Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኦሮሚያ ከተመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሥራ የጀመሩት 43 በመቶ መሆናቸው ተረጋገጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ክልል ከተመሠረተበት እ.ኤ.ኤ. ከ1992 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ከተመዘገቡ ከ20 ሺሕ በላይ የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች፣ በተጨባጭ ወደ ሥራ የገቡት 43 በመቶ ያህሉ መሆናቸውን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የተደረገ ጥናት አረጋገጠ፡፡

አሶሴሽኑ ከኦሮሚያ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ካካሄዳቸው አራት የጥናት ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ በኦሮሚያ ያለው የቁጠባና የኢንቨስትመንት ሁኔታ (Dynamics) የተመለከተው አንደኛው ሲሆን፣ ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢኮኖሚክስ አሶሼሽን ይፋ ሆኖ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  

ጥናቱን ካደረጉት ምሁራን አንዱ የሆኑትና በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ የሆኑት አበበ አምባቸው (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ ከቁጠባና ኢንቨስትመንት ፋይናንስ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል ያለው የኢንቨስትመንት ዳራ ምን ይመስላል የሚለውን ጥናቱ ዳሷል፡፡

በዚህም ክልሉ ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ወይም ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተመዘገቡት የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቁጥር ከ20 ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ወደ ሥራ የገቡት 43 በመቶ የሚሆኑት መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ከጠቅላላ 20,837 ፕሮጀክቶ ውስጥ 47 በመቶ የሚሆኑት ፈቃድ ያገኙት እ.ኤ.አ ከ2018 ወዲህ መሆኑን፣ በአጠቃላይ ወደ ሥራ የገቡት 8,926 (43 በመቶ) እንደሆኑና ከእነዚህም 41.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የያዙት የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ወደ ሥራ ገብተዋል የተባሉት ኢንቨስትመንቶችም በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ እንዳልሆኑ የኢኮኖሚክስ አሶሼሽን ጥናት ገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ፣ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ሁለተኛውና ከአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ 31 በመቶ የሚሆነውን እንደሚያስተናግድ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ፣ ክልሉ ካስተናገዳቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ተግባር የተቀየረው 55 በመቶ የሚሆነው ነው፡፡ ይህም የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎች የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳለው አኃዙ ያስረዳል ተብሏል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በአገር አቀፍም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ ተግባር የመቀየሩ እንቅስቃሴ የመቀዛቀዝ ሁኔታ እንዳጋጠመው ተገልጿል፡፡

አብዛኞቹ ፈቃድ የተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ያልገቡበት ምክንያት ሲጠና፣ በአገሪቱ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና የፖለቲካ አለመረጋጋት በዋናነት የተገኙ ምክንያቶች መሆናቸውን አበበ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ሌላው በምክንያትነት የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል ኢንቨስተሮች ግልጽ የሆነ የኢንቨስትመንት ሐሳብ ይዘው አለመምጣታቸው፣ የትግበራ (የአፈጻጸም) ስትራቴጂ አለመዘጋጀቱ ሌላው ከኢንቨስተሮች ጋር የሚያያዝ ተጠቃሽ ችግር ነው ተብሏል፡፡

በኦሮሚያ ያለው የቁጠባ ሥርዓት በተለይም እ.ኤ.ኤ ከ2011/12 ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው አኃዝ የሚበልጥበት ሁኔታ እንዳለ ጥናቱ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ለኢንቨስትመንት ቁልፍ የሆነው የባንክ ቁጠባ ሥርጭት በቅርንጫፍ ደረጃ እስከ ታች አለመሰጠቱ እንደ መሰናክል ተጠቅሷል፡፡

 ይህ ባለመሆኑ ከግማሽ በላይ የሆነው ፕሮጀክት የታሰበለትን ዓላማ በማሳካት ገቢና የሥራ ዕድል ፈጥሮ የተፈለገውን ነገር ባያመጣም በክልሉ እየተተገበረ ያለው ሪፎርም፣ የክልሉ መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብት የሰጠው ትኩረትና ቁርጠኝነት ላይ መሥራት ከተቻለ ኦሮሚያ በኢንቨስትመንት ከዚህ በላይ መልማት የምትችልበት ሁኔታ መኖሩን አበበ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን አሁን ካለው በላይ ማሳደግ፣ የተገኘውን ኢንቨስትመንት ወደ ውጤታማ ወደሆነ ዘርፍ እንዲሄድ መፍቀድ፣ የኢንቨስተሮቹን በራስ መተማመን ማጎልበትና የኢንቨስትመንቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል ተብሏል፡፡

ከኢንቨስትመንት ጋር በተገናኘ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ከሙስና ጋር በተገናኘ የሚቀርቡ ትችቶችን ማስቀረት እንደሚገባ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ፕላንና ልማት ኮሚሽነር አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በቀረበው የጥናት ውጤትና ውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የኦሮሚያ ልማት በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከኢኮኖሚክ አሶሴሽን ጋር በመሆን የተጠኑት ጥናቶች፣ የቀረቡት ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ውይይቱ በቀጣይ እንዴት የክልሉ ዕቅድ አካል አድርገው ይጠቀሟቸዋል የሚለውንም ለመመካከር ወርክሾፑ እንደተዘጋጀ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወሉ አብዱ በበኩላቸው፣ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግር ውስጥ ሆና የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት አገሮች አንዷ ሆናለች ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡

ቁልፍ የኢኮኖሚ አመላካቾች በሚባሉት የዜጎች ዕድገት መለኪያዎች፣ ቁጠባ፣ ኢንቨስትመንት፣ ትምህርትና ጤና በመሳሰሉት ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው እንደሚገኝም አቶ አወሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች