Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዳይመንድ ሊግ ተከታታይ ድሎችና አዳዲስ ክብረ ወሰኖች

የዳይመንድ ሊግ ተከታታይ ድሎችና አዳዲስ ክብረ ወሰኖች

ቀን:

በተለያዩ ከተሞች የዳይመንድ ሊግ ውድድር እየተከናወነ ነው፡፡ መነሻውን ዶሃ ያደረገው ውድድሩ አምስተኛው ከተማ ላይ ደርሷል፡፡ በ14 ከተሞች የሚከናወነው ውድድሩ አምስተኛው ዙር በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ በርካታ ከዋክብት አትሌቶችን እያሰባሰበ የሚከናወነው ውድድሩ ከወዲሁ ክብረ ወሰኖች እየተመዘገቡበት ነው፡፡

የዘንድሮ ዳይመንድ ሊግ በኳታር ዶሃ ጀምሮ፣ ራባት፣ ሮም፣ ፓሪስና ኦስሎ ተከናውኗል፡፡ በአብዛኛዎቹ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች ክብረ ወሰኖች ተመዝግበውበታል፡፡ አትሌቶች ክብረ ወሰን በማሻሻል የውድድሩ ድምቀት መሆን ችለዋል፡፡ በተለይ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ በመካከለኛና ረዥም ርቀት ሲደምቁ ታይተዋል፡፡

አምስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ባለፈው ሐሙስ በኦስሎ ከተማ የተከናወነ ሲሆን፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊም በ5000 ሜትር አንገት ለአንገት ተናንቀው የገቡበት አጨራረስ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡

የምንጊዜም ፉክክር የተባለውና ድንቅ አጨራረስ በታየበት በዚህ ውድድር አሸናፊውን ለመለየት እንኳን አልተቻለም ነበር፡፡

በ5000 ሜትር ፍፃሜ ዮሚፍ 12፡41፡73 የገባበት ሰዓት ሲሆን፣ ኡጋንዳዊው ኪፕሊም በተመሳሳይ ሰዓት 12፡41፡73 በመግባት ያጠናቀቀበት አጨራረስ አስደናቂ ነው፡፡

አሸናፊውን አትሌት ለመለየትም ስክሪን ፎቶ መመልከት ግድ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሁለቱ አትሌቶች የገቡበት ሰዓት ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ርዝመቱን ተጠቅሞና አንገቱን ቀድሞ በማሾለኩ አሸናፊ ሆኗል፡፡

እግር በእግር ተያይዘው ሲፎካከሩ የነበሩት ሁለቱ አትሌቶች የመጨረሻውን አራት ዙር 60.09፣ 60.07፣ 58.42 እንዲሁም 55.75 ሮጠውታል፡፡

በሁለቱ አትሌቶች መካከል የነበረው ፉክክር የዳይመንድ ሊጉ የማይረሳ ድምቀት መሆን ችሏል፡፡ በተለይ የዮሚፍ አይበገሬነት እ.ኤ.አ. 2011 የዴጉ ዓለም ሻምፒዮና በአሥር ሺሕ ሜትር ፍፃሜ ኢብራሂም ጄላን፣ ሞ ፋራን ያሸነፈበትን አጋጣሚ ያስታወሰ ነበር፡፡

‹‹ይሄን ውድድር ማሸነፍ የምንገዜም ህልሜ ነበር፡፡ የቀጣይ ዕቅዴ ሞናኮ ነው፡፡ ከዚያም አንድ ቀን የኦሊምፒክ ሻምፒዮን መሆን፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ማሸነፍ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ የተቻለኝን አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ውጤት በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› በማለት ዮሚፍ ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡  

በበርካታ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ልምድ ያካበተው ዮሚፍ የዓመቱን ድንቅ ብቃት ያሳየበት ውድድር መሆን ችሏል፡፡

በዚህም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ርቀቶች ካስመዘገባቸው የግሉ ምርጥ ሰዓት በተጨማሪ ሌላ የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል፡፡ በርቀቱ ሌላው ኢትዮጵያዊ ጥላሁን ኃይሌ 12፡46፡25 በማጠናቀቅ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ የራሱን ምርጥ ሰዓት አምጥቷል፡፡ ሳሙኤል ተፈራ በርቀቱ የተሳተፉ ሦስተኛው ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ 13፡02፡09 በመግባት ሰባተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

በሌላ በኩል በሴቶች የማይል ውድድር የ17 ዓመቷ ብርቄ ኃየሎም የመጀመሪያዋን የዳይመንድ ሊግ ድል መቀዳጀት ችላለች፡፡ ብርቄ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 4፡17፡13 ወስዶበታል፡፡ በዚህም የዓለም ከ20 ዓመት በታች ክብረ ወሰን መያዝ ችላለች፡፡

እ.ኤ.አ. 2022 ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሎምቢያ ካሊ 1500 ሜትር ወርቅ፣ እንዲሁም በዘንድሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በድብልቅ ሪሌይ የብር ሜዳሊያ ማሳካቷ ይታወሳል፡፡

በዶሃ ዳይመንድ ሊግ በ1500 ሜትር 4፡01፡86 ስድስተኛ ደረጃን ይዛ የግሏን ምርጥ ሰዓት ማምጣት ችላ ነበር፡፡ በሞሮኮ ራባት በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ደግሞ የአፍሪካ ከ18 ዓመት በታች ክብረ ወሰን ያስመዘገበችበት ውድድር ነበር፡፡

ብርቄ በራባት የ1500 ሜትር ውድድር 3፡57፡66 በመግባት የአገሯን ልጆች ፍሬወይኒ ኃይሉና ጉዳፍ ፀጋይን ተከትላ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡

በውድድሩ መሻሻሎችን እያሳየች የመጣችው ብርቄ፣ ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች መካከል ትጠቀሳለች፡፡

አትሌቷ እስካሁን ከተደረጉት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በዶሃ፣ በራባትና በኦስሎ መሻሻሎችን ያሳየች ሲሆን፣ በቀሪ ውድድሮች አዲስ ክብረ ወሰን ትሰብራች የሚል ግምት አግኝታለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከኬንያ አትሌቲክስ ጋር ሲነፃፀር በርካታ የቤት ሥራዎች  ይጠብቁታል፡፡

የዳይመንድ ሊግ ውድድርን ጨምሮ በአትሌቲክሱ አዳዲስ ክብረ ወሰኖች እየተመዘገቡ ነው፡፡ ውድድሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በ1500፣ በ3000 ሜትር እንዲሁም በ3000 መሠናክል እንዲሁም በ5000 ሜትር አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ተመዝግበዋል፡፡

ከሳምንታት በፊት በፈረንሣይ ፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሠናክል የዓለም ክብረ ወሰን የያዘበት ይታወሳል፡፡

የኦሊምፒክና የዓለም የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ለሜቻ በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ሦስት ሺሕ መሰናክል 7፡52፡11 በመግባት ለ19 ዓመት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብሯል፡፡  

ከዚህም ባሻገር የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ተሰጥቶት የነበረው፣ የዓለም የቤት ውስጥ 3000 ሜትር ውድድር አሸንፎ የነበረው ለሜቻ ያስመዘገበው ክብረ ወሰን የፀደቀበት ሳምንት ነበር፡፡

በሌላ በኩል ኬንያዊቷ የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮናዋ ፊያዝ ኪፕዮንግ በጣሊያን ፍሎረንስ በተደረገ የ1500 ሜትር ውድድር፣ በገንዘቤ ዲባባ ለስምንት ዓመት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበሯ ይታወሳል፡፡ አትሌቷ ከ3፡50 በታች ማጠናቀቅ የቻለች ብቸኛዋ እንስት አትሌት መሆን የቻለችበት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ፣ በ5000 ሜትር ውድድር 14፡05፡20 በመፈጸም በሌላዋ ኢትዮጵያዊት ለተሰንበት ግደይ የተያዘውን ክብረ ወሰን መስበር የቻለችበት ነበር፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ሁለት ክብረ ወሰኖችን መጨበጥ የቻለችው አትሌቷ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ 35 ሺሕ ዶላርና የመኖሪያ ቤት ሸልመዋታል፡፡

ከሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ፉክክር ባሻገር፣ ኖርዌጂያኑ የአውሮፓ  የ1500 ሜትርና 5000 ሜትር ሻምፒዮን ያኮብ ደንገብሪግሴን ሌላው የዳይመንድ ሊግ ድምቀት ነበር፡፡

በአውሮፓ በርካታ ሻምፒዮናዎች ላይ የማይረታው አትሌቱ በፓሪሱ ዳይመንድ ሊግ በ3000 ሜትር 7፡04፡00 በመግባት የአውሮፓ ክብረ ወሰንን በ4.51 ሰከንድ ማሻሻል ችሏል፡፡

በኦስሎ የማይል ውድድርም ያስመዘገበው 3፡46፡46 ብሔራዊ ክብረ ወሰን ሆኖሎታል፡፡

በዳይመንድ ሊግ ውድድር በርካታ ክብረ ወሰኖች የመሻሻላቸው ምክንያት  ዘመናዊ የሥልጠና ሒደት መከተልና ቴክኖሎጂው እያሻሻላቸው የመጡ የሥልጠና መንገዶች ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የሥልጠና ሒደቶች በዋነኛነት ሲጠቀሱ፣ ዓለም አቀፍ የትጥቅ አምራቾች የሚያቀርቡት የመሮጫ ጫማ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል፡፡

በ19 ቀናት ውስጥ አራት የተለያዩ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ ውድድሩ በሌሎች ስምንት ከተሞች  የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በዳይመንድ ሊግ ውድድሩ የተካፈሉ አትሌቶች በቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

በአንፃሩ በግል ውድድሮች ስኬታማ ጊዜ የሚያሳልፉ አትሌቶች በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ከጥቂቶቹ በስተቀር ብዙዎቹ ስኬታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡

በአዳዲስ ክብረ ወሰኖች የተንበሸበሸው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በዓለም ሻምፒዮናው ይደምቃል? አይደምቅም? የሚለው ከሁለት ወራት በኋላ በሚደረገው የ2023 የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

በዓለም ሻምፒዮናው የሚካፈሉ አትሌቶች ስም ዝርዝር በቅርቡ በተሳታፊ አገሮች ይፋ እንደሚሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በመጪው ቀናት ውስጥ የመካከለኛና የረዥም ርቀትር አትሌቶች ስም ዝርዝር አስታውቆ መደበኛ ልምምዱን እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...