Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከአፍ ነጣቂዎች!

የዛሬው ጉዞ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ነው፡፡ ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስነንት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው ‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም› እያለ እጁን ሰጥቶና አንገቱን ደፍቶ ይኖራል። ስለደጉ ጊዜ ይዘምራል፡፡ ክፉውን ይኮንናል። ጊዜን የቀደመው ደግሞ በእጆቹ ሥራ ኮርቶ ይጀግናል፡፡ አንዳንዱም ሰው ከማያየው ህሊናው ጋር እንደተሟገተ ‹የፍጥነት እንጂ የጊዜ ጀግና የለውም ያለው ሳይቲስት ለዘለዓለም ይኑር› እያለ በወኔ ይጣደፋል። በመሀል በጊዜም በፍጥነትም ነገር ያልገባው፣ ቀኔም ውሎዬም ስሜም እኔም እንደተጻፈልኝ እንጂ እንደምጽፈው የምኖረው አይደለም በሚል ስሜት፣ የሚያየውንና የማያየውን ለታላቁ አምላክ ፈቃድ አስገዝቶ ውረድ ሲሉት ይወርዳል፣ ተሳፈር ሲሉት ይሳፈራል። አይስቅም፣ አያለቅስም፣ አይደሰትም፣ አያዝንም። ይህም እንደተጻፈለት እንጂ እንደጻፈው አይደለምና። ከላይ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች አልፎ አልፎ ደመና፣ አልፎ አልፎ ብርሃን፣ አልፎ አልፎ ጨለማ፣ ከአልፎ አልፎዎቹ በታች ተራራ፣ ወንዝ፣ ባህርና የብስ አለ። በወንዞቹ፣ በተራራዎቹ፣ በየብሳቱ መካከል ክልልና ኬላ፣ ከተማና ገጠር፣ ቀበሌና መንደር አሉ። አንዳንዱ የተጨናነቀ፣ አንዳንዱ ነፃ የሆነ መንገድ መኖሩ ሳይዘነጋ። አንዳንዱ ሕይወት፣ ትዳር፣ እምነት፣ ፅናት የሚያፈርስ ሌላው የልኬቱን ብቻ ታሪፍ የሚቀበል ጎዳና። ከእዚህ ጎዳና በአንዱ እንደ አበቃቀላችንና ኑሯችን የማናምን ተሰብስበን ታክሲ ይዘናል። ተሳፍረናል ለማለት ነው!

አቀማመጣችን በሒሳባዊ ቀመር መገለጽ ቢችል ወይም ባይችል የማንደነግጥ የማንደመም፣ ብቻ ወያላው ‹ዛሬ ሒሳብ በእኔ ነው› ቢለን ጮቤ የምንረግጥ ታካች መንገደኞች ነን። በቅርበትና በርቀት ከአዕምሮአችን በላይ በሆኑ ጥበቦችና ሐሳቦች ከተሠራው ዓለማችን በላይ ተጋፍተን ወንበር መያዛችን የሚያስፈነድቀን ምስኪን የሕይወት እስረኞች ነን። መንገድ የሌለበት የለምና ከደመናው በላይ ባንጓዝ ከደመናው በታችን መጓዝ አላቋረጥም። መንገድ ውሎ ይግባና፡፡ ‹‹ሾፌር ንዳዋ ጊዜያችንን ገደልከው እኮ…›› ጋቢና የተቀመጠ ወጣት ሾፌራችንን ይጠዘጥዘዋል። ‹‹ምን ጊዜ አለ ደግሞ እዚህ አገር?›› አለው ከጎኑ የተቀመጠ ሌላ ተሳፈሪ። ‹‹እንዴት?›› ግራ ተጋብቶ ዞሮ አየው። ሾፌሩ ወያላውን እየጠቀሰ ትርፍ እንዲጭን ያበረታታዋል። ‹‹ኧረ ተወኝ አንዳችንም የለንም…›› መለሰ ‹ምን ጊዜ አለ› ባዩ። ‹‹ከማንና ከማን?›› ጠየቀው የቸኮለው ወጣት። ‹‹ከጊዜና ከእኛ አንዳችን እዚህ አገር ላይ የለንም ብዬ ነው የማምነው…›› አለው ኮስተር ብሎ ሐሳቡን ለምጡቅ የፊዚክስ ፕሮፌሰር እንደሚያቀርብ  ታታሪ ተማሪ። ‹‹ታዲያ እንደ እሱ አትለኝም። መጀመርያውኑም ‹ብዬ ነው የማምነው› ብለህ ሐሳብህን አቅርበህ ቢሆን ኖሮ ይኼው ገና አሁን ቁርሴን በልቼ ከመውጣቴ ደንግጨ ረሃብ አይሰማኝም ነበር…›› አለ በጎን ሾፌሩን እንሂድ እያለ እየወተወተው። ተጀመረ ማለት ነው!

‹‹አልገባኝም…›› አለው ደግሞ በተራው ያኛው ግራ ተጋብቶ። ‹‹ጊዜ የሚባል ነገር እኛ ዘንድ የለም አልክ። ቀጠልክና ወይ እኛ ወይ እሱ አንዳችን የለንም አልከኝ። ማስረጃ ያለህ መስሎኝ ደግሞ ምን ተዓምር አመለጠኝ ብዬ እህ ብዬ ሳዳምጥም አገር፣ ጊዜና ሕዝብ የመገነጣጠል መላምታዊ ሐሳብህ በእምነት ላይ እንደተመሠረተ ነገርከኝ። እንኳን በተጨበጠ የፍጥረት ሕግና ቁጥር ላይ አልተመሠረተ እንጂ፣ በሐሳብና በእምነት ላይ የተመሠረተ የመነጠልና የመገንጠል ቲዮሪ ፍርኃት እንደሆነ ለቆናል…›› እያለ ይባስ ግራ አጋባው። ‹‹ማነው ስለአንቀጽ 39 የሚያወራው?›› ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ሳቂታ ሰውዬ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹ምናለበት አንቀጽ መቁጠሩን ትታችሁ ዕድሜያችሁን ብትቆጡሩ? አዳሜ ከ39 ዓመት በላይ መኖር በማይችልበት አገር አሁንም አንቀጹ ላይ ነው?›› ብላ ከሰውዬው አጠገብ የተሰየመች ወጣት ሳቀች። እንዲያው የአንዳንዱን ሳቅ ዓይነት ለመግለጽ የሆነ የሳቅ መለኪያ ‹ዩኒት› በኖረ ያስብላል፡፡  አንዳንዴ!

ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ ያከፋፍላል። መጨረሻ ወንበር የተየሰመ ወጣት ስለሰብዓዊነት ይተረተራል። ‹‹ሌላው ቢቀር የዕርዳታ እህል ዘርፋችሁ እየበላችሁ ነው ስንባል አናፍርም?›› አለ። ‹‹እኛ የት አግኝተን ዘርፈን ነው የምናፍረው?›› አለች ከመሀል መቀመጫ ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ ቆይ ተይው፣ ዓይጥ በበላ ዳዋ ተመታ አሉ፡፡ ለመሆኑ እዚያው ሄደህ ዘራፊዎቹን አታናግራቸውም፡፡ እኛ በምን ዕዳችን ነው ከሌባ ጋር ስማችን የሚነሳው…›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመው ጎልማሳ አፈጠጠበት። ‹‹በሉ… በሉ… እርስ በርስ ተፋጅተን ገና ሳይበርድልን፣ ፈረንጅ የሰጠንን የዕርዳታ ምግብ እየዘረፉ ነው ከተባልንማ የዓድዋ ጀግኖች አፅም ይውቀሰን ከማለት ሌላ ምን ይባላል?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ካነሳችሁትስ አይቀር ለዚህ ወንጀላችን ንስሐ መግባት ይኖርብናል…›› ብሎ ሌላው ዙሩን አከረረው። ‹‹ሌቦቹ እያሉ እንዴት እኛ ንስሐ እንገባለን?›› በማለት አንድ ወጣት ሲጠይቀው፣ ‹‹ታጥቦ የማይጠራው በዝቷላ። ተነግሮት የማይለወጠው፣ ተመክሮ የማይሰማው፣ ተለምኖ የማይራራው እኮ ነው መንገዱን አጓጉል እያደረገ ፍዳችንን የሚያሳየን። ዛሬ ብንነቃ ነገ ፈዘን እንውላለን። እውነቱና ሀቁ እዚህ አፍንጫችን ሥር ተኝቶ አናስተውለውም። ዘራፊው አጠገባችን እየበላ እየጠጣ ቆይቶ ጋባዥ እኛው ነን። እንዲያው በአጠቃላይ ተበለሻሽተናል እኮ?›› ብሎ ሲያበቃ፣ ለጊዜው ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ትንፋሽ ያስፈልጋል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች መካከል ስለሰብዓዊነትና ስለመተዛዘን ሲሰብክ የነበረው ሰሜን ማዘጋጃ ጫፍ ላይ ወራጅ ብሎ አስቆመን። እየወረደ እያለ መሀል መቀመጫ በአነጋገር ዘዬዋና በቀናነቱዋ ቀልባችንን ስትስብ የቆየች አንዲት ምስኪን፣ ‹‹አንተ ወንድሜ ፈጣሪ ይከተልህ፣ ልብህ ንፁህ በመሆኑ ነው ይህንን አሳዛኝ ጉዳይ አንስተህ ራሳችንን እንድንመረምር ያደረግከን…›› ስትለው፣ ‹‹አንቺም እኮ ልብሽ ንፁህ ስለሆነ ነው ምግባረ ብልሹዎችን በመቃወም ድምፅሽን ያሰማሽው…›› ብሎ ተሰናበተን፡፡ ታክሲዋ ጉዞዋን ስትቀጥል በነበረው አፍታ ስለአስመራሪው የኑሮ ውድነት፣ ስለተደራራቢው ሰሞነኛ የግብር ዕዳ፣ ስለሚቀጥለው ዓመት ከፍተኛ ጉድለት ስላለበት በጀት፣ ስለዜጎች የተለያዩ እሮሮዎችና ምሬቶች ከየአቅጣጫው ብዙ ነገሮች ተነሱ፡፡ ሁሉም አጠገብ ከተቀመጠው ጋር ሲንሾካሸክ ሾፌርና ወያላ በየቀኑ የሚሰሙት የብሶት ወሬ የታከታቸው ይመስሉ ነበር፡፡ ሾፌሩ ፊቱን ከስክሶ በተጣበበው ጎዳና ላይ ሲያሽከረክር፣ ወያላው ደግሞ በመስኮት አንገቱን ወደ ውጭ አድርጎ ከእንጦጦ አቅጣጫ ሽው የሚለውን ንፋስ በአፍንጫው እየማገ ነበር፡፡ ይሰለቻል እኮ!

‹‹ካወራን አይበቃም ብለሽ ነው። ዘመኑ እኮ የወሬ እንጂ የተግባር አይደለም። ከማን አንሼ ‹በቶክ› ሆኗል። እንጂ ሥራ ድሮ ቀረ…›› እያለ አንዱ አጠገቡ ከተሰየመው ጋር ሲነጋገር፣ ‹‹ያም ሆነ ይህ ቃል የእምነት ዕዳ ነው። መቼም ልናበዛው፣ ልናሳንሰው እንችላለን እንጂ ምንም ነገር እንዲያው ሳናምንበት አናወራም። አይደለም እንዴ?›› ሲለው ጎልማሳው ከፊት፣ ‹‹ዘንድሮ ሰው ከራሱ ከልቡ ሳይሆን ከፌስቡክና ከዩቲብ የቃረመውን ነው የሚለፈልፈው። ለዚያም እኮ ነው በተግባር የማያሳየውን ነገር ሲዘባርቁ መዋል የበዛው። ሙስና ይባል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕም ይሁን የዴሞክራሲ ዕጦት የመሳሰሉት አላስኖሩን አሉ እያለን ስንትና ስንት የአገር ሸክም በእኛው በግለሰቦች ደረጃ ሊቃለሉ የሚችሉ እያሉ፣ ወሬያችንና ትችታችን ሲያበቃ ሀሞታችን ይፈሳል። ደግሞ ለሌላ  የቃል የዲስኩር ሐሜትና ትችት አጠራቅመን እንመለሳለን…›› ብሎ ከመጨረሻዎቹ አንዱ የልቡ እስኪደርስ አወራ። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ሲከፍተው፣ ‹‹አትሳሳት ወንድሜ፣ ሌብነት አናታችን ላይ እየጨፈረ የዓለም መሳቂያና መዘባበቻ እያደረገን ስለምን ትችት ነው የምታወራው፡፡ ከደሃ አፍ ተነጥቆ ሀብታም ኪስ የሚገባ ዕርዳታ የዓለሙ መፋረጃ ሲያደርገን፣ ለምንድነው ብሶታችንን ከአፋችን ለመንጠቅ የምትረባረቡት…›› እያለ እየመለሰለት ሳለ ወርደን ወደ ጉዳዮቻችን ማምራት ጀመርን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት