Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናክልሎች የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት እንደሚጋፋ ገለጹ

ክልሎች የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት እንደሚጋፋ ገለጹ

ቀን:

በማዕድን ዘርፍ ላለፉት 12 ዓመታት ሲሠራበት የቆየውን የማዕድን ሥራ አዋጅ ቁጥር 678/2002 የሚተካ ‹‹የማዕድን ሀብት ልማት አዋጅ›› በሚል ስያሜ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የሰጣቸውን መብት እንደሚጋፋባቸው የክልል ተወካዮች ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ከክልሎች፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ከተዛማጅ ዘርፎች ጋር ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለክልሎች የሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነቶች ለፌዴራል መንግሥት የሚሰጥ መሆኑን፣ የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ሥራዎች ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና በምንከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፤›› ብለው፣ ረቂቅ አዋጁ ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 1 (መ) መሠረት ማዕድንን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን መሠረት፣ ክልሎች ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንፃር ለወደፊት አዋጁ ከመተግበር አኳያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በዝርዝር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ የዝግጅት ሒደት ግልጽነትና አሳታፊነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አገራዊ ተፈጻሚነት ባላቸው የአዋጆች ዝግጅት ክልሎች በሒደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ የገለጹት አቶ ዘውዱ፣ ይሁን እንጂ በረቂቅ ዝግጅቱ  የኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ ተሳትፎ አልነበረውም ብለዋል፡፡   

በማዕድን ሀብት ላይ የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር የሚከተል መሆኑን አስታውሰው፣ በዚህ መሠረት ክልሎች አገራዊና የጋራ ጉዳዮችን በሚመለከት ለፌዴራል መንግሥት የሚተው የውስጥ ጉዳዮችን በተመለከተ በራሳቸው የሚወስኑበት የፖለቲካ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ መካተቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 8 የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በትክክል መደንገጉን አክለዋል፡፡

ይህ አንቀጽ ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን ክልሎች ማክበር እንዳለባቸውና በተመሳሳይ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎቹ የሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባራት የፌዴራል መንግሥቱ ማክበር እንዳለበት፣ በአንቀጽ 51 እና 52 ሥልጣናቸውን በዝርዝርና በግልጽ ለይቶ ማስቀመጡን አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የፌዴራል መንግሥት የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶችን አጠቃቀምና ጥበቃ በተመለከተ ሕግ እንደሚያወጣ መደንገጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 2 (መ) መሠረት ደግሞ ክልሎችም የፌዴራል መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል በማለት የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮችን አስመልክቶ ለሁለቱም የመንግሥት መዋቅሮች ሥልጣን ማከፋፈሉን ጠቁመዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል መንግሥት የማዕድን ሀብትን ልማት አጠቃቀምና ጥበቃ ሕግ ሲያወጣ፣ ክልሎች ደግሞ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን ያስተዳድራሉ የሚለው ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ አኳያ መታየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ክልሎች የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ያስተዳድራሉ የሚለው ድንጋጌ ሀብቶቹ የሕዝቦች ማንነት መገለጫ ከሆኑ እሴቶች አንዱና ዋነኛ ስለሆኑና ያላቸውን ቁርኝት በመረዳት የሚወጡ ሕጎችም፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት የሚያስቀምጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ክልሎችም ባላቸው የመሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲያስተዳድሩ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ መሆኑን ገልጸው፣ የማዕድን ሀብት ረቂቅ አዋጅ ይህንን ድንጋጌ የሚፃረር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር ከማንኛውም ባለፈቃድ ከፍተኛ ደረጃ የማዕድን የማምረት ሥራ አምስት በመቶ የፌዴራል መንግሥት ድርሻ እንዳለው፣ ሥራው የሚከናወንበት ክልል ሁለት በመቶ እንደሚኖረው መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አምስት በመቶ ለፌዴራል ሁለት በመቶ ሥራ ለሚካሄድበት ክልል ይይዛል የሚለውን ድንጋጌ፣ የፌዴራል መንግሥት የበለጠ ድርሻ እንዲይዝ ለምን እንደተደረገ ግልጽና አሳማኝ ምክንያት አልተቀመጠም በማለት ጉዳዩ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሦስት በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ የተቀረው ደግሞ ሥራው ለሚካሄድበት ክልል እንዲሆን በማድረግ ቢስተካከል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ መሬት ለማዕድን ሥራዎች ክፍት ይሆናል የሚል ድንጋጌን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ይህ ድንጋጌ ማዕድን የተፈጥሮ ሀብትን በሚያስተዳድረው የክልል አካል የሚዘጋጀውን የመሬት አጠቃቀም ዕቅዱን ግምት ውስጥ አለማስገባቱን ጠቁመዋል፡፡ ማንኛውም መሬት ለማዕድን ክፍት መሆኑን ያትታል ያሉት አንቀጽ፣ ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ከመሆኑም በላይ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታን ከግምት ውስጥ ያላስገባና  እንደ ገና መታየት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 ሚኒስቴሩ ለአገር ጥቅም አስፈላጊ መሆኑን ካመነበት ማንኛውም የማዕድን ሥራ የሚካሄድበት ቦታ ላይ ማዘዝ ይችላል፤›› የሚለውን  በተመለከተ፣ ይህ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ስለሆነ መሬትን ለማስተዳደር በሕገ መንግሥቱ ለተሰጠው አካል መተው ያለበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ ክልሎች ተወያይተውበትና አምነውበት የቀረበ አይደለም፡፡ ረቂቅ አዋጁ በጥቅሉ ሲታይ ትኩረት ያደረገው ክፍል ሦስት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የተለየ ይዘት የያዘው ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የሚደነግገው ክፍል ነው ብለዋል፡፡

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ትኩረት ያደረገው የፈቃድ አሰጣጥ ላይ ወይም ደግሞ ክፍል ሦስት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የረቂቅ አዋጁ የክፍል ሦስት የክልሎችን ሥልጣን ለፌዴራል የመውሰድ አንድምታ ያለው መሆኑን አቶ ኃይሌ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ኃይሌ ገለጻ፣ የኦሮሚያ ክልል አንቀጽ በአንቀጽ ያነሳቸው ጉዳዮች የአማራ ክልልም የሚጋራው ነው፡፡

በዚህ በረቂቅ አዋጅ የተቀመጠው ምክንያት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የቀድሞ አዋጅ የዘገየና ከወቅቱ ጋር የማይሄድ መሆኑ መገለጹን ተናግረዋል፡፡

ለአዋጁ መሻሻል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማዕድን ሚኒስቴር የተሰጠው አራት ተጨማሪ ተግባራት ስላሉ እንደ ምክንያት የቀረበ መሆኑን፣ ከሞላ ጎደል ሊያስኬድ የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ሌሎቹ ምክንያቶች አያስኬዱም ያሉት አቶ ኃይሌ፣ በምሳሌነት ያነሱት ማዕድን በሚመረትበት ክልል ለመጥቀም የሚለው ምክንያት የባሰ ለመጉዳት የሚመስል አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የሰጠውን መብት የሚጋፋ ነው የሚለውን ሐሳብ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች በተጨማሪ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚጋሩት መሆኑን ተወካዮቻቸው ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባኮሎ (ዶ/ር)፣ ‹‹ክልሎች ያነሱዋቸውን ጉዳዮች የእኛም ናቸው፡፡ መድረኩም የተዘጋጀው ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ መድረኩ አዋጁን ለማጠናከር ግብዓት የሚሰበስብበት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከሚያግዙ ዘርፎች አንዱ በመሆኑና በዓመታት ውስጥ የታዩና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው፣ ረቂቁ መሻሻሉ የግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ክልሎች መሻሻል ያለበትን ጉዳዩን ማንሳታቸውን፣ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ከፍተኛ አምራቾች በሚኒስቴሩ ድጋፍ የሚሹ በመሆናቸው በረቂቁ ውስጥ ወደ ፌዴራል መካተታቸው አግባብነት እንዳለው  ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ማዕድን አምራቾች ትልቅ ዕገዛ የሚሹ በመሆናቸው፣ ከክልሎች ወደ ማዕድን ሚኒስቴር እንዲገቡ መደረጋቸው ለአገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...