በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የራምኖን ኢትዮጵያ የዕውቀት ፓርክ ማኅበር በሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የገቢ ማሳሰቢያ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ግብርና፣ ትምህርት፣ የጤናና መሰል ማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ወድመዋል የሚለው ማኅበሩ፣ አሁናዊ ሁኔታው ሲታይ ሕዝቡ ለማምረትም ሆነ ሌሎች ሥራዎች ለመሥራት አስቻይ ነገሮች ወይም ግብዓቶች ስለሌለው ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ተጋልጦ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ አቶ ሀፍቱ አዳነ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ አበበ ፍቅር በገቢ ማሰባሰቢያውና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ማኅበረሰቡ ያጋጠሙትን ችግሮች ቢያብራሩልን?
አቶ ሀፍቱ፡- አሁን በተፈጠረው ሰላም ወደ ሥራና ወደ ትምህርት ለመመለስ በመንግሥት፣ በአገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ አካላት የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ከሆኑ ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ ለማሟላት በተለያዩ አካላት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁን ክልሉ በሚገኝበት ሁኔታ ከመሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ጎን ለጎን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው፣ አርሶ አደር ወደ እርሻው መሰማራት አለባቸው፡፡ ይሁንና በአካባቢው ካጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች የሕዝቡ የጤና ችግሮች፣ የትምህርትና የግብርና መሣሪያዎች እጥረት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሮቹን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሀፍቱ፡- ችግሮቹን ለመፍታት ማኅበራችን እንደ አገር በቀል ተቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ ለማሳካት ካቀዳቸው በርካታ ሥራዎች በቀዳሚነት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው የድኅረ ጦርነት የጤና አገልግሎት ክፍተትን መሙላት፣ የትምህርትና የግብርና መሣሪያዎችና ግብዓቶችን ማሰባሰብ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ወቅቱ ያዝመራ እንደመሆኑ አርሶ አደሩ አርሶ ዘር የሚዘራበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በመሆኑም በጦርነቱ ምክንያት ማረሻውንም በሬውንም ያጡ ገበሬዎች በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የችግሩ ስፋትና አንገብጋቢነት ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ምላሽ ለመስጠት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ቢነግሩን?
አቶ ሀፍቱ፡- የመርሐ ግብሩ ዓላማ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ሁሉም ሰው በቻለው አቅም የሰብዓዊነት/የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣና ጉዳት የደረሰበትን ኅብረተሰብ እንዲታደግ ለማስቻል ነው፡፡ ከመርሐ ግብሩ አንዱ የድኅረ ጦርነት የጤና አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብታዊ ችግር መፍታት ነው፡፡ የጤና ችግር ሲነሳ ፈርጀ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በድኅረ ጦርነት ጤና ሲነሳ በመከላከልና በማከም የሚቋጭ ነገር አይደለም፡፡ በድኅረ ጦርነት አካላዊ መጎዳት አለ፡፡ ሥነ ልቦናዊ መጎዳት አለ፡፡ ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ አለ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ልጆች ተገብረዋል፡፡ ኢኮኖሚው ወድቋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከገቢ ማሰባሰቢያው ምን ትጠብቃላችሁ?
አቶ ሀፍቱ፡- ራምኖን ኢትዮጵያ የዕውቀት ፓርክ ማኅበር በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በሚኖረው የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት መርሐ ግብር የአገራችን ጤና ተቋማት ጤናውን እንዲደግፉ፣ ከመንግሥት እስከ ግል ያሉ የጤና ተቋማት ለዚህ አገልግሎት የሚውል ፈንድ ያግዛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ገንዘቡን ካሰባሰብን በኋላ የሚቀጠሩ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ቀጥረን ከጦርነት በኋላ የድኅረ ጦርነት ሕክምና እንዲሰጡ እናደርጋለን፡፡ አንድ ማረሻ ለአንድ አርሶ አደር የሚል ድጋፍም ይኖረናል፡፡ ማኅበሩ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ አብዛኛው ገበሬ የሚያርስበት በሬና መሣሪያዎች በጦርነቱ ምክንያት አጥቷል፡፡ ከዚህ የተነሳም የእርሻ መሬቱ ጾም አዳሪ ሊሆን ነው፡፡ ዘንድሮ አርሶ ካልዘራ በሚቀጥለው ዓመት በእጅጉ ይቸገራል፡፡ ተረጂ የመሆን ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ለዘመናት አርሶ ሕዝብን ሲቀልብ የኖረው አርሶ አደር እንደ ልማዱ አርሶ ልጆቹንና ሌሎችን ይቀልብ ዘንድ አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እናግዛለን ብለን የተነሳን ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ ከ500 በላይ ሰዎች ይገኛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ በዚህም ከዘጠኝ መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- የመርሐ ግብሩ ዓላማው ምንድነው?
አቶ ሀፍቱ፡- በዚህ ዓመት የትግራይ አርሶ አደር አርሶ ራሱን የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር የዚህ መርሐ ግብር ዓላማና ግብ ነው፡፡ በተገኘው ገቢ መሠረት ለተቸገሩ አርሶ አደሮች አንድ ማረሻ ለአንድ አርሶ አደር ትግራይ ካሉ የማረሻ አምራች ተቋማት የሚገዛ ሲሆን፣ በአቅራቢ ድርጅቱ በኩል የአቅርቦት እጥረት ከገጠመ ደግሞ አዲስ አበባ ካለው የብረታ ብረት ፋብሪካ ማረሻዎቹ ተገዝተው የሚላኩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሪፖርተር፡- ገንዘቡ ከለጋሾች ከተሰበሰበ በኋላ በምን መልኩ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ አስባችኋል?
አቶ ሀፍቱ፡- ማረሻዎቹና ሌሎች በዚህ ፕሮግራም የሚሰበሰቡ የእርሻ መሣሪያዎች አንድም በትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ በኩል የሚሠራጩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከእያንዳንዱ ወረዳ የአባወራና እማወራ ብዛት በእጃችን ባለው ማስረጃ መሠረት ወደ ወረዳዎች ተልኮ የወረዳ ፋይናንስ በንብረት መቀበያ ሰነድ ገቢ ካደረገው በኋላ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪም ማረጋገጫ ደብዳቤ እንዲጽፍ በማድረግ ለሚያስፈልጋቸው አርሶ አደሮች የሚሠራጩ ይሆናል፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው መንገዶች ለተጠቃሚው የመድረስ ዕድላቸው አጠራጣሪ መስሎ ከታየን ደግሞ የወረዳው ዕገዛ የሚያስፈልጋቸው አርሶ አደሮች ስም ዝርዝር ስልክ ቁጥርና አካውንት ቁጥራቸው እንዲላክ በማደረግ በአካውንት ቁጥራቸው እንዲገባ የሚደረግበት አሠራር ሊዘረጋ ይችላል፡፡ መርሐ ግብሩ በዕቅዳችን ልክ ከሄደ አርሶ አደር በሚቀጥለው ዓመት ከተመፅዋችነት ነፃ እንደሚያደርገውና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ጠቀሜታ እንዳለው እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከግብርናው ውጭስ በሌላው ሴክተር ድጋፍ ለማድረግ አላሰባችሁም?
አቶ ሀፍቱ፡- በትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በላይ ትምህርት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ወላጆች ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ትምህርት የጀመረ ቢሆንም አብዛኛው ተማሪ የሚማርበት የትምህርት ቁሳቁስ የለውም፡፡ ተማሪ በአግባቡ ከተማረ ነገ አገርን በአግባቡ የሚረከብ ትውልድ ይሆናል፡፡ ከትምህርት ከተስተጓጎለ ግን በተቃራኒው አገርና ሕዝብ ላይ መጥፎ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑ አይቀርም፡፡ የ‹‹አንድ ሰው ለአንድ ተማሪ ደብተርና እስክርቢቶ›› ንቅናቄ ለማድረግም አስበናል፡፡ ዓላማውም በየትምህርት ቤቱ ያሉ የመማር ፍላጎት ኖሯቸው የመማርያ ቁሳቁስ አጥተው እየተቸገሩ ላሉ ሕፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ የ‹‹አንድ ሰው ለአንድ ተማሪ ደብተርና እስክርቢቶ›› በሚል የሚደረግ ነው፡፡ ንቅናቄ በትምህርት ቁሳቁስ/ግብዓት ዕጦት ምክንያት ከትምህርት የሚቀር ተማሪ እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ የንቅናቄ ዕቅዱ ሰፊና በጥናት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ በቀጣይም በየክልሉ ያሉ የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ያለባቸው ተማሪዎችን ድጋፍ የሚያደርግ ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው፡፡ በዚህ የመጀመርያው ንቅናቄ ግን በትግራይ ክልል ለሚገኙና ከክልሉ በሚገኝ መረጃ መሠረት በቀዳሚነት ሊደገፉ ለሚገባቸው ተማሪዎች የሚውል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መቼና ለምን ዓላማ ነው የተመሠረተው?
አቶ ሀፍቱ፡- በ2012 ዓ.ም. ለትርፍ ያልተቋቋመ አገር በቀል ማኅበር ሲሆን ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ያልሆነ፣ ሰዎች በፆታ፣ በዕድሜ፣ በአካላዊ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚና ትምህርት ደረጃቸው ምክንያት ልዩነት የማይፈጥር፣ ልዩ ልዩ የሥራ ሥምሪት ባላቸው ሲቪል ማኅበረሰቦች የተቋቋመ በጎ አድራጎት ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቢቆይም፣ በነበረው አገራዊ ሁኔታ ፕሮግራሞቹን ሳያሳካ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሕጋዊ ዕውቅና ካገኘበት ማግስት ጀምሮ የተለያዩ እንቅስሴዎች ሲያደርገ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ከዓላማው የመነጨ ሰብዓዊ በሆኑ ሥራዎች ላይ የሚሳተፍ ማኅበር ነው፡፡ ይህ የ‹‹አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ›› ንቅናቄም በማኅበሩ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች አንዱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ እሑድ ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋቢ ሸበሌ በሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ በአካል መገኘት ለማይችሉ ለጋሾች ሌላ አማራጭ አላችሁ?
አቶ ሀፍቱ፡- በዝግጅቱ መገኘት ያልቻሉ ሰዎች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የማኅበሩ ባዘጋጃቸው ማዕከላት በመገኘት ማስረከብ ይቻላል፡፡ ይህም ማንኛውም ሰው የቻለውን የደብተር፣ ቦርሳ፣ እርሳስና ስክሪፕቶና መሰል የትምህርት ቁወቁስ ይዞ በመሄድ ገቢ ማድረግ ይችላል፡፡ ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ወደ ሚሰበሰቡበት ሄዶ ማስረከብ የማይችል ለጋሽ ደግሞ ለመርሐ ግብሩ ተብሎ ወደ ተከፈተው ባንክ በመላክ ደብተርና ሌሎች ለተማሪዎቹ የሚውሉ ቁሳቁሶች እንዲገዛ ማድረግ ይችላል፡፡ ለተማሪዎች የተሰበሰበው ቁሳቁስ ከትግራይ ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ወደ ሚፈለጉበት ቦታ የሚያደርሱ ይሆናሉ፡፡