በዘሪሁን አድነው ጽጌ
ምሁርነት ከማዕረግ ባሻገር በጥልቅ ዕውቀት የተገነባ፣ በምክንያታዊነትና በማስረጃ ላይ የተደገፈና የማማከርም ሆነ አቋም የመያዝ የልህቀት ደረጃ ነው፡፡ አንድ ምሁር ባሳለፋቸው የትምህርት ሒደቶች ከሙያ ባለቤትነት ባሻገር፣ ማንኛውም የተማረ አካል ሊጋራቸው የሚገቡ የጋራ መለያዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ እነሱም ምክንያታዊነት፣ መረጃ ላይ መመሥረት፣ ከሌላው ማኅበረሰብ በላቀ ማሰብና ማሰላሰል፣ ለሌሎች የሕይወት ለውጥ እንደ ሞተር ማገልገል፣ በምክንያታዊነት የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስ፣ ከጠልነትና ከፍረጃ በራቀ የማስተማርና የመማማር ዕድል መፍጠር፣ እንዲሁም ከሌብነትና ከቁስ አፍቃሪነት በራቀ በላብ የመኖር ምሳሌነት በመፍጠር ማኅበረሰብን የመቅረፅ ኃላፊነትን መወጣት ናቸው፡፡
ምሁራዊነት ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ከሰብዓዊነት ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም ዕውቀት፣ በነፃነት ማሰብ፣ የዕውቀት ሽግግርና መጋራት፣ አንድ ወጥ የዕውቀት የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና በእውነታ ላይ መቆም፣ ለጋራ ጥቅም ዕውቀትን መጠቀምና የተሻለ ዓለም መፍጠርና የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የዕውቀት ውጤቶችን መገበያየት፣ ዕውቀትን መለካትና ማረጋገጥ ሰው ከመሆን ከተፈጥሮ ጋር በሚኖር መስተጋብር የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ዕውቀት በሃይማኖት/እምነት፣ በዘር፣ በቀለም፣ በሥነ ምኅዳር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በግል ፍላጎት የሚፈረጅና ለተወሰነ ዓላማ እንዲውል የሚደረግ ከሆነ ዕውቀትነቱ ያበቃለት፣ እውነትነቱ ያልተረጋገጠለት፣ ውጤቱም የማይታወቅ አፍራሽ ሆኖ መቅረቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ዕይታ መሠረት የኢትዮጵያ የምሁራዊነት ሒደትን ማየት ተገቢና የመነሻዬ መዳረሻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ የዕውቀት ሽግግርና የከፍተኛ ትምህርት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ከመጠንሰሱ በፊት ኢትዮጵያ የራሷ የዕውቀት መነሻና መድረሻ፣ መስፈሪያና ማብቂያ ሥርዓት ያላት አገር ስለመሆኗ አያጠራጥርም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ የዚህ የዕውቅ መነሻ ከአንድ ብሔርና ሰሜናዊነት ጋርና እምነት ጋር ለማያያዝ የተሄደበት መንገድ ከፍተኛውን ውድቀት እንድንቀበል አስገድዷል፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን ወደ ኢትዮጵያ ስናስገባ እንዴት ማስገባት እንዳለብን ስትራቴጂ መቅረፅ ባለመቻላችን የራሳችንን ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር እንዴት ማጣመር እንደሚቻል፣ ዘመናዊ ትምህርትም ከኋላው የተሸከመውን ዕዳና የሌሎች ፍለጎቶችን ለመቆጣጠር እንደሚቻል ሳናስብበት፣ በኢትዮጵያ ነባር ዕውቀቶች ላይ እንደ አረም በመበተናችን እውነተኛውን ማንነታቸንን አቀጭጮ የምዕራብዊያን አድናቂ ከማድረጉ ባሻገር፣ አጠቃላይ አገረ መንግሥቱንና ታሪካችንን አደጋ ውስጥ ለመክተት ምክንያት ሀኗል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ ፊደልና የጽሕፈት ሕግጋትና ሥርዓት ያላት፣ ድምፅን በቃላት፣ ቃላትን በጽሑፍ መግለጽ የሚችል የቋንቋ ምዕሉነት ያላት አገር እንደሆነች ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ፊደላትን ከማስቆጠር እስከ ላይኛው የዕውቀት እርከን በሥርዓት የምትመራበት ሥርዓተ ትምህርት የነበራት አገር ናት፡፡ በአገር በቀል ዕውቀት ረገድ ከአገር በቀል ሥልተ ምርት፣ የአነስተኛ መሣሪያዎች ማምረት፣ የዕፅዋት ቅመማን ለተለያዩ ግልጋሎት ማዋል የሚያስችል፣ የሕግና የማኅበረሰብ አስተዳደር (እንደ ገዳ ሥርዓት፣ ጉማ፣ የበልሃ ልበለሃ ፍትሕ፣ ደቦ)፣ የሥርዓተ ምግብ፣ አልባሳት፣ የመጠጦች፣ የግንባታ ዕውቀቶች የነበራትና ያላት አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ብሔርና እምነት የሚገለጽ ሳይሆን፣ ከብዝኃ ማንነታችን የመነጨ የማኅበራዊ ግንኙነታችን ትስስር ጋር የተዛመደ የዕውቅት ቅብብሎሽ መጋራትን ያስተናገደ ነው፡፡
ይሁንና ዘመናዊ ትምህርት ያለበትን ችግር ቀርፈን መቀበል ባለመቻላችን እንደ አረም የእጃችንን አጥፍቶ ራሱ በላይችን ላይ ነግሦ መነሻና መዳረሻ አልባ ከማድረጉ ባሻገር፣ በነባሩንና ለሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ለቀጣይ ችግሮቻችን መንስዔ ለመሆን የበቃ ይመስላል፡፡ ይህን ስል በአጠቃላይ የዘመናዊ ትምህርትን ለመውቀስና በዚያ ያለፉ ሁሉ ችግር ናቸው የሚል ድምዳሜ ሊኖረኝ እንደማይችል ዕሙን ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደራጃ አንቱ የተባሉ፣ ለዓለም ችግር መፍትሔ የሆኑ፣ ለአገራቸው ደግሞ ክብርን ያጎናጸፉ ምሁራንን መዘርዘር በዚህ አጭር ጽሑፍ አዳጋች ነው፡፡ ይሁንና ከማዕረግ መገለጫቸው ባሻገር ዕውቀት ሊያስገኘው የሚገባውን የሰብዕና ልዕልና መጎናፀፍ ያቃታቸው፣ ይባስ ብለው ለአገር ጠር የሆኑ ምሁራን ናቸው ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑኝ፡፡
ወደድንም ጠላንም አገራችን አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች፡፡ አገራችን ችግር ላይ መውደቅ ብርቋ ባይሆንም፣ በሒደት ችግሮች መፍትሔ አጥተው እየተንካባለሉ መምጣታቸው፣ የውጭ ሴራና የውስጥ ከትናንት መማር አለመቻል፣ እንዲሁም መሸጦነት ችግሮችን መፍትሔ አልባ አድርጓቸዋል፡፡ ዕውቀት የኖረውም ያስፈለገውም ችግር በመኖሩ ነው፡፡ ብዙ ችግር ባለበት ቦታ ብዙ ዕውቀት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ልዩነቱ ችግሩን ተረድቶ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ሐሳብ የሚያመነጭ የዕውቀት ቀንድ ከራሳችን ማንነትና ዘይቤዎች ጋር አዋህዶ፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር መፍትሔ ለመስጠት አለመቻል ነው፡፡
ለመሆኑ እንዴት ችግር የሚፈታ ዕውቀትና አዋቂ ከኢትዮጵያ ምድር ጠፋ? በእውነት የትኛው ነው የሌለው ዕውቀት ወይስ አዋቂ የሚለው በግልጽ መለይት አለበት፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባለዲግሪዎች፣ ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮችና ጸሐፍት ተወልደው፣ አድገው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከችግር ወደ ችግር እየተሻገረች የግዛት አንድነቷ ተሸርሽሮ፣ የሕዝቦች መስተጋብር ተንዶ፣ እናንተና እኛ ሰፍኖ፣ በብሔርና በተለያዩ መለያየቶች ውስጥ ተዘፍቀን፣ አገራዊ ህልውናችን ላይ ከፍተኛ አደጋ ተገትሯል፡፡
ይህንን ሁሉ መንደርደሪያ ማቅረቤ ምሁርነት ምን ማለት እንደሆነ፣ ምን እንደሚጠበቅበትና የት ቦታ መቆም እንዳለበት ለማስረዳት አንዲረዳኝ ነው፡፡ ከዕውቀት ምንጭ ፍለጋ እስከ ችግር ጋጋታ፣ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታና የችግር ፈቺ ምሁራን ሚናን ከማሳየት አንፃር ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከዕውቀትና አዋቂ ውጪ ፈጽሞ መዳኛ መንገድ የላትም፡፡ በጦርነትና በኃይል የሚፈታ ጉዳይ በኃይልና በጦርነት የሚመጣን ኃይል ይወልዳል እንጂ፣ ለኢትዮጵያ የሚፈይደው ምንም ዓይነት መፍትሔ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ትክክለኛ ጦርነቶች ካሉ የድንበርና የግዛት ማስጠበቅ፣ የዘመነ መሣፍንትና የነፃነታችን አለት የሆነው ዓድዋ ጦርነት ብቻ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ የተካሄዱ ጦርነቶች እየተካሄዱ ያሉትም ከአላዋቂነትና ከዳፍንትነት በመነጩ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከየራስ ገዝ ተልዕኮ ወጥተው አገርን ከጠላት የመከላከል ባለራዕይነት፣ ምክንያታዊነትና የዕውቀት ባለቤትነት (ዓድዋ ላይ ከሁሉም ብሔር በሔረሰቦች የተውጣጣውን ኃይል ይወክላል) ካሳዩን ቀደምት አባቶቻችን ተገልብጠን፣ እርስ በእርስ መዋጋትና እስከ መለያየት የደረስንበት የዕውቀት አልባነት በትናንቱ የኢትዮጵያ ዕውቀትና በዛሬው ዘመናዊነት መካከል ያለውን የተልዕኮ ልዩነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ አሁን ምሁራኖቻችን እነማን ናቸው? የት ናቸው? ምን እያደረጉ ነው? ይህ ሁሉ መዓት ሲወርድብን መፍትሔ እንዴት አጠራቸው? የሚለውን ጉዳይ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ምሁርነት አላዋቂዎችን ከመፈረጅ ወጥቶ በቅቶ ማብቃት ሲጠበቅበት፣ የዘመናዊ አባቱን አፄ ኃይለ ሥላሴን በአላዋቂነት ፈርጆና ወላጁን ገድሎ፣ ራሱም በደርግ የታጨደው የምሁርነት መርህ ተምሮ ማስተማርና የመለወጥ መርህ በማፈንገጡ ነው፡፡ ደርግ ለትምህርት የሰጠውን ትኩረት ያህል አዋቂ፣ ጠያቂና ምክንያታዊነትንና መበለጥን ጠል በመሆኑ በርካታ ምሁራንን ፈጅቷል፡፡ በዘላቂነት የምሁራዊነት ተፅዕኖንም በከባድ ገድሎት አልፏል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ምሁርነት በአፍጢሙ ተደፍቶ ወደ አድርባይነት ወርዶ ወደ ሥርዓት አገልጋይነት በመለወጡ፣ መሠረታዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ማምጣት አልተቻለም፡፡
ከዩኒቨርሲቲ የሸፈቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎችም ጥለውት የሄዱትን ትምህርት ከመቀጠል፣ ተምሮ የጠበቃቸውን ምሁር መግደልና ማሳደድ፣ እንዲሁም ሥርዓት አፍቃሪ ምሁር ወልደው ትምህርትን ከካባ ባሻገር ፋይዳ እንዳይኖረው አድርገውት፣ ምክርንም ሆነ መካሪን በማጣት በራሳቸው ላይ ሞትን አውጀው አስተማርነው ያሉትንም ትውልድ የጥይት ራት አድርገው፣ የዲግሪ ካባ የገዙበትን ገንዘብ ለለገሷቸው የትምህር ተቋማት ሳይከፍሉ ከሥልጣን ተወገዱ፡፡ በነገራችን ላይ ሕወሓት ከሥልጣን የተወገደውም፣ ከተወገደም በኋላ ከጥይት ውጪ መፍትሔ ማፍለቅ ያልቻለው በዕውቀት ላይ በወሰደው አጥፍቶ የመጥፋት ዕርምጃ ነው፡፡ ሕወሓቶች በዕውቀት ረጋ ብለው ለመፍታትና ለመመካከር ዕድል ሰጥተው ቢሆን ከዚህ የተሻለ ዕድል መፍጠር ይችሉ ነበር፡፡
በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ብልፅግና በወጣቶች አመፅና በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዕውቀት ጠልነት በተገኘች የኃይል መዛባት ፍንዳታ ውጤት በመሆኑ፣ እሱም እንደ ቀደምቶቹ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቅርፅ ለመያዝና በዕውቀትና በእውነት ላይ ከመቆም ይልቅ ቁርሾ ላይ የቆመ፣ ፍረጃ ላይ የተወሰነ ማግለል፣ በአምልኮ ትርክት ላይ በመቸንከሩ ሕወሓት ከወደቀበት የተሻለ መነሳትን መማር አልቻልም፡፡ የመረጠው ወደ ነገ የሚያሻግር ዕውቀትን ሳይሆን፣ ወደኋላ የመለሰ የተሳሳተ የሕወሓት ብሔር ወለድ ትርክትን ነው፡፡ በመሆኑም ብልፅግና ጥርት ያለ በእውነትና በዕውቀት መነሻ ላይ ተመሥርቶ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የጣለውን ጥቀርሻ ለመፋቅና አዲስ ሐሳባዊ ርዕዮት ለመውለድ አልቻልም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚወሰደው ለውጡ ድንገተኛ መሆኑ፣ ሕወሓት የደቀነው ሥጋት ተረጋግቶ ለመሥራት አለማስቻሉ፣ በውስጡ ለውጡ ላይ ሳይሆን ትናንት ላይ የተቸነከሩ አካላት መብዛት፣ የረቀቀ እውነት ላይ የተመሠረተ ትንተናዊ ፖለቲካዊ ዓውድ ላይ ከመመሥረት ይልቅ ስሜታዊ የኦሮ-ማራ ጥምረትን መሻገር አለመቻል ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ትልቅ ሚና ሊኖረውና ተረጋግቶ ለፖለቲከኞች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፈጣን ትንተና እየሰጠ የኋላውንም ሆነ የወደፊቱን ማሳየት የነበረበት የምሁሩ ሚና ዝቀጠኛና ወደ መሸጦነት የተቀየረ መሆኑ ችግሩን ለመቀልበስ አልተቻለም፡፡
ሕወሓት ኢሕአዴግ በሟሟያ ትምህርት፣ በብሔርና በፖለቲካ ተዋጽኦ ከዲግሪ እስከ ፕሮፌሰርነት ያከናነበው ዕውቀት በአግባቡ ያልዘለቀው ምሁር አይደለም ችግር ሊፈታ፣ በትናንትናው ላይ የፖለቲካ አድርባይነቱና የብሔር ጥላቸው ላይ እምነት/ሃይማኖትን አክሎበት አደገኛ የሥልጣንና ሀብት ማካበት ሴራ ውስጥ በመዘፈቁ አይደለም የአገር ችግር ሊፈታና አቅጣጫ ሊያሳይ ቀርቶ ራሱ ችግር ለመሆን በቅቷል፡፡ የብልፅግናን ፖለቲካዊ ዕሳቤ ከብልፅግና ወንጌል ጋር በማያያዝ ተቋማትንና ሥልጣን የሚያሳድደው ይህ አካል የለበሰውን ጋዋን ያህል ዋጋ ማውጣት የማይችል ስንኩል ነው፡፡ በሆቴል መስተንግዶ፣ በሥልጣን አንጋጦ፣ በሌብነትና በሴሰኝነት፣ እንዲሁም በክፋትና በተንኮል ተጠምዶ የመማርን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አፈር ድሜ አስግጦታል፡፡
ይህን ምሁር የትም ታገኘዋለህ፡፡ በዩኒቨርሰቲ ውስጥ ያስተምራል፣ በተቋም ውስጥ ያማክራል፣ በሆቴል ቡፌ ያደምቃል፣ በአጥቢያዎች ይሰብካል፣ በብሔር ሚዲያዎች ላይ ጥላቻን ይነዛል፣ በመሬት ላይ ሀብት ያጋብሳል፡፡ ይህ ምሁር የተማሪውም ውጤትን በእምነት፣ በፆታዊ ትንኮሳ፣ በእምነት ካባ እስከ መስጠት፣ በጥላቻ የመንግሥት ሥልጣን እስከመያዝ፣ በማማከር ስም መርዝ የሚጠምቅ፣ በጨለምተኝነት ትናንት ላይ ቆሞ ሙት የሚወቅስ፣ በሥሩ ያሉ የፖለቲካ ደቀ መዛሙርቱን ጥላቻ የሚጠምቅ ነው፡፡ ይህ አካል ፈጽሞ በእውነትና በዕውቀት ላይ የተፈተነ ከማንኛውም ተራ ዜጋና ፖለቲከኛ ለዚች አገር ከፍተኛ ሥጋት ሆኖ መጥቷል፡፡ በዚህ አካል የዕውቀት ተቋማት ፍዳቸውን እያዩ ሲሆን የነገውን ትውልድ ደግሞ ከስንዴው ይልቅ ገለባውን እያሸከሙት ይገኛል፡፡
በተለይ ሥልጣን በእምነት/ሃይማኖት ለመያዝ የሚደረገው አደገኛ አካሄድ ከወዲሁ ካልተገታ ትናንትን የወቀስንበትን የጊዜ ዕድል ማግኘት አንችልም፡፡ የትኛውም እምነት/ሃይማኖት መጥፎ አይደለም፡፡ ሆኖም በየትኛውም እምነት/ሃይማኖት መጥፎ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ስለመኖሩ ምንም የሚያሻማ አይደለም፡፡ ሆኖም እምነትን ለፖለቲካ ተረኝነት ለመግለጽ ከተወደደ ግን ምንም ዓይነት እውነትም ሆነ መፍትሔ ሊኖረው አይችልም፡፡ ዛሬ ዛሬ የምናየው የብልፅግና ርዕዮተ ዓለምን ከብልፅግና ወንጌል፣ የብልፅግና ወንጌልን ከፕሮቴስታንት ጋር በማያያዝ ለመላላጥ የሚደረገው አካሄድ አገርን በከፍተኛ አደጋ ይጥላታል፡፡ ይህ አካል ዓላማው ሃይማኖትን/እምነትን ማራመድ አይደለም፡፡ ዓላማው በአጋጣሚ የአገሪቱ የፖለቲካ ዝውውር በከፈተለት ገበያ ውስጥ ሥልጣንን፣ ሀብትንና በቀልን መወጣት ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ያሉ እምነቶች በታሪክና በፖለቲካ በመፈረጅ ተረኛ ሆኖ ለመቅረብ የሚያደርገው መላላጥ ለፖለቲካውም፣ ለራሳቸውም፣ አገርንም ከችግር ለማውጣት ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ አይኖረውም፡፡
ይህ ምሁር አንድና አንድ ዓላማው በገበያው ውስጥ ባላው አቅም (የሃይማኖትና የብሔር ገበያ) ራሱን በማስገባት፣ በሥልጣንና በሀብት ማማ ላይ በመውጣት ድህነቱን መሻር፣ የበታችነቱን ማደስ፣ የትናንቱን ቂም በመወጣት የፈረጃቸውን አካላት መጉዳት፣ ዕውቀትና ትምህርትን ባገኘው አጋጣሚ ስያሜ መደፍጠጥ ጠቃሚ ዜጎችን ያንኮታኩታል፣ በአጠቃላይ ዕውቀትና እውነት ፈጽሞ የለውም፡፡
አንድ አገር ቀደም ሲል እንዳልኩት ከዕውቀት፣ ከእውነት፣ ከጋራ ራዕይ፣ በምክንያት ከመደማመጥ፣ ከጋራ ተጠቃሚነት፣ ከታሪክና ከወደፊት የጋራ እሴት ባለቤትነት ውጪ ምንም መፍትሔ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሁሌ ሊያስጨንቀን ከተገባ ነገ እንጂ ትናንትንም በደስታም ሆነ በሐዘን አልፈነዋል፡፡ ዕውቀት እዚህ ላይ ነው ከትናንት ተሞክሮ፣ ከነገ ፍላጎት ጋር አጣጥሞ በምሁራዊ ትንተና መጪውን ለመገንባት መዋል ያለበት፣ ይሁንና ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ካለመታዳሏ ባሻገር ነገዋ በከፍተኛ ዕውቀት አልባነት፣ መፍትሔ ዕጦት ውስጥ ወድቃለች፡፡
ምሁራዊ ሴራ በምን ይገለጻል?
ሥልጣንና ተቋማትን መቆጣጠር ለእሱ የሥልጣን ትንሽና ትልቅ የለውም፡፡ ለማንኛውም ቦታ ራሱን ዕጩ አድርጎ ከመቅረብ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ተቋማትን ይገለገልባቸዋል እንጂ ፈጽሞ አያገለግላቸውም፡፡ ምናልባትም ሊያፈርሳቸው ይችላል፡፡ ተቋማቱን ይዞ ወደ ላይ ያንጋጥጣል እንጂ ዝቅ ብሎ ሕዝብን ለማገልገል ፈጽሞ ምንም ዓይነት ፍላጎት የለውም፡፡
ሀብት ማጋበስና ሙስና ላይ መሳተፍ ፈጽሞ የሚያውቀውን ድህነት፣ ትናንት ያጣውን ዕድል ለማካካስ ገንዘብ ያለበትን ከማነፍነፍና ያልተገባ ጥቅሙን ከማጋበስ አይቆጠብም፡፡ ምናልባትም ከፖለቲካ ካድሬዎች በባሰ ሙስናን እንደ እምነት የተቀበለ ነው፡፡ ምናልባት ሌብነቱን ሕጋዊ ለማድረግ ሥልት ሊጠቀም ይችላል፡፡ ሆኖም ይህም የተወሳሰበ ባለመሆኑ ለማግኘት አስቻጋሪ አይደለም፡፡ በሰበብና በአስባብ ከአንዱ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም በማዘዋወር ሕጋዊ ለማስመሰል ይጥራል፣ ተቋማዊ ኔትወርክ በመሥራት ይቀባበላል፡፡ ስሙ ላይ መንጠልጠል ይወዳል፡፡ በእርግጥ አሁን ትምህርትና ምሁርነት በረከሱበት ዘመን ምሁርነት ወንዝ የሚያሻግር ባይሆንም፣ ነገር ግን አሁንም ያለውን የትምህርት ካባ ለመሸሸጊያነት ይጠቀምበታል፣ በተግባር ግን ፈጽሞ አይገኝም፡፡
እምነትን ያላግባብ መጠቀም በዙሪያው ቡድን ለማደራጀትና የጥቅም ትስስር ለመፍጠር እንዲችል በእምነት የሚመስሉትን ይሰበስባል፣ ዕድል ይሰጣል፣ ሌሎችን ደግሞ በማግለል በአገሪቱና በሥርዓቱ ላይ አኩራፊና ተስፋ ቢስ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግም በአብዛኛው የሚከናወነው የፕሮቴስታንት አማኝ ነን የሚሉ የፖለቲካ ሴረኞች ነው፡፡ ይህም ያልተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት ከመፍጠሩ ባሻገር፣ አገረ መንግሥቱ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል፡፡ ፖለቲከኞችን ይፈራል ያከብራል ትንሽም ሆኑ ትልቅ ፖለቲከኖች ለእሱ የሥልጣን ጥም ሲል ይጠቀምባቸዋል፡፡ ፈጽሞ የተሳሳተ ሐሳብ ቢይዙ እሱ ራሱ ሐሳባቸውን ይገዛቸዋል እንጂ፣ ፈጽሞ ተሳስታችኋል ብሎ በምሁራዊ ትንተና ለመሞገት አይወድም፡፡ ምናልባትም አሁን መንግሥት የገጠመው ፈተና ይኼ ነው፡፡ መንግሥትን በዕውቀታዊ ሒስ ከመሞገትና መጪውን በማሳየት ከጥፋት ከመመለስ ይልቅ፣ ግፋ እያለ ለጥፋት ያዘጋጀዋል፡፡ ብልጣብልጥነት ማብዛት ፈጽሞ ከእሱ በላይ አዋቂ፣ ሴራ ተንታኝ፣ ለአገሪቱ የሚለፋ፣ ትልልቅ አስተዋጽኦዎች ያደረገ አካል ያለ አይመስለውም፡፡ እናም ትውልዱ ዕድሉን እንዲጠቀም ሳይሆን እሱ በትውልዱ ዕድልና ዘመን ላይ ባለቤት መሆን ይቃጣዋል፡፡
ፆታዊ ግንኙነትን ላልተፈለገ ዓላማ መጠቀም፣ የፆታ እኩልነትን በመቀበል ስም ፆታዊ ሥልቶችን ሌሎችን ማጥቂያና ፍላጎታቸው ማሳኪያነት ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ አካላት ባሉበት ተቋም የአንድ ፆታ የበላይነት ይታያል፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሠራተኛ ሽሽት ቢኖርም የተወሰኑ ለእነሱ የሚጠቅሙ ብቻ ባሉበት የማይነቀነቁ ሰዎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ፈጽሞ ብቃትና ንቃት ያላቸው ሠራተኞች በተቋም ውስጥ ማግኘት አይቻልም፣ ሕዝበኝነትን መሻት በመንግሥትና ሌሎች ታዋቂ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ፣ ተንታኝና አዋቂ በመምስል ራሳቸውን ለሥልጣን ያጫሉ፣ ቀልብ ለመሳብ ይጠቀማሉ፡፡ ይህንንም ለማሳካት የሚዲያ ባለሙያዎችን በጥቅም ሰንሰለት በማሰር ረዥም ጉዞ ይሄዳሉ፡፡ በዕውቀት፣ በተክለ ሰብዕና፣ በተቀባይነት ከእነሱ የላቀን ሰው ፈጽሞ አይቀበሉም፡፡ ካሉም ያስወግዳሉ፡፡ ሰበብ አስባብ ፈልገው በሥራቸው ጠንካራ ናቸው ተብለው የሚታመኑ ባለሙያዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና የመስመር መሪዎችን በፍረጃ ከሥራቸው ያባርራሉ፡፡
መውጫ
በአጠቃላይ ምሁራዊ ዝቅጠት የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ ምንም ዓይነት ችግር ከዕውቀትና ከእውነት ትንተና ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በተመሳሳይ ማንኛውም ክፋት ከዕውቀትና ከትንተና ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ለበጎም ይሁን ለእኩይ ዓላማ ዕውቀት ስለሌለን፣ ችግሮቻችን ሌላ ችግር ይወልዳሉ እንጂ ለጋራ ጥቅማችን የሚፈይዱት ነገር የለም፡፡
ለምሳሌ የምዕራባውያንን አካሄድ ብንመለከት አገራቸውን በዕውቀትና በእምነት ሲገነቡ፣ ሌሎች ለአገራቸው ጥቅም በሚያውሏቸው አገሮች ላይ ደግሞ በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ሴራ ፍላጎታቸውን ያስፈጽማሉ፡፡ በዚህ ዓላማ ላይ ከጋራ ፍላጎት በላይ የምትከላከለው ነገር የለም፡፡ የእኛ የጋራ ዓላማችን ድግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ እናም የውስጥ ፍላጎታችን በዕውቀትና በእውነት ላይ መገንባት ሲጠበቅብን፣ ከውጭ ያሉንን ፍላጎታችንን ደግሞ በዕውቀትና በምሁራዊ ትንተና ላይ ማስጠበቅ ይጠበቅብናል፡፡
ይሁንና ይህ በጠልነት፣ በሴራ፣ በወገንተኝነት የምሁር ካባ የተቸረው አካል አገሩን ቸርችሮ ከመጠቀም ውጪ ሌላ ዓላማ አያራምድም፡፡ ለእውነተኛ ምሁራንም ቦታውን አይለቅም፡፡ በዚህም የተነሳ የአገሪቱን ችግር በዕውቀትና በእውነት ላይ ተመሥርተን ለመፍታት አይቻልም፡፡ እናም አገራችን ተስፋ እንዲኖራትና አሁንም ያለው ችግር ተፈትቶ በሰከነ መንገድ መጓዝ ካለብን፣ መንግሥት በእውነትና በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ምሁራንን ሊደግፍ ይገባል፡፡ በዕውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ምሁር ደግሞ ፈጽሞ የብሔር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካና የጥቅም መሸሸጊያ ሊኖረው አይገባም፣ አይቻልምም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው zerihun_adenew@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡