ፣ የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ አድርጌ አቀርፃለሁ፣ የሕግ የበላይነትን (የመንግሥትን ለሕግ የመገዛትና በሕግ ሥር የማደር ልማድ) የአገር ባህል አድርጋለሁ ብሎ የተነሳ መንግሥት በሚመራው ለውጥና ሽግግር ውስጥ ሕገወጥነትን ለማሸነፍ የሚያደረገው ትግል የጥበብ መጀመርያው ይህ ራሱ በጥብቅ የሚከተሉት ሕግ ያለው መሆኑን ማወቅና ይህንንም መዘርጋት፣ ማስፈን፣ ማስረፅ ሕግ አስከባሪዎችን ሁሉ በዚህ ውስጥ የሚተዳደሩ ማድረግ ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ሕግ ከማክበር ይጀምራል፡፡ ሕግ የማክበርን የመንግሥት የሥልጣን አካላት ሥልጡንነት በተግባር ከማስመስከርና ከሕዝብ ጋር በሚደረግ በእያንዳንዱ ግንኙነት ከማረጋገጥ ይጀምራል፡፡ የአዋጁን በጆሮ ንገሩን ካልተባለ በቀር ከየትኛውም ሕግ በላይ ሕገ መንግሥቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ውስጥ በተለይም የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንቀጽ 9 (2) የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ድንጋጌ) ‹‹ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በሕግ አምላክ፣ ‹‹በሞቱ…››፣ ‹‹በ… ሞት›› እየተባለ የሚማፀኑት ምስኪኑና ሌላ አማራጭ የሌለው ተራ ዜጋ ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥት የሚባለውም ‹‹ሰው›› ነው፡፡ አሁንም የአዋጁን በጆሮ መንገር ካልሆነ በቀር በሕግ ‹‹የሰው መብት ስለተሰጣቸው…›› የሚደነግገው ዋናው መሠረታዊው የዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ከሌሎች መካከል ለምሳሌ፣ መንግሥትን ራሱን፣ የመንግሥት ግዛት ክፍሎችን፣ ሚኒስቴሮችም፣ የሕዝብ አስተዳደር ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩበትን አጠቃላይ የ‹‹ሥልጣኔ ደንብ ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ ‹‹መንግሥት በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው የሚቆጠር ነው›› እንዲህ እንደ መሆኑ መንግሥት በመሥሪያ ቤቶቹ አማካይነት ከተፈጥሮው ጋር የሚስማሙትን መብቶች ሁሉ ሊያገኝና ሊሠራባቸው ይችላል›› የመንግሥት የግዛት ክፍሎች ማለትም አሁን ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ የከተማና የገጠር ቀበሌዎችም እንዲሁ በሕግ ግዴታ ያለባቸውና መብት ያላቸው ናቸው፡፡ ሚኒስትሮቹም ‹‹የሕዝብ አስተዳደር ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶች››ም በሕግ ግዴታ ያለባቸውና መብት ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም በመሥሪያ ቤቶቻቸው አማካይነት በአስተዳደር ሕጎች የተፈቀዱት መብቶች ሁሉ ሊያገኙና ሊሠሩባቸው ይችላሉ›› ይህ መብትና ሥልጣን ግን መረን የለቀቀ አይደለም፡፡ የፍትሐ ብሔሩ ሕግ፣ በሕግ የሰው መብት ስለተሰጣቸው ስለመንግሥት፣ ወዘተ በሚወሰነው ክፍሉ (አንቀጽ/ቁጥር 394 – 403) በተለይ በቁጥር 401 ሕጋዊ ትዕዛዞችን ስላለመፈጸም ‹‹ጉድ›› ይደነግጋል፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ 1) ‹‹በሕገ የታወቀላቸው የተግባር ሥልጣን ከሚዘረጋበት ውጪ ወይም በሕጉ የተገደዱትን ሁኔታዎች ወይም ፎርም ባለመፈጸም በዚህ ምዕራፍ የተመለከቱት የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች የሚፈጽሟቸው ሥራዎች ፈራሾች ናቸው፡፡ 2) ‹‹እንደዚሁ ሕጉ በእነዚህ ምክንያቶች ሥራዎቹ ፈራሾች ናቸው ብሎ በግልጽ ባይናገርም ከዚህ በላይ እንደተነገረው ይሆናል፡፡›› ይላል፡፡ ይህን ፈራሽነት ማናቸውም ባለ ጉዳይ ሁሉ ሊጠይቅ ይችላል ሲል የሚደነግገው መሠረታዊው ሕግ ከውል ውጪ ስለሚደርስ ኃላፊነትም ያቋቁማል፡፡

እናም ዋናው ጉዳይ ሕግ የማክበር ግዴታ የሁሉም ‹‹ሰው›› ነው፡፡ የመንግሥትም፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትም፣ የባለሥልጣኖቻቸውም ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ለመንግሥትና ለመንግሥት የሥልጣን አካላት፣ እንዲሁም ለባለሥልጣኖቻቸው ‹‹ሥልጣናቸው›› መብታቸው (ፕሪቪሌጃቸው)፣ ሕግ ማክበር ግን ‹‹ምርጫቸው›› ወይም በፈቃዳቸው በቢሻን ውሳኔያቸው ወይም ምርጫቸው ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

በተለይ በተለይ ደግሞ ይህን በመሰለ በለውጥና በሽግግር ወቅት ከሁሉም በላይ ደግሞ የራሱ የመንግሥት ሕግ የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ብቃትና አቋም እንዲጠናከር ማገዝ፣ መተባበር ከሕዝብ በሚጠበቅበት ወቅት ሕገወጥነትን ለመግታት መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ የመንግሥትን፣ የመንግሥትን የሥልጣን አካላትና የመንግሥት ሠራተኞችን የገዛ ራሳቸውን የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ ሲያስገምትና ዘጭ አድርጎ ሲጥል መታየት የለበትም፡፡ እርግጥ ነው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዕዳችን ሆኖ የመንግሥት፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላት ለሕግ የመገዛት፣ ለሕግ የመታዘዝ ልምድ ገና ጥሬ ነው፣ ገና ቢከፍቱት ተልባ ነው፡፡ ይህ ግን እየተጋለጠና እየተሳጣ፣ እየተወገዘና እየተኮነነ መፍትሔና ዕርማት ማግኘት እንጂ እየተድበሰበሰ በአረም መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት ላይ የተሰባሰበውን፣ በስንት መከራ የተገኘውን/ተገኝቶ የነበረውን ደጋፍ መብትን ለዴሞክራሲ የሚያደረገውን ዋናውን ትግልም ማቁሰል የለበትም፡፡

የአገራችን የፖለቲካ ሰላም ዋና ፈተና የተለያዩ ኃይሎች፣ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (2) ውስጥ የተዘረዘሩት ኃይሎች ግንኙነት (ዜጎች መንግሥት ከአካላቱ ፓርቲዎች፣ ወዘተ) የእነዚህ ግንኙነትና ትግል ከሰላማዊና ከሕጋዊው መንገድ ወይም መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ አለመታጠሩ፣ አለመገደቡ ነው፡፡ እዚያ ሰላማዊና ሕጋዊ ግቢ ውስጥ አልገናኝም፣ አልሰበሰብም ማለቱ ነው፡፡ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኃይሎች ትግል እንዲህ ያለ ለሕግና ለሥርዓት፣ ለዴሞክሲና ለተቋም ግንባታ አስቸጋሪ በሚሆንት ወቅት በጉልበት፣ በሸፍጥ፣ በሴራና በመሠሪ መንገድ ሁሉ መዋደቅ፣ ትግል ነኝ ባለበት ሁኔታ የመንግሥት ሕግ የማስከበር አቅም ብቻ ሳይሆን ሕጋዊውን፣ ሰላማዊውን መንገድ ብቻ ተመራጭ የማድረግ ሕጋዊውን አሠራር የመንግሥት አቅምና ፈቃደኝነት ከሁሉም በላይ ግን ግንዛቤ ይበልጥ መጠናከር አለበት፡፡ መንግሥት ወደ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ቢጣራ የሚሰማው፣ ጥሪውም እየተሰማ ይህ መንገድ እየለማ የሚመጣው መንግሥት ራሱ ከእነ ሲቪልና ወታደራዊ ቢሮክራሲው (ቢሮክራሲውን ከገነቡ ሠራተኞች ጭምር) በዋነኛነት ሕግን በመጣስ የማይታሙ፣ ቢያንስ ቢያንስ ይህ አጠቃላይና ወሳኝ ባህሪያቸው ሲሆን ነው፡፡

አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ግን ከዚህ እጅግ በጣም ብዙ የራቀ ነው፡፡ በየግልና በየፊናችን የሚያጋጥመን አመዛኑ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር የምናደርገው ‹‹ግጥጥም›› ወይም ግንኙነት (ኢንካውንተር) የሚመሰክረው ነው፡፡ አልፎ አልፎም እያበረከቱ የመጡ የተረጋገጡ (የፈጠራ ሳይሆን ትክክለኛነታቸው የሚያጠራጥር) የሶሻል ሚዲያ (መንገደኛ ግለሰብ የቀለባቸው የፖሊስ ምግባር) ቪዲዮዎች የሚናገሩት ሕግ አስከባሪቻቸውን (ደንብ አስከባሪዎቻቸውን) ከልካይ የሌለባቸው የሚፈሩት ሕግ ቀርቶ የሚፈሩት መለኮታዊ ኃይል እንኳን የሌለ መሆኑን ነው፡፡

ይህን የመሳሰለውን ሁሉ ዝም ብለን የመንግሥት፣ የመንግሥት አካላትና የባለሥልጣኖቻቸውና የሕግ አክባሪ/ደንብ አስከባሪ ግለሰቦች ለሕግ የመገዛት ልምድ ገና ጥሬ ነው የሚል ምክንያት ብቻ የሚያብራራው አይደለም፡፡ ለበጎ ውጤት ተብሎም፣ ይጠቅመናል ብሎም ለ‹‹ድርጅት›› ሲባልም፣ ወይም ‹‹ድርጅትን ከአደጋ ለማዳን›› እየተባለም የገዛ ራስን ውሳኔ መሻር፣ ሕግንና ዴሞክራሲያዊ አሠራርን መጣስና አሽቀንጥሮ መጣል አለ፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን በግልጽና በአደባባይ በይፋና ሕዝብ እያየው፣ ፀሐይ እየሞቀው ድርጅትን ለማዳን መንግሥታዊ ሥልጣንን ተጠቅሞ የድርጅት ሕገ ደንብ ሲጣስ ያየነው ‹‹ግንቦት 20 አሥረኛው ዓመት›› ውስጥ ነው፡፡ ይህ ራሱ አድነዋለሁ በተባለው በድርጅት ላይ፣ በዚያ ብቻ ሳይወሰን በመንግሥትና በአገር ላይ ጥፋት መፈጸም ነው፡፡  

ዛሬም ተመሳሳይ ሥራ/ደንታ ቢስ ግዴለሽነት እየተካሄደ ነው፡፡ በሕግ ያልተቋቋመ ከተማ ሕግ ለማስከበር የሚደረገው የዕውር ድንብር ጉዞ መሳቂያ እያደረገን ነው፡፡ የበጀት ሕግ የሚባል ነገር ስለመኖሩ ድንገት ብንን ብሎ፣ ደንገጥ ብሎ የሚያስታውስ የለም፡፡ ገንዘብ የሚሰበስበው ብቻ ሳይሆን የሚወጣው በሕግ ለተወሰነ ወጪ ስለመሆኑ ገና አልተገለጸልንም፡፡ በሕግ አምላክ ስንል ከሁሉም በላይ መንግሥትን፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትንና ባለሥልጣኖቻቸውን መሆኑን ልብ አድርጉልኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...