ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልክ እንደ ዘመነ መሣፍንት የጀመርነው የክፍፍል መንገድ የት እንደሚያደርሰን ለመተንበይ ባልችልም፣ በተቃራኒው አፍሪካውያን ወገኖቻችን ግን ለታላቋና ለውህዷ አፍሪካ ዕውን መሆን የጀመሩት እንቅስቃሴ በጥቂቱም ቢሆን ተስፋ ሰጥቶኛል፡፡ ባለፈው ሰሞን በጂቡቲ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የመሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በጂቡቲ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካውያን በአፍሪ ኤግዚም ባንክ አማካይነት በአንድ ዓይነት ገንዘብ መገበያየት እየቻሉ ለምን በዶላር ግብይት ይፈጽማሉ ሲሉ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ነበር የተደረገላቸው፡፡ ለምሳሌ ኬንያና ጂቡቲ ሸቀጦችንም ሆነ አገልግሎቶችን በገዛ ገንዘቦቻቸው መፈጸም እየቻሉ፣ በዶላር ማከናወናቸው ትርጉም የሌለው መሆኑን ሲገልጹና አፍሪካዊ አንድነትን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ሲያክሉ ልብ ይነኩ ነበር፡፡
የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ በአዲስ አበባ ሲመሠረት፣ በወቅቱ የነበሩት መሥራች አባቶች ራዕያቸው በፓን አፍሪካኒዝም መርህ አንዲት ራሷን የቻለች ጠንካራ አኅጉር ለመፍጠር እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በወቅቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ አገሮችን አስተባብራ ድርጅቱን በአፍሪካ ለመመሥረት ትልቅ ተግባር ያከናወነችው ኢትዮጵያ፣ ከቅኝ ገዥ ኃይሎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቃ ነፃነቷን ባለማስደፈር ለአፍሪካውያን ኩራት በመሆኗ ነበር መቀመጫ የመሆን ክብርን ያገኘችው፡፡ በተለይ ደግሞ ታላቁ የዓድዋ ድል ለዚህ ታላቅ ክብር እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ እንኳንስ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዋነኛ መነቃቂያ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በእስያና በላቲን አሜሪካ በቅኝ አገዛዝ ለሚማቅቁ ተምሳሌት እንደነበር በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡
አፍሪካውያን ደግሞ ኢትዮጵያን የነፃነታቸው ፈርጥ አድርገዋት በክብር የሚጠሯት ኢትዮጵያ ዛሬም መሰባሰቢያቸው ብትሆንም፣ ከቀደምቶቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን እኩል መራመድ ባለመቻላችን ዛሬ ሌሎች አፍሪካውያን ለውህደትና ለጋራ ገበያ ምሥረታ ከእኛ በላይ እየተናገሩ ነው፡፡ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩትን ድንበር አፍርሰው አንዲት ታላቅ አፍሪካን ከአኅጉርነት ወደ አገርነት ለመለወጥ ተግተው ሲሠሩ፣ እኛ ግን እያደር ቁልቁል እየወረድን ኢትዮጵያን ወደ ዘመነ መሣፍንት ሽንሸና ውስጥ እየከተትናት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ታላቋ የጋራ መኖሪያ ቤታችንን የአፍሪካ ውህደት መጠንሰሻ ማድረግ ሲገባን በክልል፣ በዞንና በልዩ ወረዳነት ስም እየሸነሸንን አንድነትን ተፀይፈናል፡፡ ከአገራዊ ማንነት በላይ ብሔርና ብሔረሰብ ውስጥ ተወሽቀን እንደ ጠላት እየተያየን እየተጠፋፋን ነው፡፡
በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ትልቅ የገበያ ይዞታ እንዲኖረን ከመሥራት ይልቅ፣ በማያሠሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ታጥረን ከተመፅዋችነት የማያወጣ የፖለቲካ ልፊያ መርጠናል፡፡ ስንዴ አምርተን ስማችን የዓለም ስንዴ አምራቾች ካርታ ላይ ቢሰፍርም፣ በዕርዳታ እህል ዘረፋ ስማችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲጠለሽ እንኳን ራሳችንን መከላከል አልቻልንም፡፡ በትክክል ያመረትነውንና የተመፀወትነውን አመሳክረን ራሳችንን መከላከል ሳንችል፣ በሌላ በኩል ለጎሰኝነት ፖለቲካ የምናጠፋው ጊዜና ጉልበት ግን ምን ያህል ብኩን መሆናችንን ያሳያል፡፡ ዊሊያም ሩቶ በቀደም ዕለት እርስ በርስ በምናደርገው ግብይት ገንዘቦቻችንን መጠቀም እንችላለን ሲሉ፣ እኛ ግን ዶላር ለማግኘት ስንችል ብቻ የምዕራባውያንና የገንዘብ ድርጅቶቻቸው ሰለባ ሆነን አገር አጥፊ ድርጊቶች ላይ ተሰማርተን ድህነትን በእጥፍ እያመረትን ነው፡፡
በቅርቡ መንግሥት የመጪውን ዓመት በጀት ለፓርላማ ሲያቀርብ የበጀት ጉድለቱ ምን ያህል እንደሆነ ታዝበናል፡፡ በጀቱ ካለፈው ዓመት በጣም ትንሽ በሚባል መጠን አድጎ ቢቀርብም፣ ካለው የዋጋ ግሽበት አንፃር ጨመረ አይባልም፡፡ ስለዚህም ይህንን ጉድለት ለመሙላት ሲባል በምዕራባውያን የገንዘብ ድርጅቶች ግፊት ተደራራቢ ታክሶች ሕዝቡ ላይ እንዲጫኑ ተደርጓል፡፡ ለዚህም የቤት ኪራይና የንብረት ይዞታ ግብር ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም የብር አቅምን በማዳከም በእጥፍ ዋጋውን ማሳነስ፣ ፕራይቬታይዜሽንን በማጠናከር የመንግሥት አትራፊ ተቋማትን ለውጭ ባለሀብቶች በረከሰ ዋጋ መሸጥ፣ የመሠረታዊ አቅርቦቶችን ድጎማ ሙሉ ለሙሉ ማንሳት፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ማጠፍ፣ መንግሥታዊ ቅጥሮችን ማቆምና የመሳሰሉ ዕርምጃዎች ብዙ እየተባለባቸው ነው፡፡
አፍሪካውያን ከአሜሪካ ጋር ለሚኖረን ግብይት ዶላር፣ ከአውሮፓ ጋር ደግሞ ዩሮ፣ እርስ በርሳችን ግን ግብይቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ በራሳችን እናድርግ ብለው ፋና ወጊ ዕርምጃዎችን እያመላከቱን ነው፡፡ እኛ ግን የገባን አልመሰልንም፡፡ ይልቁንም የእርስ በርስ ሽኩቻውን በማጧጧፍ ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯትን አገር ለመፈረካከስ የተነሳን እንመስላለን፡፡ በመነሻዬና በመሀል ስለዘመነ መሣፍንት ያነሳሁት በዚያን ጊዜ በየአካባቢው የነበሩ ባላባቶች ኬላ እየመሠረቱ ሕዝብ ሲዘርፉ፣ እርስ በርስ ሲዋጉም ሕዝቡን እየማገዱ አገር ሲያጠፉ ኖረዋል፡፡ በመጨረሻም አፄ ቴዎድሮስ ተነስተው የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ ፈር ቀደው ነው፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የተነሱባቸውን ወራሪዎችና ተስፋፊዎች በማሳፈር ለአፍሪካ ኩራት የሆኑት፡፡ ዛሬ ግን ወደ እዚያ አስከፊ ዘመን እየተመለስን እንዳይሆን ያስፈራል፡፡
ኢትዮጵያ አገራችንን አሁንም የአፍሪካ ማዕከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን እንወዳታለን ከማለት በላይ በተግባር የሚገለጽ ተግባር ይጠበቅብናል፡፡ ለዲስኩር ያህል ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም›› ትኑር ከሚለው መፈክር በላይ፣ በእርግጥም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለዘለዓለም ማስታወሻ የሚሆናት አኩሪ ተግባር ለማከናወን ታማኝ እንሁን፡፡ ለሥልጣን፣ ለክብር፣ ለዝና፣ ለጥቅምና ለሌሎች ጉዳዮች ስንል ብቻ ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው ሲጠራ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪካቸውን እያሰብን፣ ከኢትዮጵያ አልፈን በአፍሪካና በዓለም ስማችንን በክብር የሚያስጠራ ሥራ ለማከናወን እንትጋ፡፡ አገር አፍራሽ ድርጊቶች ላይ መሰማራት ግን የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አንዘንጋ፡፡
(ቶማስ ሶርሳ፣ ከአፍንጮ በር)