በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጎዱ የአፋር፣ የአማራና የትግራይ አካባቢዎች ለደረሱ ፆታዊ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው የጀጅ (Judge) የፍትሕ፣ የምክክርና የፆታ እኩልነት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ የሆነውና በጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝንነርስ ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ መሪነት ከሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ለሚተገበረው ፕሮጀክት፣ የፈረንሣይ መንግሥት የ928 ሺሕ ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሬሚ መርዢ እንዳሉት፣ የፈረንሣይ መንግሥት ቅድሚያ ከሰጣቸው የማኅበረሰብ አጀንዳዎች አንዱ ፆታዊ እኩልነት ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2023 በፆታ እኩልነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ሲተገብሩ የቆዩ መሆናቸውን፣ በቀጣይ ለ18 ወራት የሚዘልቀውን የጀጅ ፕሮጀክት ይደገፋል ብለዋል፡፡
በፆታ እኩልነት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በ18 ወራት ለመቅረፍ እንደማይቻል በማስታወስም፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፍላጎት በሆነው በመልካም አስተዳደር፣ በሰላም ግንባታ፣ የሴቶችን ድምፅ በማሰማትና በተያያዥ ጉዳዮች የጀመሯቸውን ሥራዎች ለመቀጠል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ፆታን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ላይ የሚሠሩት ኒውትሪሽን ፎር ኤዱኬሽን ኤንድ ዴቨሎፕመንት፣ እንዲሁም ዮክሪያ ተባባሪነትና በጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝነርስ ሬሎውሽን ኢትዮጵያ አስተባባሪነት በጋራ የሚተገበረው የፍትሕ የምክክርና የፆታ እኩልነት ፕሮጀክት፣ በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሕግና ከተያያዥ ጉዳዮች አንፃር የሚደርስ መሆኑን፣ በፌሎውሺፑ ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ውብሸት ሽፈራው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ተጎጂዎችን ከመለየት ጀምሮ ፍትሕ እስከሚያገኙበት የሚሠራው ፕሮጀክቱ፣ ለተጀመረው የሽግግር ፍትሕና የምክክር መድረክ አጋዥ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡
የፊሎውሽፑ ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው በሰሜን ኢትትዮጵያ ጦርነት ሳይጀመር፣ በኦሮሚያ ክልልም ግጭት ሳይባባስ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ሲወተውቱ መቆየታቸውን፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ውድመት እንደደረሰ፣ የነበሩ ዕድሎችም መበላሸታቸውን በመግለጽ፣ ወደፊት በሽግግር ፍትሕና በሰላም ውይይት ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረውን ዕድል ዳግም እንዳይታጣ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ታዬ ደንደአ ኢትዮጵያ በርካታ ሀብት ቢኖራትም በአስከፊ ድህነትና ግጭት ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው፣ ‹‹በመጨረሻ መነጋገር ላይቀር ግጭት ውስጥ እንገባለን፣ ተባብረን ወደፊት መሄድ ሲገባን ስንጠላለፍ ቆይተናል፣ ለቀጣይ ትውልድ እሴት ማስተላለፍ ሲገባን ዕዳን በዕዳ ላይ ጨምረናል፣ ለትውልዱ እሴት ከመሥራት ይልቅ ያለፈው ዓመት ዕዳ ትኩረት ስቧል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የምክክር ኮሚሽኑ ታሪክ እንደሚቀየር ይጠበቃል›› ያሉት አቶ ታዬ፣ ከዚህ ቀደም ያመለጡ በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን በማስታወስ፣ የምክክር ኮሚሽኑ ይዞ የመጣው ዕድል እንዳያመልጥ ሁሉም ዕውቀቱን ተጠቅሞ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የጀጅን ፕሮጀክት ከሚሠሩ ድርጅቶች በተጨማሪ ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ስላሉ የፕሮግራም መደራረብ እንዳይፈጠር፣ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ ለመገናኛ ብዙኃን እውነተኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን በማገልገልና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ እነዚህ በፕሮግራሞች ተካተው የሚሠራባቸው እንደሆነ ከፕሮጀክቱ ፈጻሚዎች ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱን ዕውን በማድረጉ ሒደት ተባባሪ ሆነው እንዲያገለግሉም ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከተውጣጡ አካላት ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡