በኢትዮጵያ በየቦታው ተደጋግሞ የሚከሰተው የፀጥታ ችግር አገር አቀፍ ቀውስ ከሆነ መከራረሙ ይነገራል፡፡ በየአካባቢው የሚያገረሹ አለመረጋጋቶችን በአግባቡ ተቆጣጥሮ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የመቻል ጉዳይ አገር አቀፍ አጀንዳ ከሆነም ሰነባብቷል፡፡
በለውጡ ማግሥት አገሪቱን ለማረጋጋትና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት በፀጥታው ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸው ይነገራል፡፡ የፀጥታ ዘርፉን ሪፎርም የማድረግ ሥራ ደግሞ፣ የፀጥታ አካላትን አቅም የማጠናከርና የፀጥታ ተደራሽነት ሽፋንን የማሳደግ ሥራዎችን የጨመረ እንደሆነም ይነገራል፡፡
በለውጡ ማግሥት ቅድሚያ ተሰጥቶታል ከተባለው የፀጥታ አካላትን ሪፎርም ማድረግ በኋላም ቢሆን፣ በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን የመቻል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኖ መቀጠሉ ይሰማል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የፀጥታ አካላት ሰላም በማስከበር ሒደት የሚወስዷቸው ዕርምጃዎችም የውዝግብ መነሻ ሲሆኑ ይታያል፡፡
የፀጥታ አካላት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም በተደጋጋሚ መታየቱ አሳሳቢ እየተባለ ነው፡፡ ሰላም ለማስፈንና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች፣ ያልታሰበ አደጋ ወይም ከተገመተው በላይ ጉዳት ማስከተላቸው ተደጋግሞ የሚታይ ትራጄጂ እየሆነ ነውም ይባላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት፣ ‹‹ሰዎች ሁሉ ፀጥ ረጭ ባለው ለሊት በሰላም ተኝተዋል፡፡ ምክንያቱም የማይተኙ ሰላም አስከባሪዎች ያለ እንቅልፍ ስለሚያድሩ ነው፡፡ እናንተ የሰላም ዘቦች የብርሃን ጥቅም የሚታወቀው ጨለማ በሚከበን ወቅት እንደ መሆኑ፣ የሕግ አስከባሪዎች ሚና የሚታወቀውም ሰላምና ደኅንነታችን አደጋ ላይ ሲወድቅ ነው፤›› በማለት ስለፀጥታ አስከባሪዎች ሚና ተናግረው ነበር፡፡
የፀጥታ አስከባሪዎች በኢትዮጵያ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ያሉት በቂ ደመወዝ ሳይከፈላቸው፣ ከረሃብ፣ ከጥምና እንዲሁም ከአካልና ከሕይወት አደጋ ጋር ተጋፍጠው የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሥራ እንደሚሠሩ ይታወቃል፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥም ሆነው የአቅማቸውን ያህል የሰላም ማስከበር ሥራ ባይሠሩ ኖሮ በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት ከእስካሁኑም በከፋ፣ የዜጎች ሕይወትና ንብረት አደጋ ላይ የመውደቁ አጋጣሚ በተባባሰ ነበር የሚሉ አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለዚህ ይመስላል፣ ‹‹ለእናንተ ሚናና ጥረት እምብዛም ክብር አልሰጠንም፤›› ሲሉ የፀጥታ አካላትን ሚና ያደነቁት፡፡
‹‹ተኝተን የምናድረው፣ አርሰን የምንበላው፣ አገራችንን ለማበልፀግ የምንጥረው እናንተን ተማምነን ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ፣ ሁሉም የሰላምና ደኅንነት ተቋማት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚፈለገው የኢትዮጵያ ብልፅግና መሠረት ሰላም ሰለሆነ ነው፤›› በማለት ጭምር ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ተቋማትን ድርሻ ከፍ አድርገው ያወሱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ብዙዎችን የሚያግባባ ቢሆንም፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፀጥታ ማስከበር ሒደት እያጋጠሙ ያሉ የሕግ ጥሰቶች መበራከት ዘርፉ በትኩረት እንዲታይ የሚጋብዙ ሆነዋል፡፡ በሰላም ማስፈን ስም የፀጥታ አካላት ሲፈጽሙት የሚታየው ከሕግ ማስከበር ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት አሳሳቢ ሆኗል እየተባለ ነው፡፡
የፀጥታ አካላት የፈጸሟቸው ተመጣጣኝ ያልሆኑ የኃይል ዕርምጃዎች፣ ከሕጉና ከሥነ ምግባሩ ያፈነገጡ የሚባሉ ድርጊቶች በቪዲዮ ጭምር እየተቀረፁ በማኅበራዊ ሚዲያዎች መሠራጨታቸው የተቋማቱን መልካም ገጽታን የሚያጠለሽ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
‹መለዮ ለባሾች› ተብለው በኩራት የሚጠሩ ‹የአገር ዘብ› እየተባሉ የሚወደሱ የሰላም አስከባሪ ተቋማት በጥቂት ስህተቶችና ግድፈቶች ክብራቸው መጠልሸቱና ተአማኒነታቸው መሸርሸሩ፣ የወቅቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑ እየተወሳ ነው፡፡
ከሰሞነኛው የአንዋር መስጅድ አካባቢ ተቃውሞ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ መስጅዶች ተቀስቅሰው የነበሩ ተቃውሞዎችን ለማስቆም፣ የሕግ እስከባሪዎች ዕርምጃ ተመጣጣኝነት ጥያቄ ሲነሳበት ከርሟል፡፡
አንድ ሰሞን በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ተቀስቅሰው የነበሩ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ፖሊሶች ከባድ ኃይል መጠቀማቸው ሲተች ነበር፡፡ በተለይ ከፍተኛ የፖሊስ ዱላ ያረፈባቸው ተማሪዎችና ሌሎች ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ በቪዲዮዎች ተቀርፆ መሠራጨቱ ደግሞ ጉዳዩ ግነት እንዲያገኝ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡
በጋምቤላ ክልል ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይሎች የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ ዕርምጃ መውሰዳቸው ሪፖርት መደረጉ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ጉዳዩ ከፍ ብሎ እንዲነሳ ተጨማሪ ምክንያት ነበር፡፡ በሲዳማ ክልልም የፀጥታ አካላት ዕርምጃ አወሳሰድ በተመሳሳይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡
በሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ ለሰላማዊ ዜጎች ሕይወት መጥፋት መነሻ ሆኗል ተብሎ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በተለይ በከረዩ የሚቺሌ አባገዳዎች ግድያ መነሻነት፣ የፀጥታ አካላት ኃይል አወሳሰድ ጉዳይ በርካታ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡
ሦስቱን ክልሎች ማለትም ትግራይ፣ አፋርና አማራን አዳርሶ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ለሰብዓዊና ለጦር ወንጀሎች የቀረቡ አደጋዎች በሁሉም የጦርነት ተሳታፊ ኃይሎች ተፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች መቅረባቸው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አደባባዮች ስሟ ተደጋግሞ እንዲነሳ ያደረጉ መነሻዎች ነበሩ፡፡
ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ላይ የሰብዓዊ መብቶች አያያዟን ያስገመገመችው ኢትዮጵያ፣ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን አጣርቶ ለፍትሕ የማቅረብ ሥራን በተመለከተ ተወቃሽ መሆኗ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ሲባል ነው የቆየው፡፡
ከሕግ አከባበርና ከሰላም ማስከበር ሥራ ጋር የተያያዘው በፀጥታ አካላት ላይ የሚነሳው ቅሬታ በቪዲዮ ቅጂዎች በተደጋጋሚ መጋለጡ፣ በሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች በተደጋጋሚ መነሳቱ ጉዳዩ በትኩረት ሊታይ ይገባል የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራቸውን ሲሠሩ ሕግን ተከትለውና የፀጥታ አከባበር ሳይንሳዊ መርሆዎችን ተመርኩዘው መሆን እንዳለበት ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ የሕግ አስከባሪዎች በሕጎችና በሥነ ምግባር መመርያዎች የተቀመጡ የሰላም ማስከበር መርሆዎችን በዕለት ተዕለት ሥራቸው ካልተገበሩ ተጠያቂነት እንደሚከተል ተደጋግሞ ይወሳል፡፡
ለፖሊስ ሳይንስ ሥልጠና “Police Duties and Responsibilities in Controlling Riot” በሚል በቀረበው የሥልጠና ማኑዋል ላይ፣ የፀጥታ ኃይሎች የፀጥታ ችግር ሲፈጠር ሥጋቱን ለመቆጣጠር መከተል ስለሚገባቸው ሳይንሳዊ መርሆዎች በዝርዝር ተቀምጧል፡፡
ፖሊስ (የፀጥታ ኃይሎች) በሥራቸው ትክክል የሆነውንና ‹ትክክል ያልሆነውን ነገር አመዛዝኖ መበየን› ላይ መመሥረት እንዳለባቸው የሚያስረዳው ማኑዋሉ፣ የኃይል ዕርምጃ ከመውሰድ በፊት በማሳመን፣ በመሸምገልና በመደራደር ችግሮችን የመቋጨት አማራጮች እንዳሏቸው ሁሌም መረዳት እንዳለባቸው ይጠቅሳል፡፡
የፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል አማራጭን ለመጠቀም የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ኃይል እንደሚጠቀሙ የሚገልጸው ሰነዱ፣ ኃይል ሲጠቀሙ ግን ‹‹ሕጋዊነት (Legality/Responsibility)፣ አስፈላጊነት (Necessity)፣ እንዲሁም ተመጣጣኝነት (Proportionality)›› የተባሉ ሦስት መሠረታዊ የኃይል አጠቃቀም መሥፈርቶችን ተከትለው መሆን እንዳለበት ይዘረዝራል፡፡
የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ የሆኑትና ከፍተኛ የፖሊስ ሳይንስ ሥልጠናዎችን እስከ ድኅረ ምረቃ የተከታተሉት ኮማንደር ግሩም ውብሸት በበኩላቸው፣ በአድማ ብተና ሒደትና በጦር መሣሪያ አጠቃቀም ላይ መሥፈርቶች መቀመጣቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹ለአንድ የሕግ ጥሰት ፈጽሟል ተብሎ ለሚጠረጠር ሰው መጥሪያ ከመስጠት ጀምሮ ሕግ ማስከበር የራሱ ሥርዓት አለው፡፡ ግለሰቡ እንቢ ቢል መለስተኛ አካላዊ ጫና ከማሳደር ጀምሮ በግድ ይዞ እስከ መውሰድ የሚደርስ ደረጃውን ጠብቆ እያደገ የሚሄድ ኃይል ሕግ አስከባሪው ሊጠቀም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የመጨረሻውን የማስገደጃ ኃይል ወደ መጠቀም የሚገባው ብዙ ሒደቶች ታልፎ ነው፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡
ተቃውሞም ሆነ ብጥብጥ ሲፈጠር ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰዱ አስፈላጊነት ሲታመንበት ሕጋዊ፣ አስፈላጊና ተመጣጣኝ የሕግ ማስከበር ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያስረዱት ኮማንደር ግሩም፣ በዚህ ወቅትም ደረጃውን ጠብቆ የሚያድግ የኃይል ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
‹‹ተቃውሞ የሚያካሂዱ ወገኖች ሕገወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን መጀመሪያ በቃል ትነግራለህ፡፡ መጥተው መነጋገር እንደሚችሉ ወይም ችግራቸውን እንዲያቀርቡ ታሳውቃለህ፡፡ እንቢ የሚሉ ከሆነና ሕገወጥ በተባለው አድማ ከገፉበት ደግሞ የፀጥታ ማስከበር አቅምህን በሠልፍና በትጥቅ ታሳያቸዋለህ፡፡ እዚህ ድረስ ሄደህ እንቢ ካሉ ደግሞ በሠልፉ ኃይላቸውን ትበታትናለህ፡፡ ከዚህ ካለፈ ውኃ፣ ጭስ፣ ዱላና የመሳሰሉ አድማ መበተኛዎችን ትጠቀማለህ፡፡ የተኩስ ወይም የጥይት ላይ የምትደርሰው ደረጃውን ተከትለህ ያሉትን አማራጮች አሟጠህ ከተጠቀምክ በኋላ ነው፤›› በማለትም ኮማንደሩ የሕግ አከባበር ሳይንሱን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ በመስጅዶች ዙሪያ በተነሱ ተቃውሞዎች የሕግ አስከባሪዎች የወሰዱትን ዕርምጃ ተከትሎ፣ ‹የፀጥታ አካላት አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል የመጠቀም አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱን› ባወጡት መግለጫ ገልጸው ነበር፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹በዚህ የተነሳ በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየደረሱ ነው፤›› ማለታቸውም ተነግሯል፡፡
ይህን ጉዳይ በሚመለከት ኮሚሽናቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር በተደጋጋሚ ሪፖርት ማድረጉን ዳንኤል (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን ለሰው ሕይወት ሕልፈትና አካል ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ የፀጥታ አካላት ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ፤›› ጠይቀዋል፡፡
ሌላኛው በተደጋጋሚ ሪፖርቶቹ የፀጥታ አካላትን ሕግ መተላለፍ ሥጋት የሚያነሳው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በበኩሉ፣ በዚሁ ጉዳይ ከሰሞኑ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡
ኢሰመጉ ‹በመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚወሰዱ ተገቢ ያልሆኑ የኃይል ዕርምጃዎች ሊቆሙ ይገባል› በሚል ባወጣው መግለጫው፣ ከሰሞኑ በመስጂዶች የተነሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ማሳያ አድርጎ ያቀርባል፡፡
ከዓለም አቀፍ ሕጎች በተጨማሪ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው መብት ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልጽ መደንገጉን ኢሰመጉ ጠቅሷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 16 ደግሞ ማንም ሰው በአካሉ ላይ ከሚደርስ ጉዳት የመጠበቅ መብት እንዳለው አክሎ ገልጿል፡፡
ከዚህ በመነሳትም የመንግሥት የፀጥታ አካላት በንፁኃን ላይ የሚወሰዱት ተገቢና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል ዕርምጃ እንዲቆም ኢሰመጉ ይጠይቃል፡፡ በሰዎች ላይ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና የሕይወት አደጋ የፈጸሙ የፀጥታ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ መንግሥት የማድረግ ግዴታ እንዳለበትም ኢሰመጉ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት ሪፎርም ቅድሚያ ተሰጥቶት በትኩረት መሠራቱን መንግሥት ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ ከለውጡ አስቀድሞ የነበሩና ኅብረተሰቡን ለከፍተኛ ምሬት ዳርገው የቆዩ በሕግ ማስከበር ሥራዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ በከፍተኛ ሁኔታ መቀረፋቸውንም መንግሥት ደጋግሞ ይናገራል፡፡
‹‹አሳዳጅም ተሳዳጅም›› እንደማይኖር ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ሳያጣሩ ማሰርም መቅረቱን›› ሲናገር የቆየው መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የቀድሞ መንግሥታት የገጠማቸውን ዓይነት ፈተና በሕግ አከባበር ጉዳይ ሲገጥመው እየታየ ነው ይባላል፡፡
በቀደሙ አስተዳደሮች የተፈጸሙ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች እንደማይደገሙ መንግሥት ቃል መግባቱ፣ በለውጡ የመጀመሪያ ሰሞን ከፍተኛ የሕዝብ ቅቡልነት አትርፎለት ነበር፡፡
ዜጎች ‹ለመከላከያ እቆማለሁ› ብለው ለሠራዊቱ ከሰጡት ከፍተኛ ድጋፍና ይሁንታ በተጨማሪ፣ ለፖሊስና ለሌሎችም የፀጥታ አስከባሪዎች የነበረው የሕዝብ አመለካከት በከፍተኛ ደረጃ ወደ አዎንታዊነት ሲቀየር የታየበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ሊስትሮዎች ሳይቀሩ የፀጥታ አካላትን ጫማ ለመጥረግ ገንዘብ አንቀበልም ያሉበት አጋጣሚ አይረሳም፡፡ በየታክሲው፣ በየካፌቴሪያው፣ በየምግብ ቤቱና በየአገልግሎት መስጫው የፀጥታ አካላትን ቅድሚያ የመስጠት ተነሳሽነት እንዲለመድ የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር መጠየቁን ተከትሎ ኅብረተሰቡ አንድ ሰሞን ሲሰጥ የታየው ምላሽ የፀጥታ አስከባሪዎች ቅቡልነት ማደግ ጀመረ የሚያሰኝ እንደነበር የሚያስረዱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ የመንገድ ዳር ነጋዴዎችን የሚያሯሩጡ ደንብ አስከባሪዎች ድርጊት በቪዲዮ ተቀርፆ መሠራጨት ሲጀምር በየአጋጣሚው ሴቶችን፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን በየአጋጣሚው የሚደበድቡ ፖሊሶች ድርጊት በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሠራጭ፣ የሃይማኖት አባቶችን በጥፊ የሚመቱ ፖሊሶች ሲታዩ የፀጥታ አስከባሪዎች የሥነ ምግባር ጉዳይ መልሶ ጥያቄ ይነሳበት እንደጀመረም የሚናገሩ አሉ፡፡
በፖሊስ ሳይንስ ማሠልጠኛ ሰነድ ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ የሚወሰድ የአድማ ብተና ዕርምጃ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ሒደት ያለው መሆኑን ያትታል፡፡ ፀጥታ አስከባሪዎች ሕገወጥ ሆኖ የተገኘ አድማን ለማስቆም ቢያንስ አሥር የዕርምጃ ዓይነቶች እንዳለቸው ተብራርቷል፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች ደግሞ ማጥቂያና መከላከል ተብለው በሁለት ምድብ ተቀምጠዋል፡፡
መፈተሽ፣ ቅኝት ማድረግ፣ መግፋት፣ መነጠል፣ መክበብ፣ ማሳለፍ፣ ማስቆም፣ ወዘተ ተብለው የተቀመጡት እነዚህ የዕርምጃ አወሳሰድ አማራጮች የፀጥታ አካላት ወደ መጨረሻው የኃይል አማራጭ ከማለፋቸው በፊት ቢተገብሯቸው በሚል የቀረቡ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የፀጥታ አስከባሪ አካላት የመጨረሻ ደረጃ ኃይል ለመጠቀም የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሳይፈጠሩና ሳይገደዱ፣ ኢተመጣጣኝ ኃይል ይጠቀማሉ የሚል ቅሬታ ይቀርብባቸዋል፡፡ በተለይ በእምነት ተቋማት አካባቢ አድማ ለመበተን የተወሰዱ ዕርምጃዎች የተከበሩ ቤተ ክርስቲያናትና መስጂዶች ጭምር እንዲደፈሩ ያደረገ ከኢትዮጵያዊ እሴትም ያፈነገጠ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረጉ ነበሩ ይባላል፡፡
ኮማንደር ግሩም ደግሞ ፖሊስ የኃይል አማራጭ እንዲጠቀም የሚያደርግ ሁኔታ ቢፈጠር ወይም ጥይት ወደ መጠቀም ቢገባ እንኳ፣ ደረጃውን ጠብቆ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ነው የሚሉት፡፡
‹‹መጀመሪያ ወደ ሰማይ ነው የሚተኮሰው፡፡ ማስጠንቀቂያ ተኩሱን ፈርተው አልቆም ካሉ ደግሞ አመፁን የሚመሩ ሰዎችን በመነጠል ያውም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የማይጥል እንደ እግር ባለ ቦታ መምታት ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ይህ አመፁን ያላስቆመ እንደሆን ብቻ የከፋ ጉዳት በአመፁ የተነሳ እንዳይከሰት የጥቂት ሰዎችን ሕይወት ብቻ አደጋ ላይ የሚጥል ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ ወይም የፀጥታ አካላት ሕግን ተላልፈው ሲገኙ በወንጀል ሕጎች ከመጠየቃቸው በተጨማሪ በፀጥታ ማስከበር በሥነ ምግባር ደንቦችም እንደሚጠየቁ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡