Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በማራቶን በእነማን ትወከላለች?

በዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በማራቶን በእነማን ትወከላለች?

ቀን:

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር ከሁለት ወራት ያልበለጠ ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ ተካፋይ አገሮች ብሔራዊ ቡድናቸውን አሳውቀው ዝግጅት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ ከሁለት ሺሕ በላይ አትሌቶች በሃንጋሪ ቡዳፔስት በሚዘጋጀው ሻምፒዮና ይካፈላሉ፡፡

ተካፋይ አገሮች የዓለም አትሌቲክስ ያስቀመጠውን የማሟያ መሥፈርትን ከግምት በማስገባት፣ በአገርና ከአገር ውጪ በተደረጉ ውድድሮች አትሌቶቻቸውን ለይተው ዝግጅታቸውን ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሳምንት አስቀድሞ በ10 ሺሕ ሜትር አገራቸውን ሊወክሉ የሚችሉ፣ በተለያዩ አገሮች ውድድር ያደረጉ አትሌቶችን የግል ምርጥ ሰዓት በመመልከት ስም ዝርዝራቸውን ይፋ ማደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ስም ዝርዝራቸው ይፋ የሆኑት አትሌቶች በስፔን ቅድመ ማጣሪያ ውድድር አድርገው የመጨረሻዎቹ እንደሚለዩ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የማራቶን ሯጮችንና አሠልጣኞቻቸው ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት በወንዶች ስድስት አትሌቶች እንዲሁም በሴቶች ስድስት አትሌቶች ተለይተዋል፡፡  

ስም ዝርዝራቸው ይፋ ከሆኑት አትሌቶች መካከል የ2022 የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና የማራቶን አሸናፊዎቹ ታምራት ቶላና ጎተይቶም ገብረሥላሴ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል፡፡ ሁለቱ ሻምፒዮኖች የዓምናውን ውድድር ማሸነፋቸውን ተከትሎ በቀጥታ የሚያልፉ ይሆናሉ፡፡

በወንዶች ፀጋዬ ጌታቸው፣ ጫሉ ዴሶ፣ ልዑል ገብረሥላሴ፣ ሰይፉ ቱራና መሐመድ ዒሳ፣ በሴቶች አማኔ በሪሶ፣ ፀሐይ ገመቹ፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ መገርቱ ዓለሙና ወርቅነሽ ኢዶሳ ባላቸው የግል ምርጥ ሰዓት አማካይነት ታጭተዋል፡፡

ገመዶ ደደፎና ሐጂ አዲሎ የማራቶን ቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው መመረጣቸውና አትሌቶቹም ከሰኔ 7 ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት ዝግጅት እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል፡፡ በሥልጠና ቆይታቸውም፣ ወቅታዊ ብቃታቸውና ጤንነታቸው ከታየ በኋላ ሦስት ሦስት አትሌቶች ተጠባባቂዎች ጨምሮ እንደሚለዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አብራርቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአመራረጡ ቅሬታ ያለው እስከ ሰኔ 5 ቀን በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ማቅረብ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

አትሌቶቹ ባላቸው ፈጣን ሰዓት፣ በተለያዩ ውድድር የሚያገኙት ነጥብ እንዲሁም የሚካፈሉበት የውድድር ዓይነት የምርጫው ቀዳሚ መሥፈርቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ስማቸው ከተዘረዘሩት መካከል ‹‹ማን ይመረጣል?›› የሚለው ከሁለት ወራት የልምምድ ጊዜ በኋላ ምላሽ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያን ከሚወክሉ አትሌቶች መካከል ታምራት ቶላ በቀጥታ የሚያልፍ ሲሆን፣ ፀጋዬ ጌታቸው በዝርዝሩ በሁለተኝነት ተቀምጧል፡፡ ፀጋዬ የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው ደረጃ መሠረት ባደረጋቸው ውድድሮች 1,385 ነጥብ በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 በአምስተርዳም ማራቶን 2፡04፡49 በመግባት አንደኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን፣ በ2023 ቶኪዮ ማራቶን በ2፡05፡25 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ይጠቀሳል፡፡ በ2021 የፓሪስ ማራቶን በ2፡05፡11 ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ጫሉ ዴሶ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2023 ቶኪዮ ማራቶን 2፡05፡22 አንደኛ፣ እንዲሁም በ2022 ቫሌንሺያ ማራቶን 2፡04፡56 ስድስተኛ በመውጣት 1,364 ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ሌላው ልዑል ገብረሥላሴ ሲሆን በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ በ1,351 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ ልዑል በ2022 ለንደን ማራቶን በ2፡05፡12 ሁለተኛ ሲወጣ፣ ዘንድሮ በዚያው በተከናወነው የማራቶን ውድድር በ2፡05፡45 አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ መቻሉ ይታወሳል፡፡ በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች በመካፈል የሚታወቀው ልዑል በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደሚካፈል ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡  

በማራቶን ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፉ ከሚገኙ አትሌቶች መካከል ሰይፉ ቱራ አንደኛው ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮናውም በቀዳሚነት ይሳተፋሉ ተብሎ ግምት ከተሰጠው አትሌቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በ2021 ቺካጎ ማራቶን በ2፡07፡17 ያሸነፈ ሲሆን፣ በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2፡07፡17 ስድስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዥ 1,367 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል፡፡

በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች

በዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ከሚጠበቅበት አንዱ የሴቶች ማራቶን ነው፡፡ በዓምና የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጎተይቶም ገብረሥላሴ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት መቻሏ ይታወሳል፡፡ አትሌቷ ዘንድሮ በቀጥታ የማለፍ መብት አላት፡፡

ጎተይቶም በዓለም ሻምፒዮናው 2፡18፡11 በማጠናቀቅ የውድድር ቦታው ክብረ ወሰን ጭምር በማሻሻል ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ ከድሏ በኋላ በቶኪዮ ማራቶን በ2፡18፡18 ሦስተኛ እንዲሁም በኒውዮርክ ማራቶን በ2፡23፡39 ሦስተኛ መውጣት ችላለች፡፡

በዚህም መሠረት ጎተይቶም በዓለም አትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዥ 1,449 ነጥቦች በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡ በዘንድሮም ሻምፒዮና ድል ከቀናት በዓለም ሻምፒዮና አዲስ ታሪክ መጻፍ ትችላለች፡፡

በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የተካተተችው ሌላዋ ሯጭ አማኔ በሪሶ ነች፡፡ አማኔ በ2022 በቫሌንሺያ በተደረገ ውድድር በ2፡14፡58 በመፈጸም ብሔራዊ ክብረ ወሰን መስበር የቻለችበት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በ2023 ቦስተን ማራቶን በ2፡21፡50 ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ አማኔ 1,391 ነጥብ በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

በዓለም ሻምፒዮና የመጀመርያ ተሳትፎ የምታደርገው አማኔ ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ ሆኖም በቀጣይ ሁለት ወራት የምታደርገው ዝግጅት በሻምፒዮናው የምታደርገውን ተሳትፎ ይወስናል፡፡

ከ5 ሺሕና 10 ሺሕ ሜትር ርቀቶች ኢትዮጵያን ወክላ የተወዳደረችው ፀሐይ ገመቹ በ2023 ቶኪዮ ማራቶን ያስመዘገበችው 2፡16፡56 የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዥ 1,377 ነጥቦችን ሰብስባ ስምንተኛ አትሌት ነች፡፡

በሌላ በኩል በግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን መጨበጥ የቻለችው የዓለምዘርፍ  የኋላዋ ሌላዋ ተጠባቂ አትሌት ናት፡፡ የ10 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ የዓለምዘርፍ በዓለም ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ እንደምትወዳደር ይጠበቃል፡፡

የዓለምዘርፍ በ2022 ለንደን ማራቶን በ2፡17፡26 በመፈጸም ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ በዓምናው የዓለም ሻምፒዮና በምርጫው አለመካተቷ ቅሬታ ሲያስነሳ ነበር፡፡ በጊዜው አትሌቷ በግማሽ ማራቶን እንጂ በማራቶን የተሳተፈችበት አለመኖሩ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

በአንፃሩ በለንደን ያመጣችው ድል በዘንድሮ የሃንጋሪ የዓለም ሻምፒዮና ለመሳተፍ ዕጩ ሆና እንድትመረጥ አስችሏታል፡፡ በዕጩነት የተመረጡ አትሌቶች በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ በሚያሳዩት አቅም መሠረት የመጨረሻዎቹን አትሌቶች ስም ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...