በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ከሰነድ ባለፈ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መሬት ላይ ሊተገበር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂን ዓለም በደረሰበት ልክ በብቃትና በቅልጥፍና፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማቅረብ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ዕድገት ሊገድቡ የሚችሉ ሕጎችና ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
ይህ የተገለጸው ከቡድን ሰባት አባል አገሮች መካከል ሚክታ የሚባል ቡድን የመሠረቱት አምስቱ ማለትም የሜክሲኮ፣ የኢንዶኔዥያ፣ የአውስትራሊያ፣ የቱርክና የኮሪያ አምባሳደሮች በተገኙበት በኢንዶኔዥያ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ፣ ‹‹የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዓለም አቀፍ ችግሮችን በጋራ ትብብር ለመፍታት›› በሚል ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት ላይ ነበር፡፡
በውይይቱ በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና የአፍሪካ ኅብረት አምባሳደር አልቡስራ ባስኑር እንደገለጹት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ከኋላው ያዘለው የአቅም ማነስ ችግርና የሐሰተኛ መረጃ ዝውውር ፈታኝ ቢሆንም አገሮች ቴክኖሎጂ ላይ በተመሠረተ ጠንካራ ውድድር ማድረግ ካልቻሉ በየጊዜው የሚፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን የመጠቀም ዕድልን ያጡታል ብለዋል፡፡
የሚክታ አባል አገሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የደረሱበት ዕድገት ለበርካታ አገሮች ተምሳሌት እንደሚሆን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በወጣቱ ዘንድ የሚታየውን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ፍላጎት ወደ ኢንቨስትመንት በመቀየር አገር ተወዳዳሪና ዓለም በሚፈልገው ደረጃ እንድትቆም ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት እንደገለጹት ከአንድ ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዕድሉ በነበራቸውና ዕድሉ ባልነበራቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የዕድል መለያየት አንስተው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታች ከቤታቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራን በቀላሉ ሲሠሩ አንዳንዶች ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር የማይተዋወቁ ነበሩ ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከግሉ ዘርፍ፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ጋር በመሥራት የመንግሥት አገልግሎትን ቀላልና ፈጣን በሆነ መልኩ ማቅረብ ይቻላል ብለዋል፡፡
የኦርቢት ሔልዝ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለሙያው አቶ ፓዘዮን ቸርነት በመድረኩ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ዓለም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የረቀቁ ደረጃዎች ላይ በደረሰችበት በዚህ ጊዜ ቴክኖሎጂን መጠቀም የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ በመጪው ቅርብ ጊዜ በአገልግሎት አሰጣጣቸው በዲጂታል ቴክኖሎጂ በሚጠቀሙና በማይጠቀሙት መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት ይፈጠራል ብለዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተመራማሪው ካሊድ አህመድ (ዶ/ር)፣ በበኩላቸው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጠራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በዘርፉ መተማመን እንደሚፈጥር ጠቅሰው አሁን በሰነድ መልክ የተቀመጠው ፖሊሲና ዕቅድ መሬት ላይ ወርዶ በልኩ መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሚታሰበውን ያህል ለውጥ ለማምጣት ለግሉ ዘርፍና ለቴክኖሎጂ ተዋናዮች የፋይናንስ አቅርቦት፣ አመቺ የሥራ ቦታ እንዲሁም የኢኮኖሚውን ዲጂታል ክንፍ ጠንካራ መሠረት እንዲይዝ በማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በማቅረብ ቴክኖሎጂን ለመቀበል የሚታይን ሞገደኝነት መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡