የአሜሪካ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና ተመድ በኢትዮጵያ ሲያቀርቡት የነበረውን የምግብ ዕርዳታ በጊዜያዊነት ማቆማቸውን ተከትሎ ስደተኞች ሙሉ በሙሉ ከቀለብ ውጭ ሆነዋል ተባለ፡፡
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት ለስደተኞች ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግ የነበረው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በማቆሙ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞች ተግዳሮት ገጥሟቸዋል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት ዩኤስኤአይዲ ይፋ ባደረገው መረጃ አካሄድኩት ባለው የምርመራ ውጤት ከፍተኛ መጠን ያለው የዕርዳታ ምግብ አቅርቦት ላይ ምዝበራ መፈጸሙን ጠቅሶ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዕርዳታ እንዳቆመ አስታውቆ ነበር፡፡
በዚህም የተነሳ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃን የምትገኘው አትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገር ስደተኞች የምግብ አቅርቦት መቋረጡ እንዳሳሰባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2023 በሶማሊያ ላሳኖድ በነበረ ግጭት 91,000 ወደ እንዲሁም በቅርቡ በሱዳን በተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የስደተኞች ቁጥር 10,000 መድረሱን አቶ ተስፋሁን አስታውቀዋል፡፡
ከሱዳን ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች በሱዳን ተጠልለው የነበሩ የኤርትራ ስደተኞችና ሱዳናውያን ሲሆኑ የሱዳን ጦርነት ከቀጠለ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር አሁንም ሊጨምር ይችላል ተብሏል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ተስፋሁን ተጨማሪ ፋይናንስ ማግኘት ከባድ እየሆነ በመምጣቱ ምላሽ ለመስጠት ተቸግረናል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ዲያን ባለዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራውያን ስደተኞች የሚያደርገው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንና ይህ ድጋፍም እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የተወሰኑ ኤርትራውያን በአዲስ አበባ የባንከ አካውንት እንዲከፍቱ የሚደረገው ጥረት አሁንም መቀጠሉን ጠቅሰው፣ ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና የሰላም ዕጦት ካለባቸው የጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ስደተኞች አሁንም ኢትዮጵያ ድንበሯን ክፍት በማድረግ ድጋፏን በቀጣይ እንድታሳይ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡