Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው እነ መምህርት መስከረም አበራ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

የሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው እነ መምህርት መስከረም አበራ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

ቀን:

  • የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል ስላሉ ተከሳሾች ኢሰመኮ እንዲያጣራ ትዕዛዝ ተሰጠ
  • የታሰሩት በአገራዊ ምክክሩና በሕገ መንግሥት ውይይት ላይ እንዳይሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል

መምህርትና ማኅበረሰብ አንቂ ወ/ሮ መስከረም አበራ፣ ወንድወሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ መሠረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ ማዕረጉ ቢያበይን (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር (በሌለበት)፣ ገብረአብ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ አቶ ዮርዳኖስ ዓለሜን ጨምሮ 51 ተከሳሾች (24ቱ በእስር ላይ ያሉ ሲሆን 27ቱ በሌሉበት የተከሰሱ ናቸው) የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ክሱን እያየው ላለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት አመለከቱ፡፡

በጋራና በአንድነት በመሆን የህዕቡ ቡድን በማደራጀት፣ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ግባቸውን በኃይል ዕርምጃ ለመጫን፣ መንግሥትንና ሕዝብን ለማስገደድ በማሰብ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማስገደል፣ በተለያዩ አካባቢዎች አመፅ እንዲነሳ በማድረግ 214 ሰዎች እንዲሞቱ፣ በ297 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል  ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግና ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስና የወንጀሉ ድርጊት በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ ለመሆን መስማማታቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጽፎ ያዘጋጀው ክስ ያብራራል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር የመሠረተውን ክስ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ለተከሳሾች እንዲደርስ የክስ ቻርጁ በችሎት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ክሱ ከማስረጃ ጋር ተመሳክሮና በፍርድ ቤቱ ማኅተም ተረጋግጦ መቅረብ ቢኖርበትም ተሟልቶ ባለመቅርቡ ለተወሰኑ ተከሳሾች ብቻ ተሰጥቶ ለሌሎቹ ተከሳሶች ለመስጠት ክሱ በፍርድ ቤቱ ማኅተም ተረጋግጦ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡ እንዲሁም ሦስተኛ ተከሳሽ መሠረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ስለደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ አቅርበው እንደነበር አስታውሰው፣ ችሎቱ በመቀየሩ ጉዳያቸው ምን ላይ እንደደረሰ በመጠየቃቸውና 47ኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ እንየው በሰላም ማስከበር ወቅት ዘመቻ ላይ በነበረበት ወቅት በጥይት ተመትቶ በሰውነቱ ውስጥ የቀረ ጥይት መኖሩን በማስረዳት፣ በቀጠሮው ቀን ሐኪም ቤት እንዳይቀርብ በመደረጉ ለ75 ቀናት ሰውነቱን መታጠብ እንዳልቻለ በማስረዳቱ፣ ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደርሷል የተባለውን የመብት ጥሰት እንዲያጣራ የተሰጠውን ትዕዛዝ ውጤት ለመቀበልና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ክርክሩ በሰፊ አዳራሽ እንዲታይ ያቀረበውን ጥያቄ በሚመለከት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር፡፡ እንዲሁም በክሱ ላይ ማኅተምን ማድረግን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ የፍትሕ ሚኒስቴር ማኅተም በክሱ ላይ ስላለ ኃላፊነቱን የሚወስደው ተቋሙ መሆኑን በሰጠው ምላሽ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠትም ነበር ቀጠሮ የተሰጠው፡፡

ዓርብ ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ እንደተሰየመ፣ የመሀል ዳኛው ሐዘን ገጥሟቸው ባለመቅባቸው ብይኑ የተሠራ ቢሆንም በሌሉበት ማንበብ ስለማይቻል ለሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

በሰውነቱ ውስጥ ጥይት እንዳለና ሕክምና እንዳላገኘ 47ተኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ እንየው በመናገሩ ፍርድ ቤቱ ለምን ሕክምና እንዳላገኘ የፌዴራል ፖሊስ ተወካይን ጠይቋል፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመቅረቡ ተከሳሹ በሰውነቱ ውስጥ ያለው ጥይት ከሳንባው ጋር የተነካካ በመሆኑ ቀዶ ሕክምና ቢደረግለት 75 በመቶ የመሞት አጋጣሚ እንደሚገጥመው በማስረዳት የሕመሙን ከፍተኛነት ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጣርቶ እንዲቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ በሚመለከት እንዳልደረሰለት አስረድቶ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ለሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በዕለቱ ባሰሙት አቤቱታ ኢሰመኮ ለተከሳሾች እንዴት ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ጥያቄ ሲያቀርብ ፖሊስ አብሮ እየቀረበ እንደሚያስፈራራ ተናግረዋል፡፡ የኢሰመኮ ተወካዮች ግን፣ ተከሳሾቹ ፈቅደው እንጂ ኢሰመኮ ምርመራ ሲያደርግ ፖሊስ እንዲኖር አሠራሩ እንደማይፈቅድ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹የኢሰመኮ አሠራር ከሆነ ፖሊስ አብሮ እንዲሆን ለምን ፈቀዳችሁ?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸው ስህተት መሆኑን በማስረዳት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ ዓቃቤ ሕግ በፍላሽ የሰነድና የኦዲዮ ማስረጃ የሰጣቸው ቢሆንም፣ አሁን ታስረው የሚገኙበት የፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከበር ላይ እንደተቀበላቸውና የቀረበባቸውን ማስረጃ የማየትም ሆነ የመስማት መብት እንደተነፈጉ አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ እስረኞች እንደሆኑ እንደሚያምኑ የተናገሩት ተከሳሾቹ፣ አገራዊ ምክክር በሚደረግበትና ሕገ መንግሥቱ ላይ ውይይት በተጀመረበት ጊዜ የታሰሩት የአማራን ሕዝብ ወክለው እንዳይሳተፉ ለማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ለምን የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንደማይከበር ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤት የፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ጠርቶ ዕርምት እንዲወስዱ ማስደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በሕይወታቸው ላይ የሚወስንን ማስረጃ በፖሊስ ጣቢያ አስተዳደር መነጠቃቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረው፣ ከታሰሩ ከ77 ቀናት በላይ ስላስቆጠሩ ፍርድ ቤቱ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

መሠረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር) የተባሉት ተከሳሽ ለችሎቱ እንዳስረዱት በ‹‹67 ዓመቴ፣ ከልጅ ልጄ የሚያንስ የሃያ ዓመት ልጅ ልብሴን አስወልቆ ገርፎኛል፤›› ብለው ይኼ ድርጊት ተጣርቶ ፍርድ ቤቱ የደረሰባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲመለከትላቸው ጠይቀዋል፡፡

የሰነድ ማስረጃና የድምፅ ማስረጃን የያዘው ፍላሽ ተፈቅዶና ሰፊ ጊዜ ተሰጥቷቸው በመስማትና በማንበብ የመከላከል መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ዘመኑ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጊዜ በመሆኑ ተቆርጦና ተቀጥሎ የቀረበን የድምፅ ማስረጃ እራሳቸው ሰምተው ‹‹የእኔ ነው አይደለም›› የሚለውን በመለየት ለጠበቆቻቸው እንዲያስረዱ አስፈላጊ ማዳመጫ መሣሪያ ሁሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ተወካይ በሰጡት አስተያየት ፍላሽ የተከለከሉት በተቋሙ የኤሌትሮኒክስ መሣሪያዎች እንዳይገቡ በመከልከሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለተቋሙ ኃላፊዎች ማስረዳታቸውን ጠቁመው የተቋሙ አስተዳደር ግን አሠራሩ ስለማይፈቅድ መግባት እንደማይችል ለተከሳሾቹ አስረድቶ እየመዘገበ እንደተቀበላቸው ገልጸዋል፡፡ ከጠበቆች ጋር በሳምንት ሦስት ቀናት መገናኘት እንደሚችሉ ቢገልጹም ተከሳሾቹ ግን 75 ገጽ ክስና 970 ማስረጃዎች በሳምንት ሦስት ሰዓታት ብቻ ከጠበቃ ጋር በመገናኘት የሚወስደውን ጊዜ ማሰብ ይከብዳል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ ለተከሳሾችና ጠበቆች በቂ ጊዜና ቦታ እንዲሰጣቸው ነገር ግን አመቺ ቦታና ጊዜ ለመስጠት የሚቆዩበት ቦታ ሲታወቅ (አሁን ያሉት ፖሊስ ጣቢያ ነው) እንደሚታዘዝ ገልጿል፡፡ ፍላሹን በሚመለከት የእስረኞቹ መብታቸው በመሆኑ ሁሉም ነገር እንዲመቻችላቸውና ነፃ ሆነው እንዲወያዩ  እንዲደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ውክልና ለመስጠት እንዲችሉ ያመለከቱም መብታቸው መሆኑን ጠቁሞ ፍርድ ቤቱ እንዲፈጸምላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው ክስ ሰፋ ያለና ዘርዘር ያለ ሲሆን፣ የወንጀል ሕግ 32 (1 ሀ እና ለ)፣ 35 እና 38 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3(2) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ ‹‹አገር ተወስዶበታል፣ ርስቱ ተቀምቷል፣ አገሪቱ በአማራ ትውፊቶችና ዕሳቤ ብቻ አልተዳደረችም፤›› የሚል አቋም በመያዝ የአማራ ርስት ናቸው የሚሏቸውን መሬቶች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስና አገር ‹‹በአማራ ዕሳቤ ብቻ መገዛት አለበት›› የሚል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በስምምነታቸው መሠረት የያዙትን ርዕዮተ ዓለም አቋም በኃይል ለመተግብር፣ ስትራቴጂ በመቅረፅና የሲቪክ ማኅበራት በማቋቋም፣ ምሁራንን በማሰባሰብ፣ የአማራ ጠላቶች ናቸው የሚሏቸውን የሚገታና የሚያሸንፍ በሚል የራሳቸውን መከላከያ ኃይል ለመፍጠር በየአካባቢው የሚኖረውን የፋኖ ኃይል የተማከለ አመራር እንዲኖረው በማድረግና በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ እንዲነሳ ማድረጋቸውን በመርዘር በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡

ተከሳሾቹ መረጃ የሚያቀርብና የስለላ ሥራ የሚሠራ የመረጃና የደኅንነት መዋቅር በመዘርጋት የጦር መሣሪያ የሚገዛ ልዩ ስኮድ ለማቋቋምና የገንዘብ ድጋፍ ለመሰብሰብ እንዲረዳቸው ‹‹ለአማራ ሕዝብ ትግል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለመፍጠር መሥራት፤›› በሚል ሽፋን የዕርዳታ ድርጅት ማቋቋማቸውንም ጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴሩ በክሱ እንዳብራራው ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ኃይሎችን በህዕቡ ዓላማቸው ለመጠቀምና ካስፈለገም የስደት መንግሥት ለማቋቋም፣ የፕሮፓጋንዳን ሥራ የሚሠራ የሚዲያ ቡድን ለማቋቋም መስማማታቸውን ገልጿል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ የፋኖና ሌሎች ታጣቀቂዎችን በመሰብሰብ በአንድነት ለመምራት ‹‹የአማራ ፋኖ አንድነት አመቻች ኮሚቴ›› የሚል አደራጃጀት በማዋቀር፣ ‹‹የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት›› የሚል ኅዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን አብድራፊ አካባቢ መመሥረታቸውን ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በአጠቃላይ ሚኒስቴሩ ተከሳሾቹ በኅብረትና በማደም ፈጽመዋል ያላቸውን የሽብር ወንጀል የእያንዳንዳቸውን ድርጊትና እንቅስቃሴ በመግለጽ ክስ መሥርቷል፡፡ በሰብዓዊ መብቶቻቸው ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥሰትና ተያያዥ አቤቱታዎች ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...