Tuesday, October 3, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉየኢትዮጵያጊግ ኢኮኖሚ እድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ

የኢትዮጵያጊግ ኢኮኖሚ እድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ

Published on

- Advertisment -

በኢትዮጵያ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚን መጠን የሚያሳይ አስተማማኝ ስሌት ማግኘት አዳጋች ነው። ያም ሆኖ፣ በአመዛኙ ወጣቶች የሚበዙበት የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት በፍጥነት ወደ 120 ሚሊዮን ከመገስገሱ ጋር ተያይዞ፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ መደበኛ ያልሆነ ሥራ የሚሠሩ የቁርጥ ሥራ ሠራተኞች እንደሚኖሩ አያጠያይቅም።

የቁርጥ ሥራ (gig) የሚለው መጠሪያ ከተለምዷዊው የሙሉ ጊዜ የሥራ ቅጥር በተለየ፣ እንደ ሁኔታው ሊለዋወጥ የሚችል፣ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ቅጥርን መሠረት ያላደረገ የሥራ ዓይነትን የሚያመለክት ነው።

ይህ የሥራ ምድብ ዘርፈ ብዙ የሥራና የሠራተኛ ዓይነቶችን አጠቃልሎ የሚይዝ ሲሆን፣ ከቤት ሠራተኞችና የቀን ሠራተኞች አንሥቶ፣ የድረ ገጽ ዴቨሎፐሮችን፣ ጥናትና ምርምር የሚሠሩ አማካሪዎችን፣ ግራፊክ ዲዛይነሮችንና የመሳሰሉትን፣ የየጊዜው ሥራቸው የአጭር ጊዜ ሆኖ በቋሚነት የተወሰነ የሥራ ቦታ ላይ መገኘት የማያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚያቅፍ ነው። እንዲህ ያሉ ሠራተኞች ሁሉ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ የጊዜያዊ ቅጥር ሠራተኞች ተደርገው የሚቆጠሩ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እያደገ መጥቷል፤ ተያይዞም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዋናነት ዲጂታል ዘዴዎችን በመጠቀም ከጊዜያዊ እና ቁርጥ ሥራ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የሚሠጡ የግሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋናዮች እየተበራከቱ መጥተዋል።

እንደ “ራይድ” ያሉ የጥሪ ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ (ride-hailing) ፕላትፎርሞች ለብዙኃኑ የሚስማማ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔትን መሠረት ያደረገ የቁርጥ ሥራ በመጀመር አብዛኛውን ጊዜ ፈር ቀዳጅ ተደርገው ይቆጠራሉ። አሽከርካሪዎች በራሳቸው ምርጫ አገልግሎቱን እንዲሰጡ የሚያስችሉት እነዚህ ፕላትፎርሞች፣ በምዕራቡ ዓለም የተለመደውን የኡበር (Uber) ሞዴል ከማንጸባረቅ አልፈው፣ ኡበር የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚን በስፋት በማስተዋወቅ የተጫወተው ሚና ማሳያ ጭምር ናቸው።

የጥሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ፕላትፎርሞች የተቀዳጁትን ስኬት ተከትሎ፣ እንደ ሁኔታው ሞተር ብስክሌት እየተጠቀሙ ፈላጊ ጋር ዕቃዎችን የሚያደርሱ ንግድ አገልግሎቶች መታየት ጀምረዋል።

አሁን አሁን የጥሪ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች፣ ዕቃ የማድረስ አገልግሎት ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ወይም ደግሞ የማስጠናት ሥራና የመሳሰሉትን የሚሠሩ የቁርጥ ሥራ ሠራተኞችን ከዘመድ ወዳጆቻችን መካከል ማግኘት የተለመደ ሆኗል። በፕሮፌሽናሉ ዓለምም ቢሆን፣ ብዙዎች ከተለምዷዊ የሙሉ ጊዜ ሥራዎች ይልቅ በስምምነት የሚሠሩ ጊዜያዊ ሥራዎችን መምረጥ ጀምረዋል፤ የሙሉ ጊዜ ሥራን ቢሆን ብዙዎቹ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የቁርጥ ሥራ ማፈላለጉን ተያይዘውታል።

በተጨማሪም፣ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ወጣት ኢትዮጵያውያን ዴቨሎፐሮች እንደ አፕወርክ (Upwork) ባሉ ቢዝነሶችን ከሠራተኞች ጋር በሚያገናኙ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርሞች ላይ በመሥራት ይተዳደራሉ፤ ችሎታቸውንና ክህሎታቸውንም ለዓለም አቀፉ ገበያ ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚውን እያቀጣጠሉ ከሚገኙት አነሣሾች መካከል የቴክኖሎጂ እድገት፣ የሞባይል ቴክኖሎጂ ሚና ከፍ እያለ መምጣት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛነት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የቁርጥ ሥራ አዝማሚያ ተጽዕኖ ይጠቀሳሉ።

በሺሕዎች ለሚገመቱ አሽከርካሪዎች መተዳደሪያ ከሆኑት የጥሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ፕላትፎርሞች በተጨማሪ፣ ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ተጠቃሚዎች ተስማሚ ከሚባሉት የኢትዮጵያ ዋና ዋና የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርሞች መካከል ጉዳዮን (GoodayOn) እና ታስክሞቢ (Taskmoby) ይነሣሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ይበልጥ ስኬታማ የሚባለው (GoodayOn) የደንበኝነት ክፍያ የሚጠየቅበት የፕሪሚየም አገልግሎት መጀመር ችሏል። መተግበሪያው ከ100 ሺሕ ጊዜ በላይ ዳውንሎድ የተደረገለት ጉዳዮን (GoodayOn)፣ እንደ የቤት ሠራተኞች፣ አስጠኚዎች፣ ሞግዚቶች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ የኤሌክትሪክ ሠራተኞች የመሳሰሉትን አገልግሎት ሰጪዎች ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጋር ያገናኛል።

ጉዳዮን (GoodayOn) ለአንዳንድ አገልግሎቶቹ ማስከፈል ለመጀመር የወሰነው፣ ከሁለት ዓመት በላይ ሥራ ላይ ከቆየና ከ250 ሺሕ በላይ የአገልግሎት ጥያቄዎችን ካስተናገደ በኋላ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ወላጆችን ከአስጠኚዎች እንደሚያገናኘው ሀሌታ አስጠኚዎች (Haleta Tutors) እና እንደ ለድርድር ክፍት የሆነ አመቺ የሞግዚት አገልግሎት የሚያቀርበው ሞግዚት (Mogzit) ያሉ ዘርፍ ለይተው አገልግሎት የሚሰጡ ፕላትፎርሞችም መታየት ጀምረዋል።

ከእነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርሞች አብዛኞቹ በአንድሮይድም ሆነ በአይኦኤስ (iOS) የሞባይል መተግበሪያዎች እንዲሁም በጥሪ ማዕከሎች የሚገኙ ሲሆኑ፣ የጥሪ ማዕከል አማራጭ መኖሩ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ያልሆኑ ደንበኞችን ከመድረስ አኳያ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም፣ እነዚህ ፕላትፎርሞች ለፈላጊው በቅርብ የሚገኙ የቁርጥ ሠራተኞችን ለማገናኘት መገኛ ስፍራን ለይቶ የሚያመለክት (geolocation) ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ።

በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ በቅርቡ ይበልጥ እድገቱን የሚያፋጥን ዋነኛ ግፊትም አግኝቷል። በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዋና ዋና አዳዲስ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ገበያ ኩባንያ (Gebeya Inc.) እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን (Mastercard Foundation) በጋራ በመሆን “መሥራት” (Mesirat) የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት አስተዋውቀዋል።

“መሥራት”፣ የሶፍትዌር አገልግሎት አቅራቢ የሆነውና በመላው አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው ገበያ ኩባንያ እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የፈጠሩት አጋርነት ውጤት ነው። ፕሮጀክቱ 100 ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች የራሳቸውን ልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርሞች እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ የአምስት ዓመት ፕሮግራም ነው።

ሁለቱ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች አጋሮቻቸው የጋራ ልምዳቸውን እና ችሎታቸውን እንዲሁም ለፕሮግራሙ የተመደበለትን 48 ሚሊዮን ዶላር በመጠቀም የገበያን ሞዴል ቀድተው በቱሪዝም እና ሆቴል፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በጤና፣ በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በፕሮፌሽናል አገልግሎቶች፣ በትራንስፖርት፣ እንዲሁም በመዝናኛ ዘርፎች ላይ መቶ ፕላትፎርሞችን ለመፍጠር አብረው ይሠራሉ።

ፕሮጀክቱ ለሁለት ሚሊየን ወጣቶች ገበያ የማፈላለግ ክህሎት ለማስጨበጥ ያቀደ ሲሆን፣ አንድ ሚሊየን የሚሆኑትን (ከዚህም 70 ከመቶዎቹ ሴቶች፣ 10 ከመቶዎቹ ደግሞ የልዩ ልዩ ጒዳትና መድልዎ ተጠቂ የሆኑ ወጣቶች) ሰብዓዊ ክብር ያለውና ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ቁርጥ ሥራ እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ ነው።

ፕሮግራሙ የተሳካ ይሆን ዘንድ፣ መሥራት የሚተገበረው ልዩ ልዩ አጋሮችን በማሳተፍ ነው። ከአጋሮቹ መካከል ኤ.ሲ.ኢ አማካሪዎች (ACE Advisors)፣ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ (American College of Technology (ACT))፣ ሸጋ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ (Shega Media & Technology)፣ ዘ ኧርባን ሴንተር (The Urban Center)፣ ሴንተር ፎር አክሰለሬትድ ዉመንስ ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት (Center for Accelerated Women’s Economic Empowerment (CAWEE)) እንዲሁም ላውረንዱ እና አጋሮቹ (Laurendeau & Associates) ይገኙበታል።

እነዚህ ተስፋ ሰጪ ጥረቶች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፉ መረጃ አንጻር ሲታይ ገና በጅማሮ ላይ የሚገኝ ነው። በ2019 እ.ኤ.አ ማስተርካርድ ኩባንያ የሠራው ዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቁርጥ ሥራ በአጠቃላይ ድምር 204 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል። ከዚህም በላይ ይህ መጠን በ2023 እ.ኤ.አ 455 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ50 ሚሊዮን ጥቂት የዘለለ የሕዝብ ብዛት ያላት ጐረቤት አገር ኬንያ፣ በ2020 እ.ኤ.አ የማስተርካርድ ኩባንያ በሠራው ሌላ ዳሰሳ ጥናት መሠረት አምስት ሚሊዮን የቁርጥ ሥራ ሠራተኞች ነበሯት። በተጨማሪም ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ከእነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ከኢንተርኔት መረብ ውጭ ካለ ቁርጥ ሥራ ይልቅ ኦንላይን መሥራትን የሚመርጡ ናቸው።

በ2020 እ.ኤ.አ ሴፊየስ ግሮውዝ ካፒታል ፓርትነርስ (Cepheus Growth Capital Partners) የተሰኘ የኢትዮጵያ የግል ሀብት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ተቋም ባወጣው የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ (Ethiopia’s Digital Economy) የሚል ሪፖርት መሠረት፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርሞች ከቁጥጥር መስፈርቶች፣ ከአስተማማኝ ወይም ዘላቂ አገልግሎት አቅራቢዎች እጥረት፣ እንዲሁም ኢ-መደበኛ የሆኑ ሥራ ማገናኛ አማራጮች ከመግነናቸው ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በሥራ ላይ ያሉት የአሠሪና ሠራተኛ ሕጎችና መመሪያዎች ለቁርጥ ሥራ ሠራተኞች የተለየ የሥራ ሁኔታ በቂ ምላሽ አይሰጡም። ይህም ሠራተኞቹም ሆነ ፕላትፎርሞቹ ላይ ከግብርና ሕግ አክብሮ ከመሥራት ጋር በተያያዘ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል።

ከዚህም በላይ ቁርጥ ሥራ ጊዜያዊ ከመሆኑ አንጻር፣ ከሥራ ዘላቂነትና ከማኅበራዊ ዋስትና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአሳሳቢነት ይነሣሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቁርጥ ሥራ የሚያስገኘው ገቢ አስተማማኝ አለመሆኑና እንደ ጡረታ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች የሌሉት መሆኑ በሥጋትነት ይጠቀሳሉ።

በከተማና ገጠር አካባቢዎች መካከል ያለው የቴክኖሎጂ እውቀትና ተደራሽነት ሰፊ ክፍተት እነዚህን ተግዳሮቶች ያባብሳል።

በ2013 ዓ.ም የቀድሞው የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን የአሁኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር፣ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚውን ተጽዕኖ በመገንዘብ በእንግሊዝኛው ምኅፃረ ቃል FROG (Freelancing, Outsourcing, and Gigs) የተሰኘ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ነበር። ግብረ ኃይሉ የተቋቋመበት ዓላማ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን የኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ማጠንጠኛ ማድረግ ነበር። ግብረ ኃይሉ ጊዜያዊ ስምምነትን መሠረት ያደረገ ሥራ (freelancing)፣ ሥራን ከአሠሪው ድርጅት ማዕቀፍ ውጭ ባሉ ሠራተኞች ማሠራት (outsourcing) እንዲሁም የቁርጥ ሥራ (gig) የቢዝነስ ሞዴሎች መካከል ያለውን ቁርኝት ለይቶ ማውጣት፣ እንዲሁም በጎ ልምዶችና መረጃዎችን የማጋራት ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።

ኢትዮጵያ እድገቷን ካፋጠነች፣ የጀመረቻቸውን ጥረቶች ካጠናከረች እና ዘርፉ ያሉበትን ተግዳሮቶች መወጣት ከቻለች፣ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚው ማበብ ብዙ ዕድሎችና ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር የምትቸገር አገር ናት።  ሰዎች የሥራውን ዓለም ይቀላቀላሉ። በ2021 እ.ኤ.አ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ አሁን ላይ 17.9 በመቶ የሆነው የከተማ የሥራ አጥነት መጠን እየጨመረ ይሄዳል።

ከዚህ አኳያ፣ የቁርጥ ሥራው ኢኮኖሚ በከፊል መፍትሔ ይሆናል። በኢትዮጵያ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ እየተስፋፋ ሲሄድ፣ ብዙ ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል። እንደ ሁኔታው ሊመቻች የሚችል የሥራ ሁኔታ፣ የሥራና ሕይወት ሚዛንን የተሻለ መጠበቅ፣ የሥራ ፈጠራ ዕድሎች፣ የፈጠራ ክህሎት መዳበር፣ የተሻለ የፋይናንስ አካታችነት እንዲሁም ክህሎትን ማዳበርን ከማነቃቃት አንጻር ጠቀሜታዎች ይኖሩታል።

ከዚህ የተነሣ፣ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ በዘላቂነት እንዲያድግ ለማስቻል ፖሊሲ አውጪዎች የቁርጥ ሥራ ሠራተኞችንና ፕላትፎርሞችን በተሻለ መልኩ በሚያካትት መልኩ ሕጎችና መመሪያዎችን መልሰው መቃኘት ይኖርባቸዋል። ይህም የሠራተኞች ጥበቃ፣ የግብር ጉዳይ እንዲሁም የአሠራር አግባብን በተመለከተ ከቁርጥ ሥራ የተለየ ባሕርይ አንጻር የተሰናዱ አሠራሮችን መዘርጋትን የሚያካትት ነው። በተጨማሪም ሁሉም እኩል ተደራሽነት እንዲኖረው በማድረግ ከቴክኖሎጂ እውቀትና ተደራሽነት አንጻር ያለውን ከፍተኛ ልዩነት ለማጥበብ፣ ብሎም በልዩ ልዩ ዘርፎች አስተማማኝና ዘላቂ አገልግሎቶች እንዲኖሩ ቅድሚያ በመስጠት መሥራት ያሻል።

በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ እና እንደ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ባሉ ዓለም አቀፋዊ አጋሮች መካከል ትብብር መፍጠር የኢትዮጵያን የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ ሙሉ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም ወሳኝ ነው። በዚህ አዲስ የሥራ መድረክ አተያይ የሚገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ አካታች፣ እንደ ሁኔታው ተለዋዋጭ እና ብዝኃነት ያለው፣ የዜጎቿን አቅም የሚጨምርና አገሪቱን ወደ በለጸገ መጪ ጊዜ የሚያስፈነጥር የሥራ ገበያ መፍጠር ትችላለች።

የኢትዮጵያ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ እየደረጀ ሲሄድ፣ የፈጠራና ለውጥ ሞተር የመሆን አቅም አለው፤ በዚህም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ነገን እንዲገነቡ ያስችላል። ያሉትን ዕድሎች እየተጠቀሙና የተጋረጡበትን ተግዳሮቶች እየፈቱ መጓዝ፣ የቁርጥ ሥራ ኢኮኖሚ ያለውን ሙሉ አቅም አውጥቶ በመጠቀም ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ብሩሕ መጪ ጊዜን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

የፎቶ መግለጫ (ካስፈለገ) – በኢትዮጵያ ከሚገኙ ኢንተርኔትን መሠረት ያደረጉ አንዳንድ የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርሞች የሚያሳይ የሞባይል ስልክ ስክሪን

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

‹‹ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚገኘው ኢኮኖሚውን በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን ነው›› ውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር/ኢንጂነር)፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ

በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው...

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ‹‹የዓለም ማኅበር፣ የዓለም...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment - an Introduction to the...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም ምክንያት መስጠት አያስፈልግም ነበር፡፡ ዛሬን...

ተመሳሳይ

በአፍሪካ የገንዲ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደረሰ

የአፍሪካ እንስሳት ትራይፓኖሶሚያሲስ (AAT) በመባል የሚታወቀው የገንዲ በሽታ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የእንስሳ እርባታ...

ታምሪን ሞተርስ አዲስ ያስመጣዉን ሱዙኪ ኢኮ ቫን ሞዴል በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ

ለአካባቢ ሥነ ምህዳር ምቹ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ከሚያመርተው እና በዓለም ታዋቂ ከሆነው የሱዙኪ ኩባንያ ጋር...

የላይፍላይን አዲስ የቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ አገልግሎት ድርግጅት በጤናው ዘርፍ የቁርጥ ሥራ (ጊግ) ኢኮኖሚን የመገንባት ጉዞ

ዶ/ር ሰለሞን ደሳለኝ  ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሕክምና የተመረቀው በ2009 ዓ.ም. ማብቂያ...