Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበግዳጅ እንዲተገበር የተጠየቀው የቤት ግብር ማሻሻያ ሕጋዊ አይደለም

በግዳጅ እንዲተገበር የተጠየቀው የቤት ግብር ማሻሻያ ሕጋዊ አይደለም

ቀን:

በአስተውል በሕጉ ጉርሜሳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥር 10/1/9357/15 ለሚመለከታቸው የመስተዳድሩ አካላትና ክፍላተ ከተሞች፣ ‹‹የቤት ግብር ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ስለማሳወቅ›› በሚል ርዕስ ጽፎ በየወረዳው በግዳጅ እንዲተገበር ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ቢሮው ለግብር ማሻሻያው መነሻና መሠረት ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ በቁጥር ፋ/በ/2/64/2249 ኅዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም.  በተጻፈ ደብዳቤ የገለጸውን ማሻሻያ መሠረት አድርጎ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ በቁጥር ፋ/0/2/64/2249 ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የቤት ግብር ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲና ለአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፣ ቢሮው ያስጠናውን ጥናትና የጥናት ውጤት ውሳኔ ከክፍያ ሰንጠረዥ ጋር አያይዞ ልኳል። በዚሁ ደብዳቤ ላይ ግብሩ እየተወሰነ እንዲሰበሰብ በአንክሮ ጠይቋል።

የጥናቱም ሆነ የመመርያው ሕጋዊ መሠረት በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የወጣው የከተማ ቦታ ኪራይና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ ቁር 80/1968 አንቀጽ 6(2) ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ጥናት ሲያደርግ ስለአዲስ አበባ ከተማ የከተማ የቦታ መጠቀሚያ ኪራይና የቤት ግብር ለማስከፈል የወጣውን ደንብ ቁጥር የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 36/1968 ያነሳው አንዳች ነገር የለም፡፡ ይህ ደንብ እስከ ዛሬም ድረስ አልተሻረም፡፡ በሥራ ላይ ውሎ ሲተገበር የቆየውም ይኸው ደንብ ነው፡፡

የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 ባልተሻረበት ሁኔታ፣ ይህ የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ደንብ ቁጥር 36/1968 ‹‹ተሽሯል›› የሚል ግምት መውሰድ አይቻልም፡፡ ሕግ በሕግ ይሻራል፣ ይሻሻላል እንጂ በግምትና በዝምታ አይሻርም፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ በሕግ ክፍል ማስታወቂያ ያወጣው ደንብ፣ በሌላ እኩልነት ባለውና በሚታወጅ ወይም በነጋሪት ጋዜጣ ባልወጣ ደንብ በደብዳቤ ብቻ ተሽሮ በአስገዳጅነት እንዲተገበር ማድረግ ፍፁም ሕገወጥ ተግባርና አሠራር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ደንብን ሽሮ ወይም በሥራ ላይ ያለና ያልተሻረ ደንብን ወደ ጎን አድርጎ መመርያ የማውጣት ሥልጣን የለውም። እንኳንስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ አካል የሆነ ቢሮ ሌሎች ከፍ ያሉ የመንግሥት አካላትና የሚኒስትሮች መሥሪያ ቤቶችም፣ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ውጤት ያአለው መመርያ ከማውጣታቸው በፊት የመመርያው ሕጋዊነት በኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ በደብዳቤው መሠረት እንዲፈጸም ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ከማስታወቅ በዘለለ፣ ‹‹ያወጣሁት መመርያ ወይም ሰርኩላር ነው›› አላለም፡፡ ይህም በዝምታ የታለፈ ሳይሆን ቢሮው በሥራ ላይ ያለና በነጋሪት ጋዜጣ የታወጀ ደንብ ሳይሻርና ሳይሻሻል፣ ደንቡን የሚቃረን መመርያ የማውጣት ሥልጣን ስለሌለው ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በደብዳቤ አውጥቶ ለሚመለከታቸው አካላት የበተነውና እንዲፈጸም ያስጠነቀቀበት ደብዳቤ ላይ በአባሪነት የተመለከተው የግብር ማስከፈያ ሰንጠረዥ፣ በአዋጅ ቁጥር 80/1968 ላይ ከተመለከቱት ሰንጠረዥ አንድ፣ ሁለትና ሦስት በእጅጉ የተለየ ነው፡፡

አዋጁም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ያወጣው የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቤቶችን ከተሠሩበት ግብዓትና ቁስ ለይቶ በካሬ ሜትር ወርኃዊ ኪራይን አልተመነም፡፡ ያለያየው በከተማው የቦታ ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዋጅ ቁጥር 80/1968 አንቀጽ 19 መመርያ ለማውጣት ለማዘጋጃ ቤቶችና ለከተማ አስተዳደር ከሰጠው ሥልጣን ያለፈ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው ሌላ ፍሬ ነገር ቢኖር በአዋጁ አንቀጽ 19 መሠረት ደንብ የማውጣት ሥልጣን ያላቸው የከተማ አስተዳደር አካላት፣ ደንቡን ከማውጣታቸው በፊት የተባለውን ኪራይ ወይም ግብር ሊሰበስቡ አይችሉም፡፡ ከዚህ በላይ በተራ ቁጥር አንድ፣ ሁለትና ሦስት ላይ በተገለጸው መሠረት ሕጉን ተከትሎ የወጣ ደንብ ባለመኖሩ በአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በተጻፈ ደብዳቤ ብቻ ግብር መሰብሰብ አይቻልም፡፡

የገቢዎች ቢሮ ያወጣው የቤት ግብር ማሻሻያ ደብዳቤ በአዋጅ ቁጥር 80/1968 ላይና በሕግ ክፍል ማስታወቂያ 36/1968 ላይ ከወጣው እጅግ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡

የገቢዎች ቢሮ ያወጣው የቤት ግብር ሕጋዊነት የለውም እንጂ ሕጋዊ ነው ቢባል እንኳን፣ የማስከፈያ ታሪፍ ማውጣት የሚችለው ሕጉ ካስቀመጠው ሰንጠረዥ አንድ፣ ሁለትና ሦስት ላይ ከተመለከተው ዝቅ አድርጎ እንጂ አተገባበርና የማስረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱም አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ወረዳዎች ወጥ አሠራር ይጎድለዋል፡፡ ካርታ የሌላቸውና በተለምዶ ‹‹ሰነድ አልባ›› የሚባሉ ቤቶችን በተመለከተም አወዛጋቢ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ያወጣው የቤት ግብር ማሻሻያ ደብዳቤ፣ ግብሩ እንዴት እንደሚሰላና ይህ እንዲፈጸም ለሚመለከታቸው አካላት ከማስታወቅ ውጪ በቤት ግብር ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ ወገን ፍትሕ የሚያገኝበት መንገድ በአዋጅ ቁጥር 80/1968 አንቀጽ 7፣ 8፣ 9 ፣10፣ 11 እና 12 መሠረት መሆኑን ሳይገለጽ አልፎታል፡፡ ይህ ደግሞ ግብር ከፋዩ የቤት ባለቤትነት መብቱን የሚጠይቅበት መንገድና አካሄድ ምን እንደሆነ የሚገልጽ ነው፡፡

ማጠቃለያ

በንብረት የመጠቀም መብት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ላይ የተደነገገ የዜጎች መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ይህ መብት ሊከለከልና ሊገደብ የሚችለው ደግሞ ሕገ መንግሥቱን በማይቃረን ሌላ ሕግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ሕግን፣ ሕግ ደግሞ ደንብን ወይም የሕግ ክፍል ማስታወቂያን፣ ደንብን ወይም የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ደግሞ መመርያ ወይም ሰርኩላርን፣ ሰርኩላር ደግሞ ደብዳቤን ተከትሎ ይወጣል፡፡ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ ግን የዚህ ሕጋዊ አሠራር ግልባጭ ነው፡፡

የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 ፀንቶ ባለበት ሁኔታና  ሳይሻሻል ወይም ሳይቀየር፣ ሕዝብ ሳይነጋገርበትና ፓርላማ ሳይመክርበት ከዚህ በላይ በዝርዝር እንደተገለጸው፣ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካል ብቻ መመርያ አውጥቶ ነዋሪው የሚገደድበትን ትዕዛዝ ማስተላለፍ ሕጋዊ አይደለም።

 ይህን ሕዝብ እንዲያውቅ ለመጠቆም ያህል ያዘጋጀሁትን አስተያየት በጓዳ ሳይሆን ይፋ በሆነ ሁኔታ ምሁራን ይተቹበት፡፡ ሕዝብ ይነጋገርበት፣ አስተዳደሩም ያጢንበት፣ መንግሥትም ያስብበት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...