Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት የኑሮ ውድነት ችግርን ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ ችግሩን ማባባስ ምላሹ ሆኗል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ልንፈታው ያልቻልናቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ችግሮች ሊቃለሉ አልቻሉም፡፡ የሰላም ዕጦት አለ፣ በየአካባቢው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች አሁንም የሰው ሕይወት እየቀጠፉ ነው፣ ንብረት እያወደሙ ነው፡፡ ተረጋግቶ ለመሥራት የማያስችሉ እንቅፋቶች እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ የዜጎች መፈናቀልም የተለመደ ሆኗል፡፡

ይህ ሳያንሰን መንግሥት የሚወስዳቸው አንዳንድ ዕርምጃዎች ችግር እየወለዱ ነገሮችን እያባባሱ ነው። ከሰላም ዕጦትና አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አሳሳቢ ከመሆን አልፎ እያንገራገጨን ነው፡፡ 

ሌላውን ነገር ትተን በዋጋ ንረት ምክንያት የተከሰተው የኑሮ ውድነት እያደረሰ ያለውን ጉዳት ብቻ ነጥለን ብንመለከት መፍትሔ ያላገኘ በሽታ ሆኗል፡፡ የኑሮ ውድነት የአገሪቱና የሕዝቦቿ መሠረታዊ ፈተና ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን አንገብጋቢ ችግርም ሆነ ሌሎች ውስጣዊ ቀውሶችን ለመፍታት በመንግሥት እየተወሰዱ ናቸው የሚባሉ ዕርምጃዎች ይህ ነው የሚባል መፍትሔ አላመጡም፡፡ 

በተለይ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል እየታየ ካለው የዋጋ ንረት አንፃር ነገም የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት ጎልቶ በሚንፀባርቅበት ወቅት ከመንግሥት የሚጠበቀው ገበያውን ማረጋጋትና የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ነው፡፡ በእርግጥም የዋጋ ንረትን ከመከላከል አንፃር የተለያዩ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው አይካድም፡፡ ነገር ግን ምን አስገኘ ብለን ከጠየቅን አፋችንን ሞልተን የምንናገረው አዎንታዊ ምላሽ የለም፡፡ ምክንያቱም አሁንም ገበያው ግለቱ ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ 

የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት መቆሚያ አጥቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት በቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻል ባስቀመጠው ጊዜ ውስጥ ሳይቀር አከራዮች ያለ ከልካይ ዋጋ ሲጨምሩ መቆየታቸውን ብዙዎች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ 

በሸማቾችና ተገልጋዮች ላይ እንዲህ ያሉ ጫናዎች በበረቱበት ወቅት ግን ችግሩን ሊያባብሱ የሚችሉ አንዳንድ መመርያዎች ሲወጡ ደግሞ ነገን በብርቱ እንድንፈራው ማድረጉ አይቀርም፡፡ 

ለዚህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ ታሪፍ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የንብረት ግብር ነው፡፡ እስካሁን ከምናውቃቸው የግብር ዓይነቶች ለየት ብሎ የመጣው የንብረት ግብር ወይም (ፕሮፐርቲ ታክስ) የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ እያንዳንዱን ግንባታ የሚመለከት ነው፡፡ ከእነዚህ ግንባታዎች የንብረት ግብር መንግሥት አዲስ ግብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ የግብር ዓይነት በሌላው ዓለም ያለ ቢሆንም በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ኅብረተሰቡን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግና የዋጋ ንረትን ሊያባብስ የሚችል መሆኑ ሲታሰብ ነገሩን አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ የግብር ዓይነት የቱንም ያህል አስፈላጊ ነው ቢባል እንኳን ከወቅታዊው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡ የአንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምልከታም ይህንኑ ሥጋት የሚያጠናክር ሆኗል፡፡ 

የሸቀጣ ሸቀጦችና የቤት ኪራይ ዋጋ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ምሬቱን እያሰማ ያለው ተገልጋይ, የቤት ኪራይ ዋጋ ሊጨምርበት እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ አከራይ ወትሮም ቢሆን ሰበብ የሚሻ በመሆኑ የንብረት ግብር ሳይቸገር ሊከፍል ይችላል፡፡ የንብረት ግብርን የተመለከተው የዋጋ ተመን እንደሚጠቁመው ዝቅተኛ የግብር ምጣኔው ወደ ሰባት ሺሕ ብር አካባቢ ይደርሳል፡፡ ይህ ግብር እንደ ግንባታው ዓይነት  በሚሊዮኖች የሚቆጠር ክፍያ የሚጠየቅበት ቦታ ነው፡፡ እንደ ኮምዶሚኒየም ያሉ ቤቶች አማካይ የንብረት ዋጋ ተመናቸው ከ20 ሺሕ ብር በላይ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት በአማካይ በወር ሁለት ሺሕ ብር ለዚህ ግብር ዓይነት ይከፈላል፡፡ 

ስለዚህ ሁለት ሺሕ ብር የንብረት ግብር ቢያስከፍለው ይህንን ሁለት ሺሕ ብር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ዋጋ አክሎ ተከራይ ላይ ከመቆለል አይመለስም፡፡ አብዛኛው ተከራይ ደግሞ ደመወዝተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት ባወጣው አዲስ አሠራር የሚጠብቀውን ተጨማሪ ወጪ ከየት አምጥቶ እንዲያሟላም ሲታሰብ ያስፈራል፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኛው ደመወዙ ባልጨመረበት፣ እንዲያውም የደመወዝ ግብር ይቀንስለት እየተባለ በሚጮህበት በዚህ ሰዓት ጭራሽ ሌላ ወጪ የሚደረግበትን የታክስ ሥርዓት መዘርጋት እጅግ ከባድ ነው፡፡ 

ስለዚህ መንግሥት የራሱን በጀት ለማሳደግ ሲል ይተግበር ያለው የንብረት ግብር ሊያስከት የሚችለውን ተፅዕኖ እንዴት እንዳየው ባይታወቅም፣ የንብረት ግብር አሁን ባለው ሁኔታ ለመተግበር መነሳት የሚያስከትለው ቀውስ ቀላል ሊሆን እንደማይችል ግን መገመት አያዳግትም፡፡ 

ጉዳዩ ከቤት ኪራይ ዋጋ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የንብረት ግብር መጣብኝ ያለ የንግድ ቤቶችን ያከራዩ ሁሉ አጋጣሚውን ተጠቅመው ዋጋ ከጨመር የማይመለሱ በመሆኑ፣ ይህ ጭማሪ ተወደደም ተጠላ መጨረሻ ላይ የሚያርፈው ሸማቹ ላይ ስለሚሆን እስከዛሬም መፍትሔ የታጣለት የዋጋ ንረት የበለጠ ማባባስ ይሆናል፡፡ 

ለዚህ ነው መንግሥት ይህንን የግብር ዓይነት ሲተገብር ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን ላለመቻሉ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል ብለን ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው፡፡ የዚህ ሕግ ተግባራዊ መሆን ሌላው ሥጋት በአግባቡ የግንባታዎቻቸውን ብዛትና ዓይነት በቅጡ መያዝና አለመያዝ ጋርም ይያያዛል፡፡ በተለይ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ባልተደረገበትና ትክክለኛ መረጃ ተመዝግቦ ባልተያዘበት በዚህ ወቅት፣ ሕጉን አምጥቶ መጫን ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል፡፡ ጉዳዩን ጠለቅ ብለን እንየው ከተባለም እያንዳንዱን የግንባታ ዓይነት ለይቶ የሚጣለውን ግብር ዋጋ እንዲተምኑ የሚመደቡ ባለሙያዎችን በቅንነትና በንፅህና አገልግሎቱን ሊሰጡ መቻል አለመቻላቸውም ሌላው የሥጋት ምንጭ ነው፡፡ ይህ ባልጠራበት ሁኔታ ሕጉ እንዲተገበር ከተደረገ ደግሞ ወትሮም በሙስና የተጨመላለቀውን አሠራር የሚያባብስ ከመሆኑም ሌላ፣ ለሌቦች ሌላ በር እንደተከፈተላቸው ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ሕጉን ከማውረዱ በፊት ይህንን ሁሉ መመዘንና መፈተሽ ካልቻለ ብዙ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ከዚህ ግብር ጋር ተያይዞ ሌላው ሊያነጋግር የሚገባውና መንግሥት ጉዳዩን እንደገና ሊያጤነው ይገባል የሚባልበት ሌላም አኳር ነጥብ አለ፡፡ ይህም በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ያሉ መኖሪያ ትልልቅ ሕንፃዎች፣ እንዲሁም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአብዛኛው በብድር የተገነቡ በመሆናቸው ዕዳ ያለባቸው ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል፡፡ 

ስለዚህ ግንባታዎች የባንክም ጭምር ናቸው፡፡ ዕዳቸው ተከፍሎ ያላለቀ በመሆኑም ሙሉ በሙሉ በባቤትነት ሳይያዙ እንዲህ ያለው ታክስ በተጨማሪነት መጠየቃቸው አግባብ አይሆንም፡፡፡ ገና ከፍለው ባልጨረሱት ንብረት ላይ የንብረት ግብር ክፈሉ ሊባሉ እንዴትስ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የማይችል ሕግ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል መንግሥት በትክክል ማሰብ አለማሰቡን ለማወቅ ይከብዳል፡፡

ይተግበር ከተባለ ዕዳ ያለበትንም የሌለበትንም፣ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኘውንም የማያስገኘውንም መኖሪያና ሕንፃ በተመሳሳይ የዋጋ ተመን እንዲያስተናግዱ ማድረስ አግባብ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችም በአግባቡ ሊመለሱ፣ ኅብረተሰቡም ሌላ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሳይደረግ ሕጉን ለመጫን መሞከር ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ 

ለማንኛውም ግን የንብረት ግብር ጉዳይ እንዲህ በጥድፊያ እንዲተገበር ከማድረግ ይልቅ፣ አሁንም ነገሮችን በቅጡ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል፡፡ የለም መተግበር አለብን ብሎ ከተነሳ ቢያንስ በብዙዎች ዘንድ ሥጋት የሆነውን የዋጋ ንረትና የዋጋ ጭማሪ ላለማስከተሉ ማረጋገጫ መስጠት አለበት፡፡ 

ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው መንግሥት የግብር ገቢውን ለማሳደግ አንዱ መፍትሔ ይሆናል ብሎ ካመነበት ከንብረት ግብር ባሻገር ሌሎች እየተረቀቁ ያሉ የታክስ ሕጎችም በመሆኑ፣ እነዚህም ጊዜያቸው ደርሰው ሲተገበሩ ለተጨማሪ የዋጋ ንረት ሰበብ መሆናቸው ስለሚታሰብ ነው፡፡ 

ለምሳሌ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ ላይ እስከዛሬ ተጨማሪ እሴት የማይመለከታቸው አገልግሎቶች ታክስ የሚጣልባቸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ችግር ሊያባብሱ የሚችሉ እንዲህ ያሉ ሕግጋቱን ከመተግበሩ በፊት ሊያስከትል የሚችለውንም ቀውስ ደግሞ ደጋግሞ ያስብ፡፡ ግብር መክፈል ግዴታ ቢሆንም በልክና በአቅም መሆን አለበት፡፡ የዜጎችንም መብት የሚነካና አማራሪም እንዳይሆን መጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት