በግንቦት ወር የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 30.8 በመቶ ሆኖ እንደተመዘገበ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡
በሪፖርቱ እንደተመላከተው በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 30.8 ከመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በሚያዚያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.5 ከመቶ ደርሶ ነበር።
በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. የተመዘገበው የአጠቃላይ፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት መጠን ላይ መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የዋጋ የመጨመር ፍጥነት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በትንሹ ቀንሷል የሚለውን የሚያመለክት መሆኑ ተገልጿል።
ያለፈው ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 28.5 ከመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ34.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አገልግሎቱ ይፋ አድርጓል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በተጠናቀቀው የግንቦት ወር አንዳንድ አህሎች፣ ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና በቆሎ አነስተኛ የዋጋ ቅናሽ አስመዝግበዋል፡፡ በተጨማሪም ቅባትና የምግብ ዘይት ዋጋ በመጠኑ ቀንሷል። ነገር ግን ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ድንችና ሥራ ስሮች፣ ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላልም መጠነኛ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆነ የኢንዴክሱ ክፍሎች ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የአሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ መጠነኛ የሚባል ቅናሽ መታየቱን የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡
በወርኃ ግንቦት ምግብ ነክ ያልሆኑ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰጌጫዎች፣ ነዳጅ፣ የሕክምና መሳሪያዎችና ጌጣጌጥ የዋጋ ለውጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም ደረጃ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸው አሥር አገሮች ተርታ ውስጥ የተመደበች ሲሆን፣ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስቱ በርዕሰ ጉዳዩ ተጠቃሽ አገሮች ውስጥ አንዷ መሆኑን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥር 2014 ዓ.ም. አንስቶ ከሰላሳ ቤቶች ውስጥ ዝቅ አለማለቱን ሪፖርተር የተመለከተው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ገላጭ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የዋጋ ግሽበት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መካከል ዋነኛው መሆኑን በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤቱና ገዥው ፓርቲ በሚያደርጋቸው የዕቅድ አፈጻጸም መድረኮች በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚያስረዱት፣ የዋጋ ንረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁንም የሸማቾች መሠረታዊ ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍላጎትን ያገናዘበ በቂ ምርት ኖረም አልኖረም በዘፈቀደ በምርቶችና በሸቀጦች ላይ የሚጫን ዋጋ ገበያው እንዳይረጋጋ አድርጎታል በማለት ይጠቅሳሉ፡፡