Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአባላት ቅሬታና ለአመራሮች የጥቅም ምንጭ እየሆኑ ነው ተባለ

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአባላት ቅሬታና ለአመራሮች የጥቅም ምንጭ እየሆኑ ነው ተባለ

ቀን:

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን በሚከተለው ሕግን ያላማከለ አሠራር፣ ክትትልና ቁጥጥር ማነስ የተነሳ ማኅበራቱ ለአባላት የቅሬታ ምንጭ፣ ለተወሰኑ አመራሮች ደግሞ የጥቅማ ጥቅም ምንጭ መሆናቸው ተነገረ፡፡  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኮሚሽኑን የ2013/14 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ሲገመግም ነው ይህ የተነገረው፡፡

በኦዲት ሪፖርት ግምገማ መድረኩ ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶ አደሮች፣ ለመሠረቷቸው አባላትና ማኅበረሰቦች የቅራኔ ምንጭ እየሆኑ ነው፤›› ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሱመያ ደሳለው ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሱመያ አንዳንዱ ለአመራሩ ብቻ የጥቅማ ጥቅም ምንጭ በመሆን ከሌላው ለአንዱ የሚጠቃቀምበት አሠራር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፣ ማኅበራቱ የፀረ ሙስና መቆጣጠሪያ ሥርዓት የሌላቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቦች የሚበዘበዙበት አንዱ መንገድ ሆነዋል ብለዋል፡፡

‹‹ከብዙ አባላት ገንዘብ ይሰበሰባል፣ ነገር ግን የተወሰነ አባል የሚጠቀምባቸው ተቋማት እየሆኑ ነው፤›› ብለው፣ ኮሚሽኑ እስከ ታች ድረስ መፈተሽና መታየት አለበት ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ሱመያ አክለውም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአገራዊ ምርት አንፃር ወደ ላይ የሚስፈነጠር አስተዋጽኦ ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ወደ ታች እያሽቆለቆሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመተጋገዝና በትኩረት ካልተሠራ ተቋሙ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ተቋም የሚገነባው አሠራርና ሥርዓት ሲኖረው ቢሆንም በኮሚሽኑ ውስጥ የታየው ግን ሥርዓት፣ አሠራርና ደንብ እንደሌለው ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ አዋጅ የወጣለት ቢሆንም የሚሠራው ሥራ ግን በዘፈቀደና በግለሰብ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከተሰጠው ሥልጣን፣ ዓላማና ተልዕኮ ጋር እኩል እየተራመደ እንዳልሆነና የግብይት ሥርዓት ችግር እንዳለበት የገለጹት ምክትል ሰብሳቢዋ፣ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ኦዲት ተደርጎ የማይሻሻል ተቋም በመሆኑ በመንግሥት ጠንካራ ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ አዋጅ ከወጣለት በኋላ ለሰባት ዓመታት ደንብና መመርያ ሳይዘጋጅ እንደገና አዋጅ ይሻሻልልኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ከአባላቱ ቅሬታ የተነሳበት ሲሆን፣ በመድረኩ የተገኙት የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የሰጡት መልስ ቋሚ ኮሚቴውን የሚያሳምን አልነበረም፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ኮሚሽኑ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ኦዲት ተደርጎ ግኝቶቹን እንዲያርም አስተያየት የተሰጠው ቢሆንም፣ በኦዲተር በተሰጠው አስተያየት ላይ ማስተካከያ ሳያደርግ በምክር ቤቱ መገኘቱ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ተቃውሞ ተነስቶበታል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ላይ በተለያዩ ጊዜያት የክዋኔ ኦዲትና የክትትል ኦዲት ሥራ ቢሠራም፣ ኮሚሽኑ ግኝቶችን በማስተካከል ለውጥ አለማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ እንዳሉት፣ ኮሚሽኑ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተሰጠው የኦዲት ግምገማ መደርደሪያ ላይ ከመቀመጡ ውጪ ለውጥ አልታየም፡፡ ወ/ሮ መሠረት የኮሚሽኑን እንቅስቃሴና ተግባር በፈሊጥ ለማስረዳት፣ ‹‹ሰውየው ሚስትህ ወለደች ወይ ቢሉት፣ ማንን ወንድ ብላ ብሎ መለሰ አሉ፤›› የሚል ምሳሌ አቅርበዋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቁጥር 106,000 መድረሱን ገልጸው፣ ነገር ግን በአባላት ቁጥር እንጂ ጥራት የላቸውም ብለዋል፡፡  

በተጨማሪም ማኅበራትን ለማደራጀት ሕግን መሠረት በማድረግ መሠራት ቢኖርበትም፣ አሠራሩ ሕግን ያልተከተተለ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበራቱ ትልቅ የሕዝብ ገንዘብ የያዙ ቢሆንም፣ በሕዝብ ገንዘብ ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ሥርዓት ወጥ የሆነ መመርያ የሌለውና ዓመቱን ጠብቆ የተጠያቂነት ሥራ የማይከናወንበት በመሆኑ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ መካሄድ እንዳለበት ዋና ኦዲተሯ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...