- ቦርዱ በሕወሓት ስም ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት የምዝገባ ጥያቄ እንዲያቀርብ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ ቢሰጠውም አለማቅረቡንና የሚመዘገበው በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡
ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን ማግኘት እንዲችል በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 66 መሠረት የምዝገባ ጥያቄ እንዲያቀርብ ምርጫ ቦርድ ቢያሳስብም፣ እስካሁን አለማቅረቡንና በአባልነት ሊመዘገብ የሚችለው በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ካቀረበ መሆኑን ከቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ምርጫ ቦርድ ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የምዝገባ ጥያቄ በአንድ ወር ውስጥ እንዲያቀርብ ለሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የቀጠሮ ጊዜ ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄ ሳያቀርብ የቀጠሮው ጊዜው አልቋል፡፡
በተሰጠው ቀነ ቀጠሮ መሠረት የምዝገባ ጥያቄውን ለምርጫ ቦርድ ባለማቅረቡ ሕወሓት የወደፊት ዕጣ ፋንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄም፣ ‹‹በድጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንመዘግበዋልን፤›› የቦርዱ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት የጀመረው የምዝገባ ሒደት እንዳለና እንደሌለ ለቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹እስከሁን የለም፤›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በሕወሓት ስም ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት ከ120 መሥራች አባላት የቀረበለትን የቅድመ ፈቃድ ዕውቅና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በአቶ ገብረ ሚካኤል ተስፋይና ሌሎች ሦስት ግለሰቦች አወያይነት ሕወሓትን ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ክልላዊ ፓርቲ አድርገው ለመመሥረት መወሰናቸውን፣ የ120 መሥራች አባላት ዝርዝር በማያያዝ፣ የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ እንዲሰጣቸው ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ መጠየቃቸውን፣ ምርጫ ቦርድም ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የቀረበለትን የጊዜያዊ ፈቃድ ጥያቄ አግባብነት ካላቸው የአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌዎች አንፃር መርምሬያለሁ ማለቱን ሪፖርተር የተመለከተው የቦርዱ ደብዳቤ ያሳያል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 86 (1) እንደተገለጸው፣ ቦርዱ ይህን መሰል ጥያቄን በሚያስተናግድበት ወቅት የምዝገባ ጥያቄ የቀረበበት ስያሜ አህፅሮተ ስም በምርጫ ጊዜም ሆነ ከምርጫ ውጪ በዜጎች ዘንድ መምታታትን ወይም ግርታን የሚፈጥር መሆኑን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ነው በደብዳቤው የተገለጸው፡፡
‹‹በሌላ በኩል ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በሚል ስያሜ እየተጠራ በትግራይም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ መራጮች ዘንድ ለረዥም ዓመታት የሚታወቅ ፓርቲ እንደነበር ግልጽ ነው፤›› ያለው ምርጫ ቦርድ፣ ‹‹ይህ ሁኔታ ባለበት ሌሎች ግለሰቦች በዚህ ስም አዲስ ፓርቲ ቢያቋቁሙ፣ መራጮችን የሚያደናግሩ በመሆናቸው፣ እነ አቶ ገብረ ሚካኤል ተስፋይ ያቀረቡትን የቅድመ ዕውቅና ጥያቄ ቦርዱ አልተቀበለውም፤›› ብሏል፡፡