ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ያነሰው ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› በሚባለው የማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድና በፀጥታ ችግር ምክንያት መሆኑን፣ የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት በማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ በጠራው ስብሰባ ነው፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ መጠን ያለው ወርቅ ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ የገባው ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም. መሆኑን ጠቁመው፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በዓመት እስከ 12 ቶን ወርቅ ድረስ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
ከዚያ በኋላ በ2013 ዓ.ም. ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚገዛበትን ዋጋ 35 በመቶ በማሳደጉ ሳቢያ፣ በዓመት እስከ ስምንት ቶን ወርቅ ባንኩ መግዛቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚያ ወዲህ ግን ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተው፣ ይህም በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመጀመርያው ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› በሚባለው የማዕድን ማምረት ፈቃድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከተሰማሩ በኋላ፣ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ አለማስገባታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ተብሎ በሚኒስትሩ የቀረበው ደግሞ የፀጥታ ችግር ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ አብዛኞቹ የወርቅ ማዕድን የሚገኝባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ችግር አለባቸው፡፡ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን በፀጥታ ችግር ተጠቃሽ አድርገዋል፡፡
በተለይ በ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› የማዕድን ማውጣት ፈቃድ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ የገቡ የውጭ አገር ዜጎች ጭምር ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም የአካባቢዎችን ማኅበረሰቦች የጠቀመ እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ፈቃድ ምክንያት ወርቅ ከአገር እየሸሸ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ወክለው የተገኙት አቶ ፍቅሬ ኃይሌ፣ ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› ማዕድን የማምረት ፈቃድ በረቂቅ አዋጁ መሰረዙ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በ‹‹ልዩ አነስተኛ ፈቃድ›› ችግር ካለም አስተዳደራዊ ላይ መሆኑን በመግለጽ፣ ከረቂቅ አዋጁ ከመሰረዝ ይልቅ የተሻለ አሠራር መዘርጋት እንደሚሻል አቶ ፍቅሬ አሳስበዋል፡፡
በማዕድን ልማት ዘርፍ ፈቃድ አግኝተው የሚሠሩ ቁጥራቸው በርካቶች በመሆናቸው፣ በረቂቅ አዋጁ አለመካተቱን አዋጭ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ወክለው የተገኙት አቶ ዓረቢ አብዲላሂ በበኩላቸው፣ በክልሉ ካሉት ከሃያ ያላነሱ ወረዳዎች ውስጥ በ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› ወርቅ በማምረት የተሰማሩ ቁጥራቸው ብዙ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኑሮዋቸው፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውና የምግብ ዋስትናቸው ጭምር ከዘርፉ ጋር የተቆራኘ መሆኑን በመግለጽ ከተዘረዘሩ ፈቃዶች ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› ፈቃድ መሰረዙ ተቃውመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ መሠረት በባህላዊ መንገድ ሲያመርቱ የነበሩትን ክልሉ ዕገዛ አድርጎ ወደ ልዩ አነስተኛ ፈቃድ እንዲሸጋገሩ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የማዕድን ልማት ረቂቅ አዋጅ ልዩ አነስተኛ ደረጃ ማዕድን የሚወጣት ፈቃድ መሰዘረዙ ተገቢነት እንደሌለው በማስረዳት፣ በዘርፉ ላይ ችግሮችም ቢኖሩም ሀብቱን ማስተዳደር ጉድለት የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ዓረቢ ገለጻ፣ ሚኒስቴሩ በረቂቅ አዋጁ ‹‹ልዩ አነስተኛ ፈቃድ›› ከመሰረዙ በፊት፣ ያለውን ጠቀሜታና ጉዳት በጥናት ማረጋገጥ ነበረበት፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ለአልሚዎች ከሚሰጡ ፈቃዶች በተራ ቁጥር አምስት ላይ በሚገኘው ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› ማዕድን ማምረት ሥራ የተሰማሩት፣ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ ሲያስገቡ የቆዩ ናቸው ብለዋል፡፡
ዘርፉ አገር በጦርነት በተጠመደችበት ወቅትም ቢሆን ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ በማስገባት ብቸኛው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ የማዕድን ማምረት ፈቃድ ላይ ክፍተቶች ቢታዩ እንኳ የተሻለ መፍትሔ ማቅረብ እንጂ፣ ከረቂቅ አዋጁ ውስጥ ማውጣት ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ አንዱ የሆነው ‹‹ልዩ አነስተኛ ፈቃድ››ን በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ አለማካተት ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር ትልቅ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋታቸውን በመግለጽ፣ ሚኒስቴሩ በድጋሚ ማየት እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጨቃ፣ ሌሎች ክልሎች በሥጋት ያነሱትን ጉዳይ እንደሚጋሩት አስታውቀዋል፡፡
የ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› የማዕድን ማውጣት ሥራ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ከረቂቅ አዋጁ ከመሰረዝ ይልቅ፣ በሌላ ሁኔታ የሚካተቱበትን አማራጭ ማየት እንደሚሻል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
የማዕድን ማምረት ፈቃድ ዓይነት ጊዜና ጉልበት ከመቆጠብና ከሌሎች ሁኔታዎች አንፃር ከባህላዊ ማዕድን ማምረት የተሻለ በመሆኑ፣ ከረቂቅ አዋጁ ባይሰረዝ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ይህንን ሐሳብ የሚጋሩት ጋምቤላ ክልልን ወክለው የተገኙት አቶ ሙት ሎንግ ሲሆኑ፣ ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› ፈቃድ መሰረዝን ከሚቃወሙት ወገን ናቸው፡፡
በጋምቤላ ክልል በልዩ አነስተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች በርካቶች በመሆናቸው፣ ፈቃዱን መሰረዝ ሥራ አጥነትን እንዳያባብስ ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከረቂቅ አዋጁ ከመሰረዝ ይልቅ ያሉበትን ችግሮች ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በዘላቂነት መፍታት የሚቻልበትን ዘዴ ማዘጋጀት እንደሚያሻ ጠቁመዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ኢንጂነር) ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ብዙ የተቀየረ ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ ‹‹ሜጋ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎችን እንደ አገር መደገፍ ይሻላል በማለት ወደ ፌዴራል መጥተዋል፡፡ ይህም በፌዴራል ቢተዳደሩ ጠቃሚ ነው በሚል የገቡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በማዕድን ዘርፍ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች አገር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሟል፡፡
ለዝርፊያው አንደኛው መንገድ ሆኖ የተገኘው ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› የማዕድን ማምረት ሥራ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ፈቃድ አወጣን ከሚሉት ሰዎች ጋር ያልተፈቀደላቸው የውጭ አገር ዜጎች ጭምር ገብተው ማዕድናትን ሲያሸሹ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይህንን የአገር ሀብት የማሸሽ ችግር በጥልቀት በማየት ሕግ ለማስከበር በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡
የማዕድን ሀብት በጥንቃቄ ካልተመራ የፀጥታ ችግር በመፍጠር አገር እንደሚያናጋ ያስረዱት ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ በትክክል ለማስተዳደር የሚቻልበት የተሻለ አሠራር ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የ‹‹ልዩ አነስተኛ ደረጃ›› የማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ዓይነት በቀድሞ አዋጅ አንቀጽ 44 ንዑስ አንቀጽ 35 (ሀ) መሠረት፣ በግለሰቦች ወይም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ደረጃ የሚከናወን ሥራ ነበር፡፡