ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የያዘ ‹‹ከገበሬው ታወር›› የተሰኘ ሪል ስቴት ለመገንባት በጨረታ ያዝኩት ላለው ለ30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ማረጋገጫ ሳያሳይ፣ 1.5 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች መሸጡን አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ 1.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቆ፣ በዕለቱ ከአንድ አክሲዮን 3.5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 750 አክሲዮኖችን ለመሸጥ በዕለቱ (ሰኔ 1 ቀን) መጀመሩን ገልጿል፡፡
የፐርፐዝ ብላክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) ‹‹ከገበሬው›› የተሰኘውን ፕሮጀክት ለማቀላጠፍ ያግዛል ያሉትን ፕሮጀክት ለማስጀመር፣ ሜክሲኮ አካባቢ ቦታውን በጨረታ ተወዳድረው በማሸነፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጨረታውን ካሸነፉ በኋላ የሚጠበቀውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ክፍያ መፈጸም ስለሚጠበቅባቸው፣ 1,000 አክሲዮኖችን እያንዳንዳቸው በ1.5 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ይዞታው በእጃቸው መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
ሕንፃዎቹ የሚገነቡበት ትክክለኛ ቦታ የት እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ የውል ጉዳይ ስለሚይዛቸው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ጥያቄ በድጋሚ ለፐርፐዝ ብላክ የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ታደሰ ሰይፉ ቀርቦላቸው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቋሚ ውል እስኪደረስ ድረስ ለሚዲያ መረጃ እንደማይሰጥ ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ፍሰሐ (ዶ/ር) በመግለጫው ወቅት የአክሲዮን ሽያጩን በተመለከተ የተደበቀ ነገር እንደሌለ በመግለጽ፣ አሸንፈንበታል ያሉትን የጨረታ ሰነድ ከፍ በማድረግ ለጋዜጠኞችና ለድርጅቱ ሠራተኞች አሳይተዋል፡፡
በአንዱ ሕንፃ 115 ወለሎች የመገንባት ዕቅድ የያዘው ፐርፐዝ ብላክ፣ ለግንባታው 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና አራት ሺሕ አክሲዮኖች መሸጥ እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ግንባታ የሚውል ሀብት ለማሰባሰብ በመጀመርያ ምዕራፍ 1.5 ቢሊዮን ብር ከ1,000 አክሲዮኖች የሰበሰበ መሆኑን፣ በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ 750 አክሲዮኖችን እስከ ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ይሸጣሉ ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በ1.5 ሚሊዮን ብር ባለሦስት መኝታ አፓርታማ ሕዝቡን ለመዝረፍ ሆን ብላችሁ አስባችሁ ነው ወይ? ወዘተ የሚሉ ብዙ ውዥንብሮች እንደነበሩ በመግለጽ፣ ‹‹ፐርፐዝ ብላክ አፓርታማ ሳይሆን አክሲዮን እንደሚሸጥ ነው ያስታወቀው›› በማለት አስተባብለዋል፡፡ በ1.5 ሚሊዮን ብር ባለሦስት መኝታ አፓርታማ መሸጥ ከተቻለም ማንም እንደማያገባው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለዚህ ምላሽ እንደ ምሳሌ ያነሱት በ40/60 ፕሮጀክት በመንግሥት የሚገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ነው፡፡ በካሬ ሜትር 11,000 ብር በ100 ካሬ ሲሰላ 1.1 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን በማስረዳት፣ ‹‹መንግሥት በዚህ ገንዘብ ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ከገነባ እኛ የማንችልበት ምክንያት የለም፤›› በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ጥያቄ ሲያስነሳ የሰነበተውን ጉዳይ አብራርተዋል፡፡
‹‹እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በ1.5 ሚሊዮን ብር ቤት ለመሸጥ አላሰብንም፡፡ ዝቅተኛው አምስት ሚሊዮን ብር፣ ከፍተኛው ደግም አሥር ሚሊዮን ብር ለመሸጥ ነው ያሰብነው፤›› ብለዋል፡፡
ቤት ገንብቶ ለመሸጥም ቢሆን ሕጋዊ ፈቃድ እንዳላቸው የጠቀሱት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን የፕሮጀክቱ ዓላማ አንድ ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የመጥቀም ራዕይ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሪፖርተር ካነጋገራቸው አክሲዮን ገዥዎች መካከል አቶ ሃይደር አሸናፊ፣ ፐርፐዝ ብላክ ሜክሲኮ አካባቢ ከቢጂአይ የሚገዛው ቦታ ላይ ሕንፃውን እንደሚገነባ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ሃይደር 1.5 ሚሊዮን ብር ከፍለው የቤት ባለቤት ለመሆን ቢሄዱም፣ አክሲዮን እንዲገዙ ስለተነገራቸው በዚሁ መሠረት መፈጸማቸውን አክለዋል፡፡
‹‹ቃል ስለገቡልኝ አምኛቸዋሁ፤›› ያሉት ሌላው ባለአክሲዮን አቶ አስቻለው ደሴ፣ ‹‹ሜክሲኮ አካባቢ ከማለት ውጪ ትክክለኛ ቦታው አልተገለጸልንም፤›› ብለዋል፡፡
ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጋር የመነጋገር ዕድሉን እንዳገኙ የተናገሩት አክሲዮን ገዥው፣ ድርጅቱ ያለው ስምና ዝና እንዳሳመናቸውም አስረድተዋል፡፡