Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአካል እስከ በይነ መረብ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሕፃናት

ከአካል እስከ በይነ መረብ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሕፃናት

ቀን:

ሕፃናት ካለባቸው ኃላፊነት ይልቅ ያላቸው መብት የበዛና በወላጆች ጥበቃና እንክብካቤ ማደግ የሚገባቸው የሚገባቸው ናቸው፡፡ ‹‹ልጅ የፈጣሪ ስጦታ ነው›› ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ውስጥም ሕፃናት የወላጆች መልካም ስጦታና የአብራክ ክፋይ መሆናቸው ይታመናል፡፡

ሕፃናት የሚገባቸውን አግኝተው ሲያድጉና ነፍስ ሲያውቁ ወይም ለአቅመ አዳምና ለአቅም ሔዋን ሲደርሱ ለወጆቻቸውና አሳዳጊዎቻቸው ጧሪ ቀባሪ፣ የኋላ ኋላም አገር ተረካቢ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደረጃ እንዲደርሱ እንደ ችግኝ መንከባከብ የወላጅ፣ የአሳዳጊና የአገር ድርሻ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገሮች ላይ የሕፃናት ልጆች መብት ሲጣስ ይታያል፡፡

በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ችግሩ ከመጉላቱ የተነሳ በርካታ ሕፃናት ፈተና ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሕፃናት ልጆች ዕድሜያቸው ሲደርስ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲሄዱ ከማድረግ ይልቅ፣ በጦርነት እንዲሁም በተለያዩ  ጎጂ ድርጊቶች እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ችግሩ በኢትዮጵያም የሚታይ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሲሠራም ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ ያስችላል የተባለው ውይይትም፣ የሕፃናት ቀንን ምክንያት በማድረግ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዳኛ አቶ ተክለ ሃይማኖት ዳኜ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሕፃናት መብቶቻቸው ተጥሰው ወደ ሕግ ቦታ ሲሄዱ ትክክለኛ ፍትሕ አያገኙም፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በሕፃናት ልጆች ላይ በደል የሚያደርሱ ግለሰቦች ወይም አጥፊዎች ባጠፉት ልክ ፍርድ እንዳያገኙም፣ በተበዳይ ወላጆች የመሸፋፈን ሥራ እንደሚሠራና እዚህ ላይም ሰፊ ክፍተት እንዳለ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በሕፃናት ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከ700 በላይ መሆናቸውን፣ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና የችግሩ ስፋት ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይም በተደጋጋሚ የሚመጣው ጉዳይ አስገድዶ መድፈርና ተያያዥ ጉዳዮች መሆናቸውን፣ እነዚህ በአካል ወይም በበይነ መረብ የሚፈጸሙ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለመቆጣጠርም ሆነ ጉዳዩን ለማስፈጸም ችግር እየሆነ ያለው በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚፈጸሙ ወንጀሎች መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ዜጎች ማንነታቸው እንደማይታወቅና ቢታወቅም ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ያለበት ቦታ ታውቆ ወደ ፍትሕ ለማቅረብ ችግር እንደሆነባቸው አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከድብደባና ተገቢ ካልሆነ አያያዝ ጋር የሚነሱ  ጉዳየች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን፣ በተለየ ሁኔታ የሚነሱ ጉዳዮች ግን የፆታዊ ጥቃትና ሕፃናት ዕድሜያቸው ሳይደርስ ያልተገባ ሥራ ላይ ማሳተፍ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ሕፃናት ላይ ለሚፈጽሙ ወንጀለኞች አስተማሪ የሆነ ቅጣት በመቅጣት የወንጀል ድርጊቶችን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ተቋሙም ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጣቸው መካከል የሕፃናት መብት ደኅንነት መከበር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው ያሉት ኃላፊው፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለሕፃናት መብት መሟገት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የሕፃናትን ቀን በየዓመቱ ከማክበር በዘለለ በርካታ ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ ይህም ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከፍርድ ቤት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሠሩ መሆኑን፣ በቅንጅት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የጥቃት አድራሾች ቁጥራዊ መረጃ ማወቅ፣ ወንጀል የተፈጸመባቸውን ሕፃናት ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረግና ሌሎች ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ እያንዳንዱ ምድብ ችሎት ላይ የሴቶች ሕፃናት ምድብ ችሎት እንዳለ፣ እነዚህ ተቋማት የተለያዩ መረጃዎችን በተጠየቁ ወቅት ከማቅረብ በዘለለ የሕፃናትን መብት የሚያስከብሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሕፃናት ልጆች የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወጥ የሆነ አሠራር ተዘርግቷል ያሉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡምድ ናቸው፡፡

የሕፃናት ልጆችን የመብት ጥሰት ሆነ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ቀበሌ በመውረድ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን በመቆጣጠርና በመንከባከብ፣ ከአጉል ድርጊት እንዲወጡ መሥራት እንደሚኖባቸው ገልጸው፣ በሕፃናት ልጆች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት መፍትሔ ለማበጀት መንግሥት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...