Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለጋሾች ለሚያደርጉት ድጋፍ እምነት እንዲኖራቸው ተመዘበረ ስለተባለው ዕርዳታ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ...

ለጋሾች ለሚያደርጉት ድጋፍ እምነት እንዲኖራቸው ተመዘበረ ስለተባለው ዕርዳታ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

በሰሜን ኢትዮጵያ ለዕርዳታ እንዲውል የተለገሰው ምግብ የመመዝበሩ ጉዳይ በፍጥነት ካልተቋጨና መፍትሔ ካልተገኘ፣ አሜሪካና ሌሎች ለጋሾች የመልሶ ማቋቋምና የግንባታ ፕሮግራሙን ለመደገፍ ሊኖራቸው የሚገባውን መተማመን እንዳያጠፋው የሚል ሥጋት መኖሩ ተነገረ፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የኢትዮጵያ ሚሽን ምክትል ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቴይን እንደገለጹት፣ ሁለቱ ጉዳዮች የተለያዩ ቢሆኑም ሥጋታቸውን መግለጽ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ለጋሾች ለሚያደርጉት ድጋፍ እምነት እንዲኖራቸው ተመዘበረ ስለተባለው ዕርዳታ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሚስተር ቲሞቲ ስቴን የዩኤስ አይዲ
ኢትዮጵያ ሚሽን ምክትል ዳይሬክተር

‹‹ይኼ ጉዳይ (የዕርዳታ ምግብ ምዝበራው) የአሜሪካ መንግሥትና ሌሎች ለኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ድጋፍ የሚያደርጉት አካላት የሚኖራቸውን መተማመን ያጠፋዋል፤›› ሲሉ የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ መተማመኑ መጥፋት የለበትም ብለዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ተሰናድቶ ለአጋር ድርጅቶችና ለጋሾች ገለጻ የተደረገበት የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ዕቅድ፣ ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ይፋ ሆኗል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ለጋሽና አጋር ድርጅቶች አንደኛው የሆነው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትን የወከሉት ስቴይን፣ ከተዘጋጁት የፓናል ውይይቶች በአንደኛው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ‹‹በመርሐ ግብሩ ላይ ከተገኘሁ አይቀር›› በማለት ነበር ሰሞኑን ስለተፈጠረው የምግብ ዕርዳታ የተናገሩት፡፡

ምዝበራው ተፈጥሯል ወይም አልተፈጠረም የሚል ውይይት ከሚካሄድ፣ በአፋጣኝ ወደ ቀጣዩ ዕርምጃ በመሸጋገር ድጋፉ በእጅጉ ለሚያስፈልጋቸው የሚደርስበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በአፋጣኝ አንድ ላይ ተቀምጠን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ መስጠትና ችግሮቹን ለመፍታት ወደ ቀጣዩ መንገድ መኬድ አለበት፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ድርጅታቸው ምርመራ አድርጎ ደረስኩበት ባለው የምግብ ዕርዳታን መመዝበር ምክንያት መጀመርያ በትግራይ ዕርዳታ አቁሞ የነበረ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ድጋፉን ማቆሙ የሚታወስ ነው፡፡ ከዩኤስኤአይዲ በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በተመሳሳይ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ማቆሙን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ይፋ የሆነበትን መርሐ ግብር በዋነኛነት ሲያስተባብሩ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የዕርዳታ ምግብ ምዝበራን በሚመለከት ከተሳታፊዎች ጥያቄ ተሰንዝሮላቸው ነበር፡፡

ሚኒስትሩም የችግሩን መኖር እንደሚገነዘቡ፣ ከአሜሪካ መንግሥትና ከተራድኦ ድርጅቱ ጋር በመሆንም በጋራ ምርመራ በማድረግ መንግሥት ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም የዕርዳታ ሒደቱን በአዲስ መንገድ መቅረፅና መታረም ያለበትንም ጠንካራ በሆነ ዘዴ እንዲታረም መንግሥት እንደሚያደርግ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በአንክሮ ጉዳዩን እየከታተለው ስለሆነ በምርመራ ውጤቱ የተሳተፉትን ተጠያቂ ያደርጋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ቅዳሜ ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ከዕርዳታ ምግብ ምዝበራው ጋር በተያያዘ መንግሥት በሁሉም ሥፍራዎች የምርመራ ቡድን አሰማርቶ እያጣራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የምርመራና ማጣራት ሒደቱ ባልተጠናቀቀበትና የጋራ መግባባት ባልተደረሰበት ጉዳይ፣ ዩኤስኤአይዲ በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎችና ትንታኔዎች የመከላከያ ኃይላችንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እጅ እንዳለበት እየገለጸ ይገኛል፤›› ሲሉ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትን ወቅሰዋል፡፡

ድርጅቱ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ከማንኛውም የመንግሥት አካል ጋር ያልተመከረበትና በማጣራት ሒደት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በአካባቢዎቹ አጋር ድርጅቶቹ በራሳቸው ድጋፍ እንደሚሰጡና እንዲሁም የዕርዳታ ሥርጭቱና ቁጥጥሩ በራሳቸው አደረጃጀት የማካሄድ መሆኑን ዘንግተዋል ሲሉም፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትንና የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ዕርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው አክለዋል፡፡

‹‹ተፈጠረ የተባለውን ችግር ከመንግሥት መዋቅርና ሥርዓት ጋር ብቻ በማያያዝ፣ ራሳቸውን ከውንጀላው ለማራቅ የሞከሩበት መንገድ ተቀባይነት የሌለው ነው፤›› ሲሉ ለገሰ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...