Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም ባንክ የኢንሹራንስ ዘርፉን በሚቆጣጠር ተቋም ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንሹራንስ ዘርፉ ከብሔራዊ ባንክ ውጪ በሆነ ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲመራ ለማስቻል ተፈላጊ የሆነው ጥናት በዓለም ባንክ አማካይነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በዓለም ባንክ በኩል የሚደረገው ጥናት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰፊ የሆኑ ተግባራትን እንደሚሸፍን ተጠቅሷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጣጠር ከብሔራዊ ባንክ ውጪ የሆነ ተቆጣጣሪ እንዲቋቋም ጥናት ተጀምሯል፣ “Terms of Reference” እና ሌሎችም ጉዳዮች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

በጥናቱ የመጀመርያ ሥራ ተብሎ የተያዘው ጉዳይ ገለልተኛ ተቋም ‹‹እንዴት ይዋቀር?›› የሚለው ሲሆን፣ ከዚያም ተጠሪነቱ ለማን ይሁን? ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ነው? ለፓርላማው ነው? የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችንም መሆኑን ምክትል ገዥው አስታውቀዋል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን የኢንሹራንስ ዘርፉን ለውጭ ክፍት ለማድረግ ሪፎርም መደረግ እንዳለበትና ብዙ የሕግ ማዕቀፎች ጎን ለጎን መሠራት ስላለበት ሥራው በአሁኑ ወቅት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በየካቲት ወር መጀመርያ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥው የኢንሹራንስ ኢንዲስትሪውን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሠሩ ጉዳዮች አንዱ ዘርፉን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ማቋቋም መሆኑን፣ ሥራውንም ከአማካሪና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር፡፡

ስድስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ባሳለፍነው ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ሲደረግ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ፣ በአምስተኛ ጉባዔ ላይ ማኅበራቸው የኢንሹራንስ ዘርፉ ‹‹ሊበራላይዝ›› እንዲደርግና ራሱን የቻለ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ አካል እንዲቋቋም ጠይቆ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ የሚቋቋምለት ሒደት ላይ እንደሆነ፣ ለዚህም ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ለገንዘብ ሚኒስቴር ምሥጋና እንደሚገባቸው አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡

 በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ፣ በ2009 ዓ.ም. የወጣው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ የማሻሻል ሥራ እየተጠናቀቀ እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ‹‹ከአንዳንድ የድጋፍ ሰጪዎች ግብዓቶች ካሉ እየጠየቅን ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ከዚህ በፊት ባሉት መሠረት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለፓርላማ እናቀርባለን ተብሏል፡፡ ስለዚህ እየተፋጠነ ነው›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

አዋጁ እንደወጣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚጠጉ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ይሰጣል ተብሎ የታቀደ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከዚያ በላይ ከፍ የማድረግ ዕቅድ እንደሌለ፣ ይህም ከአቅም በላይ እንዳይሆን ከሚል ዕሳቤ እንደሆነ ምክትል ገዥው ተናግረዋል፡፡

 በስካይላይት ሆቴል በተደረገው የምሥራቅ አፍሪካ አጠቃላይ የፋይናንስ ስድስተኛው ጉባዔ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ፣ የፋይናንስ አካታችነት፣ የካፒታል ገበያ ቅልጥፍና እንዲሁም አጠቃላይ ቀጣናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ለውጥ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

ጉባዔውን ያሰናዳው የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ለስድስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ጉባዔ የፋይናንስ ዘርፉን መሠረት ያደረገ ውይይት እንደማድረጉ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት የፋይናንስ ሥርዓት እንዴት ይገነባል? ከተደራሽነት አንጻር ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ አገሮች ጋር ስትነፃፀር ያላት የፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የት ላይ ነው የሚለውን የሚዳስስ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች