Tuesday, September 26, 2023

የመንግሥት በጀት ቅነሳ ተፅዕኖዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት መንግሥት ከመጠን በላይ ያሰፋውን ወጪ እንዲቆጥብ በዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለብዙ ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት በጀት ስትመድብ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ እነሆ ዘንድሮ ስለበጀት ቅነሳና ወጪ ቁጠባ መነጋገር መጀመሯ አዲስ ነገር ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

ለአብነት ያህል በ2011 ዓ.ም. ወደ 346.9 ቢሊዮን ብር በጀት ነበር ኢትዮጵያ የመደበችው፡፡ በጊዜው 287 ቢሊዮን ብር ከታክስ፣ ከዕርዳታና ብድር ይገኛል ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ በጀቱ 59 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳለበት ተነግሮም ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ባለሥልጣናት ያም ቢሆን በጀቱ ከቀደመው ዓመት ጉልህ ብልጫ እንዳለው ሲከራከሩ ተደምጠው ነበር፡፡

የ2011 ዓ.ም. በጀት ከ2010 ዓ.ም. በጀት የ3.6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡንና ይህም የ12 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያለው መሆኑን መንግሥት ገልጾ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በአገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ያለና የታክስ አሰባሰቡ ያላደገ ቢሆንም፣ የወጪ ምርት አፈጻጸም ደካማ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን በተቻለው መጠን የተሻለ በጀት መመደቡን ለማሳመን ጥረት አድርጎ ነበር፡፡

ለ2013 ዓ.ም. ደግሞ ለካፒታል፣ ለክልሎች ድጎማና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በድምሩ 476 ቢሊዮን ብር መመደቡን ይፋ ያደረገው መንግሥት በተነፃፃሪነት ከቀደሙት ዓመታት ትርጉም ያለው ጭማሪ ያሳየ በጀት ስለመመደቡ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ከዚያ በጀት 350 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢዎች ሰብስቦ ለመሙላት ማቀዱን ተናግሮ ነበር፡፡

የ2011 ዓ.ም. በጀት ሲፀድቅ ከውጭ ብድር የማግኘት ችግር እየገጠመው ስለመሆኑ ተናግሮ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም የወጪ ንግድ ገቢ መቀነስ፣ የሃዋላ ገቢ መውረድ፣ የኢንቨስትመንት መቀነስ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም የሰላምና መረጋጋት ዕጦት እየተባለ ለበጀት ዕድገት ጎታች ምክንያቶች ተብለው ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አገሪቱ እያለፈችም ቢሆን፣ መንግሥት በየዓመቱ ጉልህ ጭማሪ ያለው በጀት ነበር ሲመድብ የቆየው፡፡

ዘንድሮ የ2016 ዓ.ም. በጀት ይፋ ሲደረግ ግን የወጪ ቁጠባ ጉዳይ ነበር በጉልህ የተነሳው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሰኔ 1 ቀን 2015 የበጀት ረቂቅ ዕቅዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ይህን በይፋ አስተጋብተውታል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የተትረፈረፈ በጀት ወይም የተጋነነ ወጪ እንደማይኖር አበክረው ተናግረዋል፡፡

‹‹የፋይናንስ እጥረቱ ሁሉንም የወጪ ፍላጎቶቻችንን ለመሸፈን የማያስችል ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተጀመሩ የካፒታል በጀት ፕሮጀክቶች ሊታጠፉ (ሊቋረጡ) ይችላሉ ነበር ያሉት፡፡ የክፍያ ጊዜ ማሸጋሸግና የበጀት ቅነሳ ማድረግንም በአማራጭነት አውስተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ማለትም ባለፉት 20 ዓመታት ከዓመት ዓመት ሲሰፋና ሲለጠጥ የመጣው የመንግሥት በጀት ፍሰት በምን መንገድ ጉድለቱ ሲሞላ ከረመ የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁን በምን አስገዳጅነት ነው መንግሥት ስለቁጠባና በጀት ቅነሳ ወደ መናገር የገባው የሚል ጥያቄም ይከተላል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያውና ፖለቲካኛው አቶ ግርማ ሰይፉ ይህ የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የዋጋ ንረትና ግሽበት እጅግ እየፈተነው የሚገኝ አገር ወጪን ያዝ ማድረጉ የተመለመደ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መንግሥት ወጪውን መቀነስ የፈለገ ይመስለኛል፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመንግሥት በጀት ቢጨምርም ሆነ ቢቀንስም አብዛኛው ለመልሶ ግንባታና ማቋቋሚያ እንደሚውል ይገምታሉ፡፡ ‹‹በጦርነት ውስጥ የከረመ ኢኮኖሚ ነው ያለው፡፡ መንግሥት የሚመድበው በጀትም ቢሆን አብላጫው ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራዎች እንጂ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል የተትረፈረፈ በጀት እንደሌላው ጊዜ የለም፤›› ይላሉ፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ተንታኝ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ቅናሽ የተመዘገበባቸውን የበጀት ዘርፎች በዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡ ከቅናሾቹ ትልቁ ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት ተከታታይ ጭማሪ እያሳየ በመጣው የካፒታል በጀት ላይ የታየው ቅናሽ ዋናው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ለአዲሱ በጀት ዓመት ለካፒታል ወጪ 203.9 ቢሊዮን ብር ነው የተመደበው፡፡ ይህ ደግሞ ለ2015 ዓ.ም. ከተመደበው 218.11 ቢሊዮን ብር አንፃር በ6.51 በመቶ የቀነሰ ነው፤›› በማለት አነፃፅረውታል፡፡

በአጠቃላይ ለ2016 ዓ.ም. የተመደበው በጀት 801.6 ቢሊዮን ብር በ2015 ዓ.ም. ተመድቦ ከነበረው የ786.6 ቢሊዮን ብር በጀት ጋር ሲነፃፀር የ1.9 በመቶ ብቻ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የጠቀሱ ወገኖች፣ ይህ ኢኮኖሚውን የማያነቃቃ መሆኑን ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ አለመላቀቋን የሚናገሩ ደግሞ፣ ከዚያ ቀደም የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት ተፋዞ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ተከታታይ ግጭቶችና ከባድ ጦርነት አገሪቱ ማስተናገዷን በማስታወስ፣ አገሪቱ ከዚህ የዞረ ድምር ተላቃ የተነቃቃ ዕድገት እንድትፈጥር የሚያስችል የበጀት ምደባ ሊኖራት ይገባ እንደነበር ያሳስባሉ፡፡

ለ2016 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ 369.6 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል 203.9 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች ድጎማ 214.07 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ይፋ ሆኗል፡፡ በዓመቱ ኢኮኖሚው የ7.9 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብም መንግሥት ትንበያውን ይፋ አድርጓል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ዘንድሮ ለመሰብሰብ ያቀደው 520.6 ቢሊዮን ብር ገቢ ቢሆንም፣ ካቀደው በታች 440.8 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ለ2016 ዓ.ም. የቀረበው የ801 ቢሊዮን ብር በጀት የ281 ቢሊዮን ብር ጉድለት ያለበት እንደሆነ ነው መንግሥት የተናገረው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ይህ ሁሉ የበጀት ጉድለት ከየት መጥቶ ሊሞላ ነው የሚል ሥጋት አለ፡፡  

የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የውጭ የገንዘብ ምንጮችን ማማተር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ ጦርነት ውስጥ እንደከረመችና ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ጨምሮ ኦሮሚያም ቢሆን አስተማማኝ ሰላም አጥተው መዝለቃቸውን ያስረዳሉ፡፡ በትንሹ ከአገሪቱ አንድ – አራተኛ የሚሆን መሬትና ሕዝብ ያቀፉ አካባቢዎች ምርትም ሆነ ገቢ ሳይሰበሰብባቸው መዝለቁን ኢኮኖሚስቱ ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የውጭ የገንዘብ ምንጮችን ማማተር የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት አስፈላጊ መሆኑን ነው የሚያስቀምጡት፡፡

‹‹የውጭ አበዳሪዎችና ዕርዳታ ሰጪዎች በትንሹ በዓመት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚሰጡን ናቸው፡፡ ይህ ቀላል ጉድለት አይሸፍንም፡፡ ከእነሱ ጋር ያለውን ልዩነት ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በሃዋላ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲገኝ የሚያደርጉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የብርን የመግዛት አቅም ብናወርደው በትንሹ ዳያስፖራው ከ10 እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር ሊልክ ይችላል የሚል ግምት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ አማራጮችን መውሰድ ካልቻለ ብር በማተም የበጀት ጉድለቱን ወደ መሙላት እንደሚገባ ነው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ምልከታቸውን የሚያጋሩት፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ የበጀት ረቂቁን ሲያቀርቡ የገንዘብ የማተም አማራጭ (የቀጥታ ብድርን) መንግሥታቸው ለመቀነስ ማሰቡን ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡ የበጀት ጉድለቱን መንግሥት ጤናማ ማለቱ ደግሞ ለዚህ መነሻ ነው ይላሉ፡፡

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ጤናማ ነው ብሎ ለማስቀመጥ የበጀት አኃዙን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታማነት ጋር ብቻ ተነፃፃሪ አድርጎ ማስቀመጥ እንደሌለበት አቶ ግርማ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የበጀት ጉድለቱ ጤናማ ነው ወይም አይደለም ሊባል የሚችለው፣ ከአጠቃላይ ምርት በተጨማሪ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበትና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ጋር መሆኑንና በሌላ በኩልም የነበርንበት የጦርነት ሁኔታ መታየት አለበት፡፡ ምርት ሳይኖር ፍላጎትና ፍጆታ ብቻ የነበረበት ጊዜ አሳልፈናል፤›› በማለትም ያብራራሉ፡፡

‹‹መንግሥት ስትሆን ጠብመንጃ፣ ታንክና አውሮፕላን ከመታጠቅ በተጨማሪ ያለህ ሌላ ሥልጣን ገንዘብ ማተም ነው፡፡ የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት በሚል ለአጠቃላይ ምርታማነት አንዳችም አስተዋጽኦ የሌለው ብር እያተሙ የትሪሊዮን ብር በጀት ዕቅድ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህንን ግን አላደረጉም፡፡ አሁን የተመደበው በጀት ጉድለት ቢኖረውም በቶሎ ውጤታማና ምርታማ በሆኑ መስኮች ላይ በመመደብ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው እላለሁ፤›› በማለት አቶ ግርማ አክለዋል፡፡

የበጀት ጉድለትን ከመሸፈን ጉዳይ ሌላ በተመደበው በጀት አዳዲስ የሥራ ዕድል የመፍጠር ጥያቄም በጉልህ እየተነሳ ነው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ‹‹ወጣቱ ሥራ ይፈልጋል፡፡ አገር ከድህነት የምትወጣበት ብቸኛ መንገድ ሥራ ፈጠራ ነው፤›› በማለት በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ዋዜማ በመስቀል አደባባይ፣ ‹‹ሥራ አጥ እንጂ አደገኛ ቦዘኔ የሚባል ወጣት የለም፤›› የሚል መፈክር እያሰማ ቅንጅትና ኅብረትን ለመደገፍ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ፣ ፓርቲያቸው ኢሕአዴግን በምርጫው  ዕለት በደንብ እንደቀጣው አቶ መለስ ከዚያ አጋጣሚ የተማሩ ይመስል ነበር፡፡

ለዚህ ነበር አቶ መለስ ሚሊኒየም አዳራሽ ለሰበሰቧቸው ወጣቶች ‹ሥራ ፈጠራ ነው የሚያስፈልጋችሁ› ሲሉ የተናገሩት፡፡

ከሰሞኑ የ2016 ዓ.ም. በጀት ዕቅድ ሲቀርብ ግን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ የሥራ ፈጠራ ጉዳይ መንግሥታቸው እንደማይመለከተው መናገራቸው ዋና መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋና አንቀሳቃሽ መንግሥት በሆነባቸው አገሮች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይን መንግሥት አይመለከተኝም ማለት የሚችልበት ዕድል እንደሌለ የጠቀሱ አንዳንድ ወገኖች፣ ሥራ መፍጠር አንዱ ግዴታው መሆኑን እየተሟገቱ ነው፡፡

ይህን በሚመለከት አስተያየት የሰጡት አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ መንግሥት ቀጣሪ መሆን እንደሌለበት ነው የተናገሩት፡፡

‹‹መንግሥት አሁን ያሉትን ሠራተኞች ውጤታማነት በመጨመር የሠራተኛ ቁጥሩን ቢቀንስና በዚህም የአገሪቱን የመደበኛ በጀት ወጪ ቢቀንስ የተሻለ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ግርማ እንደሚሉት የመንግሥት ዋና ሥራ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ቁጥር መጨመር ሳይሆን የግሉ ዘርፍ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን እንዲፈጥር ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡

ይህ የሥራ ፈጠራ ጉዳይ ያሳሰባቸው የሚመስሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግን በጀቱ ተረቆ በቀረበበት ወቅት ጉዳዩ እንዲታሰብበት አሳስበው ነበር፡፡ በጀቱ በትክክል ድህነት ተኮር ልማቶችና የሥራ ዕድል ፈጠራዎች ላይ መዋል እንዳለበት ያሳሰቡ አንድ የምክር ቤት አባል፣ የካፒታል በጀት ጭምር ለቢሮ ማስዋብና ቀለም መቀባት ዓይነት ሥራዎች መዋሉ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የበጀት አመዳደቡ አላስፈላጊ ወጪዎች፣ ብክነትና በቂ የገቢ አሰባሰብን ያላማከለ መሆኑን የምክር ቤት አባሉ ተችተዋል፣ በወጪ ጉዳይ መንግሥት እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ሥራ የመፍጠር ግዴታ ያለበት መሆኑንንም በተለያዩ መንገዶች አውስተዋል፡፡

ከሥራ ፈጠራና ከበጀት አጠቃቀም በተጨማሪ የአንዳንድ አካባቢዎች በጀት ድጎማ ጉዳይ በአሳሳቢነት ተነስቷል፡፡ በፓርላማው እንደተገለጸው በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች በጀት አልቆ ከቀጣዩ ዓመት በብድር እየተጠቀሙ ነው ተብሏል፡፡

በአንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ደመወዝ ለመክፈል ራሱ ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተነስቷል፡፡ ለሁለትና ለሦስት ወራት ያለ ደመወዝ መኖር አሳሳቢ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ መንግሥት ደረጃ በደረጃ የአንዳንድ አካባቢዎችን የዕዳ ሸክም ለመቀነስ እንዲሞከርም ተጠይቋል፡፡

መንግሥት ድህነት ቅነሳና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የበጀት አመዳደብ ያስፈልገዋል የሚሉ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ እንደ መንገድ ያሉ ሁለቱንም ሊያሟሉ የሚችሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በጀት አባካኝ ሆነው የቆዩ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለአብነት የመስኖ ልማት ሥራዎች እንዲታዩ ተጠይቋል፡፡ ዘላቂ ልማት ትኩረት ይሰጠው ሲባል የትኞቹ ናቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሥራዎች የሚለው ተነስቷል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከናወኑ የሚባሉ ግንባታዎች በጀት ግልጽነትም ጥያቄ የተነሳበት ሲሆን በኢትዮጵያ የተፈናቀሉ፣ ለድርቅና ለሌላም ማኅበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ዜጎች ብዙ ሆነው ሳለ የመንግሥት ወጪና በጀት አመዳደብ ጉዳይ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባው ነው ማሳሰቢያ የቀረበው፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -