Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማዳበሪያ ገዝተው ማስገባት ሊጀምሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመጪው 2016 ዓ.ም. ጀምሮ  የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያ ግዥን ከውጭ አገር ገዝተው ማስገባት እንደሚጀምሩ ተገለጸ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከውጭ አገር ግዥ ፈጽመው ወደ አገር እንዲያስገቡ የሚከለክል ሕግ ባይኖርም አሁን ላይ ገዝተው እያስገቡ አለመሆኑን ገልጸው ከመጭው ዓመት ጀምሮ ግን ማስገባት እንደሚጀምሩ በግብርና ሚኒስትር የኢንቨስትመንትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፊያ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

 ሚኒስትሯ አክለውም ለሙከራ እንዲሆን በመጪው ዓመት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ፌዴሬሽን ቢያንስ አንድ መርከብ ማዳበሪያ አስገብቶ እንዲለማመዱ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት ከጥቂት ቀናት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን የ2013/14 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት በገመገመበተ ወቅተ ነበር፡፡

 መንግሥት ማኅበራት እንደ አንድ የግል ዘርፍ መወዳደር ስላለባቸው ማዳበሪያን ከውጭ አስገብተው ለገበሬው እንዲያከፋፍሉ እንደሚፈለግ ተናግረዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከውጭ ንግድ አኳያ ያላቸው አገራዊ አስተዋጽኦ እየቀነሰ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለዚህም ተቋማቱ የአቅም ችግር ካለባቸውና መስተካከል ካለበት ተገቢው ሥራ ተሠርቶ ድርሻቸው መጨመር አለበት ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው ፍላጎት መሠረት የአገሪቱን የአፈር ማዳበሪያን ግዥ በብቸኝነት የሚያከናውነውና የእርሻ መሣሪያዎችን ጨምሮ ምርጥ ዘርና አግሮ ኬሚካሎችን የሚያቀርበው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡ በቀጣይ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በሙከራ ተጀምሮ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ማኅበራት ማስገባት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡

ለ2015/16 የመኸር ወቅት የማዳበሪያ ግዥ ላይ 21 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉን መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፣ ለተያዘው የመኸር ወቅት በበርካታ ክልሎቸ በመንግሥት በኩል በብቸኝነት የሚቀርበው ማዳበሪያ በሰዓቱ ባለመድረሱ በርካታ አካባቢዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ ለአብነት በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሠልፍ በማድረግ ቁጣቸውን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን፣ ግንቦት 23 ቀን በባህር ዳር ከተማ በርካታ ገበሬዎች በከተማ ውስጥ ተቃውሞ ሲያደርጉ ተስተውለው ነበር፡፡ ማዳበሪያው በወቅቱ ባለመሠራጨቱ በርካታ አርሶ አደሮች ግብዓቱን ከነጋዴዎች በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውንም ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች