ይህ ወቅት ለብዙዎች ከመጠን በላይ ግራ አጋቢ፣ አስጨናቂና ፈታኝ እየሆነ ነው፡፡ ዜጎች በገጠርም ሆነ በከተማ የሚያስጨንቋቸውና የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ከመብዛታቸው የተነሳ፣ ግራ መጋባትና ሥጋት ብዙዎች የሚጋሩት የዘወትር አሳር እየሆነ ነው፡፡ አርሶ አደሮች ከግብርና ግብዓቶች በተለይም በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል በተደጋጋሚ አቤቱታ እያሰሙ ነው፡፡ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት የሚመሩ አርሶ አደሮች በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ከድህነት መላቀቅ ሲገባቸው፣ የተለመደውን ኋላቀር እርሻቸውን የሚያከናውኑባቸው ግብዓቶች ሲያጡ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ለከተሜው የምግብ ምንጭ የሆኑ አርሶ አደሮች ራሳቸው ተቸግረው ማምረት ሲሳናቸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊከተል የሚችለው የምግብ እጥረትና የዋጋ ግሽበት አስፈሪ ነው፡፡ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በሥራ አጥነት፣ በዝቅተኛ ገቢ፣ በመጠለያ ዕጦት፣ ማቆሚያ ባጣ የኑሮ ውድነትና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው ሕይወታቸው ሲመሰቃቀል ከተስፋ ይልቅ የሥጋት ደመና ይከባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሰላም ዕጦት ሲታከልበት ምሬትና ተስፋ ቢስነቱ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ጭንቀትና ሥጋት የወረረው ሕይወት መምራት እየከበደ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ተስፋ የሚያሳጡ ችግሮች ሲበዙ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት፣ ሕዝብን የሚያረጋጉና በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለቤትነት የሚፈጥሩ ሥራዎች ላይ ማተኮር ነው፡፡ እርግጥ ነው አገር ችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ እያንዳንዱ ዜጋ የችግሩ ተጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ ከችግር የሚያወጡ መፍትሔ አመላካች ተግባራት ላይም አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማበረታታት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ዜጎች እንደ ዕውቀት፣ ልምድ፣ ሀብትና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ አስተዋፅኦዎች ማበርከት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሳይደረግ መግባባት ሊኖር አይችልም፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ፣ የሕዝብ ተሳትፎን ጉዳይ ከታይታ ባለፈ በተጨባጭ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ሲጎዳም ሆነ ፀጥታዋ ሲታወክ የአገር ባለቤት የሆነው ሕዝብ ምክረ ሐሳብ ቢጠየቅ፣ አስደናቂ የሆኑ መፍትሔ አመንጪ መላዎች ከውስጡ ሊገኙ እንደሚችሉ መጠራጠር አይገባም፡፡ ምክንያቱም የዕውቀት ደጃፍ ያልደረሱ በአገር በቀል ዕውቀት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ጠብሰቅ ያለ ዕውቀት የሰነቁ ደግሞ በዘመናዊው መንገድ ሊያግዙ ይችላሉ፡፡
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወሰዳቸው ባሉ ዕርምጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምሬቶች ሲሰሙ፣ የምሬቶቹ መነሻ ምክንያቶች ስለሚታወቁ ቀረብ ብሎ ለማነጋገር ፈቃደኝነት አይታይበትም፡፡ ማንም ዜጋ ሆነ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም የሚፈለግበትን ግብር መክፈል እንዳለበት ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ግብር መክፈልም የሚያኮራ አገራዊ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም በሥራ ላይ ያሉ ዜጎች የግብር ሥርዓቱ መረብ ውስጥ መግባትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ደሃ አገሮች መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ፣ በሀብታቸው ጣራ የነኩ አገሮች ሳይቀሩ በጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ግብር ይሰበስባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብር ሰብሳቢ ተቋማትን ዘመናዊነት በማላበስ፣ ጠንካራ አመራሮችንና ብቁ ባለሙያዎችን በመመደብ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር በማስፈን ግብር መሰብሰብ በብዙ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ይህ በምልዓት መከናወን ከቻለ፣ አሁን ከሚሰበሰበው ግብር በላይ መንግሥት ማግኘት አያቅተውም፡፡ ነገር ግን ግብር ሰዋሪዎች፣ አጭበርባሪዎችና በሐሰተኛ ደረሰኝ የሚሸፍጡ መንግሥትን በርካታ ቢሊዮኖችን እያሳጡ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
መንግሥት የግብር ሥርዓቱን በማዘመን በግላጭ የሚታወቁ አጭበርባሪዎችን አሳዶ መያዝ ከቻለ፣ ለማመን የሚያዳግት ገቢ እንደሚያገኝ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ውስጡ ሆነው ውጭ ካለው ዘራፊ ጋር የሚሞዳሞዱትን ልክ በማስገባት ጥንካሬውን ካሳየ፣ ለልማት ሊውል የሚችል ከፍተኛ ሀብት ማግኘት አያዳግተውም፡፡ ነገር ግን የግብር ሥርዓቱ በቀላሉ የሚያውቃቸው ግብር ከፋዮች ላይ ግብር ሲደራረብ ምሬቱ ጣራ ይነካል፡፡ የይዞታ ግብርም ሆነ የኪራይ ግብር መሰብሰብ ያለበት ቢሆንም፣ ከዜጎች አቅም በላይ የሆነ ሥሌት ይዞ መጥቶ ውለዱ ማለት ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ለሥራ ፈጠራም ሆነ ሀብት ለማፍራት አያደፋፍርም፡፡ የታክስ መረቡ የማያውቃቸው በርካቶች በሐሰተኛ ደረሰኝ በማጭበርበር፣ በኮንትሮባንድ በመነገድና የተለያዩ የረቀቁ ዘዴዎችን በመጠቀም መንግሥት ማግኘት ያለበትን እያሳጡ እየከበሩ በግላጭ እየታዩ፣ ለፍቶ አዳሪዎችን መጫን ፍትሐዊ ስለማይሆን ይታሰብበት፡፡ በዘፈቀደ የሚነገሩ አኃዛዊ መረጃዎችና የተሳሳቱ ሥሌቶች ምሬቱን እየጨመሩ ስለሆነ፣ ችግሩን ጠጋ ብሎ በአንክሮ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይም ሕዝባዊ ምክክር ማድረግም ተገቢ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከዓለም ባንክም ሆነ ከአይኤምኤፍ ጋር በሚደረጉ ውይይቶችም ሆነ ስምምነቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁለት የገንዘብ ተቋማት ለአገር ጠቃሚ የሆነ ብድርና ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ በመንግሥት ሲታሰብ፣ ያደርጋሉ ተብሎ ከሚጠበቀው ድጋፍ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን እጅ ጥምዘዛ ማጤን ይገባል፡፡ እነዚህ ተቋማት መንግሥትን የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ እንዲዳከም፣ በመንግሥት እጅ ውስጥ ያሉ ስትራቴጂካዊ ድርጅቶች ለውጭ ባለሀብቶች በረከሰ ዋጋ እንዲተላለፉ፣ ነዳጅን ጨምሮ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ድጎማ እንዲነሳ፣ የመንግሥት ወጪዎች ከሠራተኛ ቅጥር ጀምሮ በጣም እንዲቀንሱና በዜጎች ላይ ከፍተኛ የግብር ጭማሪ እንዲደረግ እንደሚያስገድዱ በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ ከላይ በማሳያነት የተጠቀሱ ጉዳዮች እንደ ወረዱ አገር ላይ የሚጫኑ ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ከኮቪድ-19 ጀምሮ በጦርነትና በተፈጥሮ ችግሮች የተጎሳቆለውና የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የተሳነው ሕዝብ ያበቃለታል፡፡ መንግሥት ከውጭ የሚገኝ ድጋፍ ላይ ተማምኖ አላስፈላጊ ውሳኔ ላይ ከሚደርስ ይልቅ፣ በተፈጥሮ የታደለች አገር ፀጋዋን መጠቀም የምትችልበት ስትራቴጂካዊ መፍትሔዎች ላይ ያተኩር፡፡
የኢትዮጵያ ችግሮች ቢበዙም በትብብር መልክ ማስያዝ አያቅትም፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሊተባበሩ የሚችሉት ለተሳትፎ ዕድል ሲሰጥ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ያላቸው በርካታ አንጋፋ ዜጎች አሉ፡፡ ለወጣቱ ትውልድ አመራሮች ልምድ በማካፈልና በማማከር ውጤታማ ሥራዎች እንዲከናወኑ ማገዝ ይችላሉ፡፡ አበርክቶአቸውንም ያለ ክፍያ በነፃ ለማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ ይህም ቁርጠኝነት በተለያዩ መድረኮች ሲነገር ተደምጧል፣ በተግባር ያሳዩም ብዙ ናቸው፡፡ በውጭ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በጣም በርካቶች ለአገራቸው ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ገንዘባቸውንና ሌሎች ድጋፎቻቸውን ለማበርከት ፈቃደኛ እንደሆኑ በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጉልበታቸውንም ሆነ ሕይወታቸውን ለአገራቸው ከመስጠት እንደማይመለሱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የሚያኮራ እውነታ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ጭንቀትና ግራ መጋባት በሥጋት ታጅበው ሲስተዋሉ፣ መንግሥት ከማንም በፊት አዎንታዊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ቀድሞ መነሳት ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት የጭንቀትና የሥጋት ደመናውን ይግፈፍ!