Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ59 ሚሊዮን ዶላር ለዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን አዲስ ሕንፃ ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 59 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅና ለዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አየር መንገዱ አሁን ከሚገለገልበት የተሻለ መሥሪያ ቤት በማስፈለጉ ምክንያት፣ ሊገነባ የታቀደ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዲስ ለመገንባት የታቀደው ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ በመጪው ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን፣ ይህ አዲስ ሕንፃ የሚያርፈው በአየር መንገዱ ውስጥ በሚገኝ 23 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ግንባታውን የሚያከናውነው ‹‹China Civil Engineering Construction Corporation Ltd. (CCECC)›› የተባለው ድርጅት፣ ከሦስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ግንባታውን ለማከናወን ከተመረጠው ኮንትራክተር ጋር በቅርቡ ውል መፈጸሙን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

‹‹CCECC›› ከዚህ ቀደም የተለያዩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፣ ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ገንብቷል፡፡

የቻይናው ‹‹CCECC›› ኮንትራክተር ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ሠርቶ የማያውቅ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መስፍን፣ ያለውን የሥራ ልምዶች መሠረት በማድረግ የተመረጠ ነው ብለዋል፡፡

ከድርጅቱ ጋር ሲወዳደሩ የነበሩት ሌሎች ሦስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ‹‹CCCC, AVIC International Holding Corporation›› እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤትን የገነባው ‹‹China State Construction Engineering Corporation›› ተሳታፊ እንደነበሩ የአየር መንገዱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አዲስ የሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት ስድስት ወለሎች፣ ሁለት ቤዝመንትና የመኪና ማቆሚያ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመግለጫው እየተገባደደ በሚገኘው በጀት ዓመት 6.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ጨምሮ አስታወቋል።

በበጀት ዓመቱ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ተፅዕኖና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የአቪዬሽን ዘርፍ ፈተና ሆነው መቆየታቸውን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ የዘንድሮ የገቢ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

በበጀት ዓመቱ 13.7 ሚሊዮን መንገደኞችንና በጭነት ረገድ ደግሞ 723 ሺሕ ቶን ማጓጓዙንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ አየር መንገዱ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ዳግም ካስጀመራቸው በረራዎች በተጨማሪ ሰባት አዳዲስ የመዳረሻ ጣቢያ ተከፍተዋል ተብሏል፡፡

12 አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመግዛትም አጠቃላይ የአውሮፕላን ብዛት ከ140 በላይ ማሳደጉን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የደንበኞች አገልግሎትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፣ በአየር መንገዱ የጥገናና ምሕንድስና ማዕከል ከመንገደኛ ወደ ጭነት አገልግሎት ሰጪነት የተቀየሩ ሁለት አውሮፕላኖች የካርጎ ሥራ መጀመራቸውንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች