Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አሥር)

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አሥር)

ቀን:

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

‹‹የእንግዳ ውበቱ፣ ሲታይ ነው ባቱ፡፡››

ባለፈው በክፍል ዘጠኝ ባነሳነው የስስት ጉዳይ ላይ ትንሽ መረቅ ማድረግ ሳያስፈልገን አልቀረም – ባላየናቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር…

መጀመርያ ስስትና ንፍግና ያላቸውን ተቀራራቢነትና ልዩነት ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም ለሌላው ለመስጠት ወይም ለማካፈል ዝግጁ አለመሆንን የሚያሳዩ ሲሆን፣ መስገብገብን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ በደረጃ ካየናቸው ግን ስስት የንፍግና ትልቁ ደረጃ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ መስገብገብ አነስተኛ ደረጃን በያዘ ቁጥር ከስስት ሲቆጠር፣ ከፍተኛውን ደረጃ ሲይዝ ደግሞ ከንፍግና ይቆጠራል፡፡

የምግብ እጥረት ባለበት ቤተሰብ ወይም ኅብረተሰብ አካባቢ ከንፉግነት ይልቅ ስስታምነት የአንዳንድ ሰዎች ይበልጥ መገለጫ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ስስት በደሃዎች ወይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች መንደር፣ ንፍግና ደግሞ በሀብታሞች ወይም ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች መንደር የመዘውተር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡  

ስስትና የምግብ እጥረት፣ ስስትና ድህነት የተያያዙ ናቸው፡፡ ‹‹ሁሌም›› ማለት ባይቻልም፣ በአብዛኛው አንዱ ሌላውን የማስከተል ድሉ ሰፊ ነው፡፡ በቂ ነገር ወይም ምግብ እያለው የሚሳሳ ሞልቷል፡፡ ይህን መሰሉን ሰው ከንፍግነት ተርታ መመደቡ ግን ትንሽ ሊያስቸግር ይችላል – በእሱ አዕምሮ በሚለካ የቅርብ ርቀት ውስጥ ችግር ወይም እጥረት ሊደርስብኝ ይችላል በሚል ሥጋት የፈጸመው ሊሆን ስለሚችል፡፡

ሀብት እያለ፣ ለሌላው ለመስጠት አለመፈለግ ከስስት በላይ ነው – ንፉግነት! ‹‹ንፉግ ለግሶ ቢሰጥ እጁ ይንቀጠቀጥ›› መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ለሌላው የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ ባለው ሀብት የራሱን ኑሮ መቀየር ያልቻለ ሰው፣ ‹‹ያለው ደሃ›› የመባሉ ሚስጥርም ይህ ነው፡፡ ንፉግነት በሀብታም ሰው ሥነ ልቦና ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለመረዳት የሚከተለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ማየት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ለንፉግ ሰው የገበያ መንገድ ይጠበዋል››፡፡

በነገራችን ላይ ንፉግነት ባልነበረ፣ በዓለም ላይ ደሃም ሆነ የሚራብ ሰው አይኖርም ነበር፡፡ ዓለማችን በዓመት የምታመርተውን እህልና አሜሪካ ዋጋው እንዲወደድ በማሰብ ውቅያኖስ ውስጥ የምትደፋውን ስንዴ እንተወውና ዓለማችን በቀን ከምታበስለው ምግብ ላይ ሊመገቡት ከሚችሉት በላይ የሚያነሱና የተረፋቸውን የበሰለ ምግብ የሚደፉ ባልነበሩ የሚራቡ ሰዎች ባልኖሩ ወይም ቁጥራቸው በጣም ትንሽ በሆነ ነበር፡፡ ዓለማችን በቀን ከምታበስለው ምግብ ውስጥ ሰውነታቸው ከሚያስፈልገው መጠን በላይ የሚመገቡና ከመጠን በላይ የሚወፍሩ ሰዎች ባልነበሩ፣ የሚራቡና ከልክ በላይ የሚከሱ፣ ከዚያም አልፎ የሚሞቱ ሰዎች ባልነበሩ፡፡ ወይም ቁጥራቸው አነስተኛ በሆነ ነበር፡፡

አብዛኛዎቹ ቦርጫም ሰዎች፣ ቦርጫም የሆኑት ሰውነታቸው ከሚያስፈልገው በላይ በመብላታቸው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ዓለማችን በቀን ከምታበስለው ምግብ ውስጥ፣ ለረዥም ጊዜ የሌላን ሰው ‹‹ድርሻ›› ወይም ለሌላ ሰው ድርሻ ሊሆን ይገባ የነበረን ምግብ በመብላታቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታም ማለትም ከልክ በላይ መወፈር ለተለያዩ የጤና ችግሮች እያጋለጣቸው እንደሚገኝም እሙን ነው፡፡

አሜሪካንና አውሮፓን ጨምሮ፣ ሠለጠነ በሚባለው ዓለም ከልክ በላይ በመብላት ምክንያት የመጣው አላስፈላጊ ውፍረት፣ ሸክምም፣ የበሽታ ምንጭም የሆነባቸው ሰዎች በሰውነታቸው ላይ የተከማችን ስብ በሕክምና ለማስወገድ በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጥር ገንዘብ ያፈሳሉ፡፡ ያስ ሆኖ ጤና ከተገኘ አይደል? ንፉግነት – ‹‹የኔን ሀብት እኔው በልቼ ልፍጀው›› ማለት – የሚያስከፍለው ዋጋ ጤናን እስከማቃወስና ለሌላቸው ከማካፈል የሚገኘውን ውስጣዊና ህሊናዊ እርካታ እስከ መንፈግ እንደሚደርስ ከተረዳን በቂ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የሀብታሞች ንፉግነት በደንብ የሚገለጠው በድሆችና መካከለኛ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሀብታም በሀብታም ላይ ንፉግ አይሆንም፡፡ ሀበሾች ‹‹ያለውን ያለው ወደደው፣ እያበላው ነው እያጎመደው›› ማለታቸው ያለ ነገር አይደም፡፡ የዚህ ግጥም የመጨረሻ ስንኝ ‹‹እያበላው ነው እያጎመደው›› ሲል ከአንዱ ሀብታም በኩል ባለ ‹‹ቸርነት›› ምክንያት የተገነባ ውዴታ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ግጥም በባህሪው ቃላትን ስለሚቆጥብ (የቃላት ስስታም ስለሆነ) የተፈጠረ ነው፡፡ ሀብታሞች እርስ በርሳቸው እየተገባበዙ የፈጠሩት መወዳጀት እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ውዴታው ራሱ የተፈጠረውና ቀጣይ የሆነው አንዳቸው አንዳቸውን (ምናልባትም በወረፋ) በማብላታቸው/በመጋበዛቸው መሆኑ ይገባናል – በ‹‹ልከክልህ፣ እከክልኝ›› የተገነባ መዋደድ፤ አንዱ ማከኩን ሲያቆም የሚፈርስ መዋደድ፡፡

ያም ሆነ ይህ ስትትም ሆነ ንፉግነት በአገራችን እንዴት ወደ ባህልነት እንደተቀየሩ የሚያጠኑ ባለሙያዎች፣ ከድርጊቶችና ክዋኔዎች ድግግሜ (Pattern) በመነሳት ከሚያገኙት የጥናት ውጤት አንዱ ሊሆን የሚችለው ማኅበረሰባችን ለረዥም ዘመናት በምግብ እጥረትና ከፍ ሲልም በረሃብና ቸነፈር ውስጥ ማለፉ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ስስትና ንፉግነት በኅብረተሳባችን ውስጥ ጥሩ መደላድል ያገኙ መሆናቸውን የሚነግሩን ምሳሌያዊ አባባሎች በርካታ ናቸው – ከፊሎቹ በቀጥታ፣ ከፊሎቹ በተዛዋሪ፡፡ አሁን መግቢያችን ላይ ወደ አነሳነው ነጥብ እንመለስ፡-

‹‹እንግዳ ክቡር ነው›› የሚል አገላለጽ አለ፡፡ እርግጥም ክቡር ነው፡፡ (እዚህ ላይ የፖለቲከኛውን ወይም የዲፕሎማሲውን አለማለቴ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ የእዚያ ሠፈር ሰዎች ሲፈልጉ የሚከባበሩ፣ ሲያሻቸው ደግሞ የሚዘላለፉና አንዳቸው ሌላውን የሚያዋርዱ ናቸው፡፡ ከእነሱ ሜዳ ውጭ ያለው እንግዳ ግን – የሚታወቅም ሆነ የማይታወቅ – እንግዳ እስከሆነ ድረስ ክቡር ነው)፡፡

አንድ ሰው በእንግድነት ከሄደበት ቤት ውስጥ ዋል-አደር ባለ ቁጥር፣ ያ ሲመጣ እጅግ ደማቅ የነበረው የእንግድነቱ ቀለም እየገፈፈ ይሄድና ብዙም ሳቆይ ይፋቃል፡፡  እየቀነሰ የሄደው ሸብ እረብም ይቀርና የእንግድነቱ ፋይል ይዘጋል፡፡ ባለእንግዳዎቹ የእንግዳውን መሄድ ወይም የመሄጃ ቀኑን ‹‹መናፈቅ›› ሊጀምሩም ይችላሉ፡፡ ለዚህ አይደል ‹‹የእንግዳ ውበቱ፣ ሲታይ ነው ባቱ›› መባሉ፡፡

አንድ እንግዳ በአካባቢው ንዑስ ባህል (Subculture) ከሚጠበቀው በላይ በእንግድነት ከሄደበት ቤት ውስጥ ከዋለና ካደረ፣ ውበት የለውም፤ ያ በእንግድነት ሲመጣ የነበረው ውበት ተፍቆ ይጠፋል፡፡ በሚጠበቀው ቀን ወደ መጣበት ከተመለሰ ማለትም ባቱን (የእግሩን የኋላ ክፍል) ካሳየ፣ ያኔ ነው ውበት የሚኖረው፤ ያኔ ነው እንግድነቱ ከውበት የሚቆጠርለት፡፡ አባባሉ እንግዳ ሲሄድ አስተናጋጆች መደሰታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ቶሎ ቤታቸውን ለቆ እንዲሄድ ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ጭምር እሚናገር ነው፡፡

አንድ እንግዳ ከሰው ቤት ሄዶ መቆየት ያለበት የቀን መጠን እንደየ አካባቢው ንዑስ ባህል፣ ሰውዬው በእንግድነት ከሄደባቸው ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት (ዝምድና፣ ወዳጅነት፣ ወዘተ) እና ለእንግድነት በሚያበቃው ጉዳይ ዓይነትና መጠን የሚወሰን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሦስት ቀን መቆየት ሲገባው፣ አራት ቀን፣ ሁለት ቀን መቆየት ሲገባው ሦስት ቀን፣ አንድ ቀን መቆየት ሲገባው ሁለት ቀን፣ ደርሶ መልስ መሄድ ሲገባው ማደር (አንድ ቀን መቆየት) የለበትም፡፡ ይህን ካደረገ፣ የእንግድነት ቀለሙ በመፋቁ ምክንያት ውበቱን ያጣል፡፡  

በዚህም አለበለዚያ ‹‹የእንግዳ ውበቱ፣ ሲታይ ነው ባቱ›› የሚለው አነጋገር፣ አቶ ስስት ቢያንስ በተዛዋሪ ከተገለፀባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ መቼስ እንግዳው ቶሎ ወደ መጣበት እንዲመለስ የተፈለገው፣ ቤቱ ወይም የመደቡ መኝታ ጠቦ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ መድቡ ቢጠብ ከቆጥ ላይ፣ ቤቱ ቢጠብ ከጎረቤት፣  አንዳንዴም ከጓሮ ካለው ክምር ሥር ጭምር በማደር እንግዳን ማስተናገድ የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ ወጭ አልባ ናቸው፡፡ እናም እንግዳው ምግብ በመካፈል በኩል ‹‹ይፈጥርብናል›› ተብሎ የሚታሰበውን ችግር ለመከላከል የተቀመረ ተረትና ምሳሌ ነው፡፡ ባጭሩ የሆድ ነገር ያስከተለው ጣጣ ውጤት ነው፡፡

ከምግብ ጋር የተያያዘው ስስት አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ልክ ከማጣቱ የተነሳ፣ ‹‹እና ሰው የሚለፋው፣ ክረምት ከበጋ የሚፈጋው ለምንድን ነው?›› ያስብላል፡፡ ‹‹ሞልቶ አይመረግ›› የሚለውን ብሂል እስቲ ልብ ብለን እንየው፡፡ ይህ የተባለው ለሆድ ሲሆን፣ ባዮቹ ደግሞ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ሆድ ልክ እንደ  ጉድጓድ እህል የሚመረግ (ታሽጎ የሚቀመጥ) ቢሆን ኖሮ ምኞታቸው መሆኑን ይጠቁማል – ምኞቱ ‹‹ክንፍ ቢኖረኝ ኖሮ፣ እበር ነበር›› ዓይነት ምኞት ቢሆንም፡፡

ዋናው ነጥብ ያለው፣ ‹‹ከዚህን መሰሉ ምኞት ያደረሳቸው ምንድነው?›› የሚለው ላይ ነው፡፡ አንዴ ከበሉና ከጠገቡ በኋላ፣ ሆድን እንደ ጉድጓድ እህል ለወራት ወይም ለዓመት አሽጎ የማስቀመጥ ምኞት ወደ አዕምሯቸው ለምን መጣ? ዕድሜ ልካቸውን አፈር የሚገፉት፣ በጭቃው የሚዳክሩት፣ ቁርና ፀሐይ የሚፈራረቅባቸው ለምን ሆኖ? ቢቻል በቀን ሦስቴ፣ ያ ቢቀር ሁለቴ ለመብላት አልነበረምን? (እርግጥ ነው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህን ሁኔታ ለአገሬ ገበሬ ተመኝተውለት ነበር – ምኞቱ፣ ‹‹ክንፍ ቢኖረኝ ኖሮ…›› ሆኖ ቀረን እንጂ)፡፡

‹‹ሞልቶ አይመረግ›› የሚለው አነጋገር ከምርት እጥረት፣ ከዚያም ከምርት መጥፋትና መጥፋቱ ከሚያስከትለው ረሃብ የተወለደ ቀቢፀ ምኞት እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ሰዎች ይህን አባባል ረሃብ ቀርቶ፣ የምርት እጥረት በሌለበት ጊዜ ሁሉ ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህን መሰሉ ሁኔታ ሆድ በ‹‹ሞልቶ አይመረግ›› ሲገለጽ፣ አገላለጹን የመጠቀሙ ጉዳይ ከስስት ጣጣ የመነጨ እንጂ ምን ሊሆን ይችላል? ስስቱ ደግሞ ማኅበረሰቡ ያለፈበት የምግብ እጥረትና ረሃብ ጥሎት ያለፋው ሥነ ልቦናዊ ጠባሳ ነፀብራቅ ከመሆን ብዙም አይርቅም… (ጎበዝ ርዕሰ ስሰት የሚያልቅ አልሆነም፡፡ አበሾች ከሆድ ጋር የተያያዘውን ስስት፣ ያለ ስስት ነው የተረቱት፡፡ እኛም ሳንሳሳ በሚቀጥለው ጽሑፍ ማየት ግድ ይለናል)፡፡ (በክፍል አሥራ አንድ እንገናኝ – ኢንሻ አሏህ!)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...