Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በዕርዳታ ምግብ ዘረፋ ላይ ለቀረበው ስሞታ በቂ ምላሽ ያስፈልጋል!

በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለኢትዮጵያ የሚያቀርቡት የዕርዳታ ምግብ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ሹማምንት አማካይነት፣ ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውል ተደርጓል በማለት ዕርዳታ ማቋረጣቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መረጃ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሃያ ሚሊዮን በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በጦርነት ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉ፣ በድርቅ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የሰው እጅ የሚጠብቁ ናቸው፡፡፡ እንደሚታወቀው ከውጭ ከሚገባው የምግብም ሆነ የምግብ ነክ ቁሳቁሶች ዕርዳታ በአብዛኛው የሚገኘው ከአሜሪካ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሌሎች ለጋሽ አገሮችና ድርጅቶችም በተመድ አማካይነት አበርክቶ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚያጋጥሟት ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት፣ በስንት ልመና በምፅዋት የሚገኝ ነፍስ አድን ዕርዳታ የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነ ሲባል የመንግሥት ዕርምጃ ፈጣንና ቅፅበታዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለቀረበው ስሞታም አሳማኝ መረጃ በማቅረብ ሚሊዮኖችን ከቅጣት መታደግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስናም ይባል ሌብነት ከመጠን በላይ ቅጥ እያጣ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት መረን የለቀቀ ድርጊት ከመጠን በላይ ሲንሰራፋ፣ መንግሥት ሕግና ሥርዓት በማስከበር አገርን መታደግ ግዴታው ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል ብሔራዊ መንግሥታት ውስጥ እንደ አረም የበቀለውን የዘረፋ ሙጃ ማስወገድ ካልተቻለ፣ ይህ ማናለብኝነት አገርን የሚያፈራርሱ አስደንጋጭ ወንጀሎችን ከመፈጸም ወደኋላ አይልም፡፡ መሬት ወርሮ በመዝረፍና የመንግሥት በጀት በመመንተፍ እየከበሩ ያሉ የመንግሥት ሹማምንትና ግብረ አበሮቻቸው፣ በዕርዳታ የመጣ ምግብን ለነጋዴዎች በማስተላለፍ ወደ ውጭ ጭምር ኤክስፖርት አድርገዋል ተብሎ በለጋሾች ሪፖርት ሲደረግ ያስደነግጣል፡፡ ለአገራቸው ማንኛውንም መስዋዕትነት በደስታ ለመክፈል ቅር የማይላቸው በርካታ አገር ወዳድ ዜጎች፣ እንዲህ ዓይነቱን መረን የወጣ ድርጊት ሲሰሙ የደረሰባቸው መከፋት በቃል ከሚገልጹት በላይ ነው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በተመድ የቀረቡ ሪፖርቶችን በተመለከተ መንግሥት እውነቱን አጣርቶ ማስታወቅ ይጠበቅበታል፡፡

በአገር ላይ አሳፋሪ ድርጊት ተፈጽሞ ከማየት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ አሳፋሪ ድርጊቶች የሚበራከቱት የሕግ የበላይነት ሳይኖር ቀርቶ ሥርዓተ አልበኝነት ሲንሰራፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሥርዓተ አልበኝነት ከመጠን በላይ እየተንሰራፋ ለመሆኑ ማሳያ ከሚሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ቅጥ ያጣው ሌብነት ነው፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ከመጠን በላይ ሥር የሰደደው ሙስና ዓይን አውጣ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በሁሉም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሊባል በሚችል ሁኔታ ያለ ጉቦ ተገልጋዮችን ማስተናገድ ብርቅ ሆኗል፡፡ በዚህ አስከፊ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሃይ የሚል በመጥፋቱ የተገልጋዮች ቅሬታ ከሚነገረው በላይ እየሆነ ነው፡፡ የዕርዳታ ምግቦችን ከተረጂዎች አፍ ላይ ነጥቆ በመሸጥ የተጀመረው አሳፋሪ ድርጊት ዕድሜው ረዘም ያለ ቢሆንም፣ በሰሞኑ የአሜሪካ መንግሥትና የተመድ ሪፖርቶች ውስጥ የተሰማው አደገኛ አዝማሚያ ግን ከሚታገሱት በላይ አስደንጋጭ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት ድርጊቱን በጋራ መርምረው ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ መስማማታቸው እንዳለ ሆኖ፣ መንግሥት ግን ውስጡ የበቀለውን አደገኛ አረም ካልነቀለ መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል የዕርዳታ ምግብ ተዘርፎ ለሽያጭ መዋሉን፣ የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ማስታወቁና ዕርዳታ ማቆሙ አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ ተመድና የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት፣ ተመሳሳይ ምክንያት በፌዴራልና በሰባት ክልላዊ መንግሥታት ላይ በማቅረብ ዕርዳታ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዕርምጃ ምክንያት ሚሊዮኖች ለቅጣት ተዳርገዋል፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን፣ ይህ ጉዳይ በፍጥነት ተጣርቶ እውነታው ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መቅረብ አለበት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምዕራባውያን የጀመሩት የስንዴ ፖለቲካ እጅ ጥምዘዛ ከሆነም፣ መንግሥት በአገር ውስጥ ተፈጽሟል ተብሎ ሪፖርት የቀረበበትን የዘረፋ ድራማ ገሃድ ሊያደርገው ይገባል፡፡ ሚሊዮኖችን ከረሃብ ጋር ያፋጠጠው የዕርዳታ ማቋረጥ እንደተባለው ከዝርፊያ ጋር የተያያዘ ከሆነም፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታውም እንደሆነ ይታወቅ፡፡

በሚስጥር ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሾልከው ደረሱ በተባሉ መረጃዎች መሠረት፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት በመንግሥት አካላት ከለጋሾች የተገኘ የምግብ ርዳታ ወደ ወታደራዊ ክፍሎች መዘዋወሩን ማመኑ ተሰምቷል፡፡ ይህንን በተመለከተ በሁለቱም ወገኖች በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ መረጃው ለሚዲያዎች እንዲሾልክ ሲደረግ ግን እንዲተላለፍ የተፈለገ መልዕክት አለ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ይህንንም ጉዳይ በነካ እጁ አጣርቶ ማስታወቅ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለበት በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ስለተደነገገ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሽና የወገኖቻችን ሰቆቃ የሚያባብስ ድርጊት ካለም፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እውነታው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አገር የሌቦችና የዘራፊዎች መፈንጫ እንዳትሆን ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ በዕርዳታ ምግብ ዘረፋም ሆነ በሌሎች አስከፊ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩ ካሉም ለሕግ ማቅረብ ይለመድ፡፡ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የተንሰራፋውን አደገኛ የዘረፋ ኔትወርክ ማስታመም ይቁም፡፡

ከሃያ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወገኖች መቅረብ የሚገባው ዕርዳታ ሲቋረጥ ቅጣቱ እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ለጋሽ አገሮችም ሆኑ ተቋማት ዕርዳታ ለማቋረጥ ምንም ዓይነት ምክንያት ይኑራቸው፣ መንግሥት ግን ውስጡን በሚገባ አብጠርጥሮ ማጥራት ካልቻለ ጫናው በአገር ላይ ነው፡፡ በብልሹ ሥነ ምግባር የተበከሉ አካላትን ታቅፎ ለጋሾችን ለመውቀስ ከመጣደፍ በፊት፣ የውስጥ ገመናን በሕግና በሥርዓት ማስተካከል ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ ይታወቅ፡፡ በአገር ውስጥ በሕዝብና በመንግሥት ሀብት እንዳሻቸው የሚፈነጩ በወገንተኝነት የሚደረግላቸው ማድበስበስ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ጊዜው ሳይረፍድ ይከናወናል የተባለው ምርመራ በፍጥነት ተካሂዶ እውነታውን ማሳወቅ ላይ ይተኮር፡፡ ለሚሊዮኖች መድረስ ያለበት የዕርዳታ ምግብ የተቋረጠው በማስረጃ ላይ በተመሠረተ ግኝት ነው ተብሎ በግልጽ ሲነገር፣ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ፈጣን ምርመራ በማድረግ ተረጂዎችን ለረሃብ የሚያጋልጠውን ድርጊት ማስቆም ነው፡፡  በዕርዳታ ምግብ ዘረፋ ላይ ለቀረበው ስሞታ በቂ ምላሽ እንደሚያስፈልግ መተማመን ተገቢ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...