Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

… ይህቺ መንገድ ሁለተኛዋን አትሽርም….

ትኩስ ፅሁፎች

አንድ ሰው አሞራ መሆን ቢችል ወይም አውሮፕላን አብራሪ ቢሆንና፣ ወደ ሰማይ ወጥቶም የመንደሬን የመንገድ ሥርዓት ቢቃኝ የሚያየው ማዕከሉን መሰየም የሚከብድ፣ ጠመዝማዛ፣ መጥረጊያ ያፈረሰው የሸረሪት ድር ነው፡፡ ይኼ ተመልካች የሚገነዘበው  ተደጋጋሚ ትዕይነት ከእያንዳንዱ ግቢ መውጫ ላይ የሚነሱትን ትናንሽ የአቧራማ መንገዶች ነው፡፡ እነዚህ ትናንሾች እንደ መትን ተሰብስበው ትልቁን የአፈር መንገድ ይቀላቀሉታል….

ከቤቴ ደጃፍ በተጥመዘመዘ ስልት ዋናው የሰፈሬ ኮረኮንች መንገድ የምታስገባ እርዝመቷ አራት መቶ ሜትር ያህል፣ ስፋቷ አንድ እርምጃ ያህል የሆነ በየጉድጓዶቿ ላይ ድቡልቡልና ሰታታ ድንጋዮች የተነጠፉባት የመጋቢዎች መጋቢ መንገድ አለች፡፡ ክረምት ክረምት መንገዷ ሁለት የተቆራኙ የባሕር ለውጦች ታሳያለች… የመጀመሪያው (መሐሉ) ጭቃና የሚያዳልጥ ሲሆን ዳር ዳሩ ግን ጎፈሬያም ሳር ይሆናል፡፡ በጋ በጋ ሳሩ ይደርቅና እነዚህን ሁለቱን የሚለያቸው ነገር ቢኖር ለምድ ያቀናበረው ነሲበኛ የእርምጃ ባህላችን እየተመተመ የገነባው መረሬና ነጭ የተደባለቀበት የአፈር መቀነት ብቻ ይሆናል፡፡

 በጠቅላላ አራት ኩርባዎች አሏት፡፡ የመጀመሪያዋ ኩርባ፣ አነ ካሱ ቤት ስትደርስ የመንገድነት ሕልውናዋ እንዳይጠፋ ወደ ግራ የታጠፈችዋ ናት፡፡ ሁለተኛዋ ኩርባ በጎርፍ የተሸረሸረ ዘባጣ ቦታ ስትደርስ ወደ ቀኝ የታጠፈችዋ ናት ሦስተኛዋ የሠፈሩ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ያለችው ሰፈረተኛው በአፍንጫው እየተመከረ የሰራት እንደ ደባ  የምትሸት ገመምተኛ ቅንፍ ናት፡፡ አራተኛዋ ኩርባ ወጣት ናት መሬቱ ተሸጦ ስለታጠረና እንደተለመደው መሄድ ስላልተቻለ ታፍኖ ላለመቅረት ሠፈረተኛው ማንንም ሳያማክር ቀላል አጭር አቅጣጫ ፈልጎ የፈጠራት ናት፡፡ ሌሎች ትናንሽ  ኩርባዎች ቢኖሩም በተጓዥ ሕሊና ‹መጠምዘዝ› ‹መታጠፍ› የተባሉትን ቃላት ለመጠቀም የሚያደርሱ አይደሉም፡፡

መንገዷ በቤቶች የአጥር ቢጋር እንደ ዘንጋዳ እንጀራ የተሰባበረው ጠፍጣፋውና ሰርባዳው የሠፈራችን መልከአምድር ላይ እንደ ወፍራም ስፌት አርፋለች፡፡ ስም የላትም፡፡ ደራሲዋ ነጠላ ስም የለውም፡፡ ሁላችን የሰራናት የየራሳችን የግል እቅዶችና ትርምሶች ጭማቂ ናት፡፡

  • አዳም ረታ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ›› (2003)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች