Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ይህችን ማስታወሻ የምልክልዎት ግለሰብ ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ አቀንቃኝ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የአገሬ ጉዳይ ስለሚያሳስበኝ የሚሰማኝን ስሜት በአክብሮት ለማሳሰብ ነው፡፡ ከመሰለዎት አንድም ይሁን ሁለት ይጠቅማል የሚሉትን ከአስተያየቴ ውስጥ መርጠው ቢወስዱና ቢያመዛዝኑት ብዬ በድፍረት ይህችን ማስታወሻ ስልክልዎት በታላቅ አክብሮት ነው።                                                                      

እኔ ነዋሪነቴ በአሜሪካ ሲሆን የትውልድ አገሬን እንደ ማንም ሰው ባለማና ብረዳ ጥሩ ነው ብዬ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ብዙ ከለፋሁ በኋላ፣ ከሚገባው በላይ የአስተዳደር ችግርና የጉቦ መፈልፈያ ኢንኩቤተር መስሎ በተፈጠረው አዲሱ አስተዳደር ምንም መሥራት ባለመቻሌ፣ ምናልባት ሁኔታዎች ሲለወጡ ለመመለስ ወስኜ ወደ ነበርኩበት አገር ተመልሻለሁ። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት የአገሬን ችግር መካፈል ፈርቼ ሳይሆን፣ ክቡርነትዎ ከ60 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ሰው ምንም እንደማያውቅና ለጡረታ ብቻ የተቀመጠ ነው ብለው ስለሚያስቡ፣ ዕውቀታችንን ለማካፈል ካልቻልን ምን ፋይዳ ይኖረናል በማለት ነው፡፡ ባለሁበት አገር ለሞት እንኳ የተቃረበ አዛውንት ዋጋ ስለሚሰጠው ወደ እዚህ አመራሁ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዴት እንደተቀበለዎትና እንደተደሰተ ያስታውሱታል፡፡ በሚገባ አይተውታልም ብዬ እገምታለሁ። ይህንን ሁኔታ ሳይውል ሳያድር እንዲቀለበስ አደረጉት፡፡ ይህንንም አልተገነዘቡም ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም የፀጥታንና የሰላምን ጉዳይ ከማንም በበለጠ  ስለሚያውቁት፡፡ ይህ ጉዳይ ከእርስዎ ጆሮ ይርቃል ብዬ ስላላሰብኩኝ ነው።                  አንድ ሰው የአገር መሪ ሲሆን የራሱ ሰው ከመሆን ወጥቶ የሚያስተዳድረው ሕዝብ ንብረት ይሆናል ይላሉ አሜሪካኖች፡፡ ክቡርነትዎም የሕዝቡ አለኝታና መመኪያ በመሆን ዓለምን ሊያስደንቁ የተፈጠሩ ሰው መስለው፣ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ወዳጅም ባይኖራት የኢትዮጵያ ወዳጅ ነን ባዮችን ሁሉ አስደምመው ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል? ውሎ ሳያድር ሁኔታዎች ሁሉ መቀየር ጀመሩ፡፡ ወገን በወገኑ ላይ አደጋ ሲጥል የየክልሉ ገዥዎች ነገሩን ይመልከቱ በሚል መንገድ አንዱ አንዱን ሲገድል በዝምታ ማለፍን መረጡ፡፡ ካሊፎርኒያ፣ ሲያትል ዋሽንግተን ወይም ቨርጂኒያ በሕዝብ ላይ መከራ ቢደርስ የፌዴራሉ መንግሥት ለሚመለከተው ስቴት የአስተዳደር ኃላፊነቱን ትቶ በዝምታ አይመለከትም፡፡ ለሁሉም ወሰን አለውና፡፡

ክቡርነትዎ አነሳስዎ እጅግ የሚገርምና የሚያስደንቅ ቢሆንም በቀላሉ እንዲሸረሸር አደረጉት፡፡ ለምን? በማወቅ ወይስ ባለማወቅ? ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለውን የአባቶች ምሳሌ ይመልከቱ። በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ›› በሚል ርዕስ ከአንድ ዓመት በፊት ጽፌ ያወጣሁትን ጽሑፍ እንደገና ቢመለከቱ መልካም ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ጊዜ እንደሌለዎት አውቃለሁ። በዓለም ላይ በታላቅ መሪነት ስምዎ እንዲነሳ የሚያስችለውን ዕድልዎን በመካሪ ማጣት ያጡት ይመስለኛል፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር ባይ ነውና ወደ ልቦናዎ ተመልሰው ይቅር በሉኝ ብለው፣ በብሔርኝነት የተሰማሩ የሚያስመስለውን ሁኔታዎን በመለወጥ በኢትዮጵያዊነትና በቀናነት አገርዎን ለማገልገል ቢያተኩሩ የተሻለ ዕድል ሊኖርዎት ይችላልና ወደ ልቦናዎ ይመለሱ።                                                                     

ታላላቅ ሰዎች ከመናገር ይልቅ ማድመጥን ያስቀድማሉ፡፡ ለጥያቄም ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ክቡርነትዎ ግን ስሙኝ እንጂ ልስማችሁን አልታደሉም፡፡ አዳምጡኝ እንጂ ላዳምጣችሁን ጨርሶ የሚያውቁት አይመስልም። በእርግጥ አዋቂ፣ ብልህና የተለየ ተሰጥኦ ሊኖርዎት ይችላል፡፡ ማንም ሰው ካላዳመጠና የአድማጩን ሁኔታ ለመረዳት ካልቻለ በወንፊት ላይ ውኃ የመሥፈር ያህል ነው የሚሆነው፡፡ ‹‹አዎን፣ አዎን›› የሚሉትን ብቻ መከተል መጨረሻው ውድቀት እንዳይሆንብዎት ይጠንቀቁ፡፡ በየትኛውም ዓለም መሪ የነበሩ ሥራቸው የሚሳካላቸው በአማካሪዎቻቸው ጥልቅ ዕውቀትና ችሎታ ጭምር እንጂ፣ በራሳቸው ዕውቀት ብቻ እንዳልሆነም መገንዘብ ያሻዎታል፡፡ አማካሪዎችዎ የአቤት ጌታዬን ፎርሙላ ተከትለው በሹመት ላይ ለመሰንበት ታች ላይ የሚሉ ይመስላሉና ይህ ለዘለቄታው ስለማይበጅዎት በጠንካራና በብልህ አማካሪዎች ቢመሩና ሁሉም ነገር መስመር ይዞ ቢሄድ የተሻለ ይሆንልዎታልና ሳይርቅ በቅርቡ ቢያስቡበት መልካም ነው።

በቋንቋና በብሔር መዘጋጀቱ ወደኋላ ቀርቶ የነበረን የአፍሪካ ሕዝብ የባሰውን ወደኋላ ይጎትት እንደሆን እንጂ ፍሬያማ ስለማያደርግ ያስቡበት።  ምናልባት በዕድሜ ምክንያት አልደረሱ ይሆናል እንጂ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት አማርኛ የአፍሪካ ቋንቋ ይሁን የሚል ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ የየራሳችንን ቋንቋ ለማስተማር ጊዜ ይወስድብንና ከልማት ወደ ኋላ እንዳይጎትተን አሁን ባለው ቋንቋ እየሠራን ወደፊት የአፍሪካን ቋንቋ አማርኛ እናደርጋለን በሚል ስምምነት ነበር የወቅቱ መሪዎች የተለያዩት፡፡ በኋላ እነኛ ለአፍሪካ የማይተኙ ነጮች ያ እንዳይሆን አድርገው ቀልጦ ቀረ። አሁን እኛም 80 ቋንቋዎች ፈጥረን አንዱ ወደ ቀኝ ሲል ሌላው ወደ ግራ እየተባባልን፣ ከኢንዱስትሪና ከቴክኖሎጂ ዕድገት እንድንለያይ መደረጉን ልብ ይሏል።                                                                                                          

የክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳን ሐሳብ ወስደን ወደ ሥራ ብናውለው የተሻለ ይሆናልና ይታሰብበት፡፡ እሳቸው ሐሳባቸውን ለጃንሆይ ያቀረቡት እንዲህ ነበር፡፡ ‹‹አማርኛ ስንል የአንድ ኅብረተሰብ ቋንቋ ብቻ እንዳይመስል ኢትዮጵኛ ብለን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ እናድርግ፤›› ብለው ያቀረቡት ሐሳብ ተደግፎ ወደ ጥቅም ላይ ሊውል ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ሊመራ ሲታሰብ ደርግ በድንገት ደርሶ ሁሉንም አጥፍቶ ጠፋ።                                                                   

ዛሬ አለን አለን የሚሉ ኦሮሞ፣ ትግሬና አማራ ሲራኮቱ ነገ ደግሞ ወላይታው፣ ሀዲያው፣ ሲዳማው፣ ካፋው፣ አርጎባው፣ ናኦው፣ በኔሾውና ሌሎችም ቋንቋዬን ሲሉ ነጭ የተመኘልንን መለያየትና መበታተንን ራሳችን ወጥመድ ውስጥ መግባታችንን መገንዘብ አለብን፡፡ አንዱን ቋንቋ የሁላችን አድርገን የምንጓዝበትን መንገድ ለመቀየስ ሕዝቡን አስተባብረው ለልማት ቢያነሳሱ መልካም ይሆናልና ያስቡበት፡፡                                    

ማንም ሰው ኃላፊ መሆኑን ከእኔ በተሻለ እንደሚያውቁት አልጠራጠርም፡፡ ሁላችንም ወጣቶች ነበርን፣ ወጣትነት ያልፋል፡፡ ግን የማያልፍ መልካም ሥራ ነውና ለመልካም ሥራ መዘጋጀት ሁሌም መልካም ነው። በዓለም ላይ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ እነ አብረሃም ሊንከን፣ ቶማስ ጀፈርሰንና ሐሚልተን አልፈዋል፡፡ ግን ደግሞ ሥራቸው ለዘለዓለም ይኖራልም፡፡ ደግም ይሁን ክፉ እንደ መልኩ  ይኖራልና። የነበረን አጥቶ አዲስ ፈጣሪ ነኝ ለማት ከመሞከር ይልቅ፣ አሻሽሎና ለወገን አትርፎ ማለፍን መገንዘብ የታላቅ ታላቅ ያደርጋልና ያስቡበት፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች የታሪክ አገር አጥፍቶ መጥፋት ለማንም አይበጅምና በቅጡ ይታሰብበት፡፡

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሳይዘዋወሩ አይቀሩም፡፡ ታዲያ ሕፃን አዝላ ረሃብ ለማስታገስ ዳቦ ግዙልኝ የምትል ወጣት አላዩ ይሆን? ይህንንማ ካላዩ ምኑን ኢትዮጵያን መሩ? ዛሬ ከወላይታ የፈለሱ ወጣቶች ትምህርት ቤት ከመሄድና የነገ የኢትዮጵያ አለኝታ ከመሆን ይልቅ፣ በልመናና መንገድ ላይ በመተኛት ጊዜያቸው ሲያልፍ በስፋት ይታያሉ፡፡ የዕለት ምግባቸውን ዳቦ መግዣ ስጡኝ እያሉ ሲለምኑ በመንግሥት ከትንሽ ቢሮ እስከ ታላላቅ ቢሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ላንድክሩዘሮች ተገትረው ስናይ ለእነዚህ ቆመው ለሚውሉ መኪኖች የሚከፈለው የሾፌር ደመወዝ፣ የባለጊዜ ልጆች ትምህርት  ቤት ማመላለሻ ልዩ መኪናና ለቤንዚን የሚወጣው ገንዘብ ጠላት ፋሽስት ጣሊያን ካደረገብን የከፋ የግፍ ግፍ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ይህንንም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቁጥጥር ቢደረግበት መልካም ነው።

ክቡርነትዎ ለምኜ ባመጣሁት ገንዘብ ማንም ሊጠይቀኝ አይችልም ይላሉ፡፡ ልመናው በማን ስም ነው? በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወይስ በኢትዮጵያ ስም? ባለዕዳው ኢትዮጵያ መሆኗን የዘነጉት ይመስላልና ወደ ኋላ መለስ ብለው የአፄ ኃይለ ሥላሴን ታሪክ ይመልከቱ፡፡ የዓለም ባንክ አዲስ አበባ ይቋቋም ሲሏቸው ምን እንደሚያስከትል ካስጠኑ በኋላ ነው ይቅርብን ያሉት፡፡ ማስረጃ ለሚሻ ጥናቱን ጄኔቫ በመሄድ ወይም አጥኚ ቡድን በመላክ ማረጋገጥ ይቻላል።                                        

መሪ አገርን ያድናል፣ ሊያጠፋም ይችላል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የጀርመን መሪ የነበረው አዶልፍ ሒትለር በጀርመን ላይ ያወረደውን ተውሳክና የጣሊያን መሪ የነበረው ቤኒቶ ሞሶሎኒ በጣሊያን ያስከተለውን የማይረሳ ቀውስ ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ መሪዎች አገርን ያሳድጋሉ፣ ያጠፋሉም፡፡                                                                             ይህ እንዳይሆን በጭሩ ከሕዝብዎ አስተሳሰብ ተለይተው አንድን ዘር ከመበደልና እልህ ውስጥ ገብተው መጨረሻዎ እንዳይበላሽ አሁኑኑ ለማስተካከል ቢሞክሩ ሁላችንም ከእርስዎ ጋር እንቆማለን፡፡ ይህንን ምክሬን በክፉ አይመልከቱት ከሚያሙዎት ጋር ቁጭ ብዬ በወሬ አገር የማሸብር ግለሰብ አይደለሁም፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎም ለመላው ጥቁር ሕዝብ ከልቤ የምቆረቆርና የማስብ ስለሆንኩ ነው ይህንን በግልጽ ላሳስብዎት የተነሳሳሁትና በክፉ አይውሰዱት።                                                              

ሌላው ሳላነሳ የማላልፈው ነገር የሚሾሟቸው ሰዎች የአገር ፍቅር፣ ለሕዝብ የሚያስቡና ችሎታ ያላቸው ናቸው? ወይስ ለመሽቀርቀርና የጊዜውን ሁኔታ ለመጠቀም የተሰባሰቡ? ይህንንም ልብ ማለት ያሻልና ያስቡበት፡፡ አንድ ችግር ተፈጥሮ ችግሩ መፍትሔ ከማግኘቱ በፊት ሌላ ችግር የሚጨምሩ የየክልሉን መሪዎች ልብ ብለው ይሆን? ሕዝባችን በጦርነትና በወገን መለያየት ምክንያት ነገ ምን ይመጣ ይሆን ብሎ ሆድ ብሶት መግቢያ ባጣበት ጊዜ፣ ብዙ አስደንጋጭ ነገሮችን መፍጠር ያረጋጋል? ወይስ ሌላ ተቃዋሚ ይፈጥራል? ምናልባት የተቃዋሚዎች ግራ መጋባት ለአመራር ትንሽ ፋታ የሚሰጥ መስሎ ከታየ አላውቅም፡፡ ግን ችግር፣ መከራና ጠላት እንዳያበዛብዎት ያስቡበት።                               

ለምሳሌ በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የቤት ኪራይና የንብረት ታክስና የመሳሰሉት የሕዝቡን ልቦና አያሸብሩም ብለው ያምናሉ? በእርግጥ መንግሥት ግብር ማግኘት አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ተብሎ ወደ ሕዝቡ ጆሮ ደርሶ፣ ፓርላማው በሚገባ መክሮበትና በስክነት አዎንታዊ ምላሽ በማግኘት የአብዛኛውን ሕዝብ ልቦና አሳምኖ የሚደረግ መሆን ሲገባው፣ የዲክታተሮችን ፀባይ የሚያመላክት በማናለብኝነት የሚካሄድ አሠራር ለአገርም ለመሪም የማይበጅ የጠብ ያለሽ በዳቦ እንዳይሆን ይመከርበት። እኔ ባለቤት ሆኜ ሳይሆን የሚያመጣውን ንትርክና ያላግባብ የሚጠፋውን ጊዜ በማገናዘብ ነው። ማንኛውም ሰው ራሱን አዋቂ አድርጎ ሊገምት ይችላል፡፡ ነገር ግን የሩቅ ተመልካች ሁሉንም ሊያይ ባይችልም ለመገንዘብ አቅም አለውና አይናቅ።

አንድን ታላቅ አገር አስተባብረው ለመምራት ይሞክሩ እንጂ፣ የማይመስል ታሪክ ለመፍጠር ሲሉ የዛሬ 100 ዓመታት ዓብይ የሚባል ሰው የ3,000 ዘመን ታሪክ አለኝ የምትለዋን ኢትዮጵያን አጥፍቶ አለፈ ለመባል ከሆነ የሚሠሩት ይህ አይሳካም፡፡ ይልቁንም ሐሳብዎን ለውጠው ወደ ጥሩ ኢትዮጵያዊነት ቢመለሱና ሕዝቡን አስተባብረው ቢነሱ እጅግ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ እንዳይሳሳቱ በአስቸኳይ ይመለሱ ነው ምክሬ፡፡ የዜጎች ደም ሲፋሰስ ከማየት ይልቅ ዕርቀ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ቢቀይሱ ይሻላል፡፡ ወደ ሰላም ሕዝቡን ለመመለስና ለመምራት ቢያተኩሩ የሚል ምክሬን ስለግስዎት ከእርስዎ በላይ አዋቂ ሆኜ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነት ቁጭትና ስሜት ስለሆነ አደራዎን ሳይቆጡ በትዕግሥት የአዛውንት ምክር ይስሙ። መቼም ልወደድ ባዮች ይህች የተማፅኖ ደብዳቤ እንዳትደርስዎት ያደርጉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ቅንና መልካም አሳቢዎች ሳይኖሩ አይቀሩምና ተማፅኖዬ ትደርስዎታለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከዚህ ቀደም የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘክር ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው                                                                                          assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...