የዓለም አትሌቲክስ፣ የወርቅ ደረጃ ያለውን የዓለም የቤት ውስጥ 3000 ሜትር ውድድር አሸንፎ የነበረው የለሜቻ ግርማ ክብረ ወሰን ማፅደቁን ይፋ አደረገ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በፈረንሣይ ለቨን የቤት ውስጥ 3000 ሜትር 7፡23.81 በመግባት ነበር ክብረ ወሰኑን የሰበረው፡፡
ባለፈው ዓርብ በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ውድድር የ3000 ሜትር መሰናክልን አዲስ ክብረ ወሰን በመጨበጥ ማሸነፍ የቻለው ለሜቻ፣ ሁለተኛው ክብረ ወሰኑም ፀድቆለታል፡፡
የቤት ውስጥ የ3000 ሜትር ውድድር ክብረ ወሰን እ.ኤ.አ. 1998 በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄድ ውድድር ኬንያዊው ዳንኤል ኮመን 7፡24፡90 በመግባት ተይዞ ነበር፡፡
ሆኖም ለሜቻ በድንቅ አጨራረስ ታጅቦ ስፔናዊውን መሐመድ ካቲር በማስከተል የዓለም ክብረ ወሰን በእጁ መጨበጥ መቻሉ ይታወሳል፡፡ ሁለቱም አትሌቶች የገቡበት ሰዓት ቀድሞ ከነበረው የክብረ ወሰን ሰዓት በታች በመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ለሜቻ በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር 7፡52.11 በመግባትና በ1.52 ሰኮንድ በማሻሻል ለ19 ዓመት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል፡፡
ለሜቻ እ.ኤ.አ. በ2019 ዶሃ ዓለም ሻምፒዮና፣ በ2022 የኦሪጎን ዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያዎች ማሳካት መቻሉ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር በቤልግሬድ የቤት ውስጥ 3000 ሜትር ውድድር ሦስተኛ ደረጃ ይዞ የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል፡፡
‹‹በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ክብረ ወሰን መጨበጥ ከውድድሩ ሦስት ቀናት አስቀድሞ ስናገር ነበር፡፡ ወንድሜ አሠልጣኜ ነው፡፡ ክብረ ወሰን መስበር እንደምችል ይነግረኝ ነበር፡፡ በእርግጥ አምንበት ነበር፤›› በማለት ለሜቻ ከውድድሩ በኋላ ስለድሉ አስተያየት ሰንዝሯል፡፡
ለሜቻ ልምምድ ሲያደርግ ጥሩ ስሜትና ጥሩ አቋም ላይ እንደነበር፣ በተጨማሪም በዕለቱ በስታዲየሙ በርካታ ተመልካቾች መመልከቱን ተናግሯል፡፡
ለሜቻ ከዚህ ድል በኋላ በዘንድሮ የሃንጋሪያ ዓለም ሻምፒዮና በርቀቱ ማሸነፍ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
የ3000 ሜትር የቀጥታና የመሰናክል ሩጫ ባለክብረ ወሰኑ የ22 ዓመቱ ለሜቻ፣ በቀጣይ በግል ውድድሮች፣ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶች ቀዳሚው ነው፡፡