በአገር አቀፍ ደረጃ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሪፈራል ሆስፒታል እንደሚገነባ፣ ኅብረት ለበጎ የኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ የፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ደጀኔ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሮጀክቱን ይፋ ሲያደርጉ እንደገለጹት፣ መንግሥት በለገጣፎ አካባቢ በሰጣቸው የ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ዘመናዊነት የተላበሰ ሪፈራል ሆስፒታል ለመገንባት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
ሆስፒታሉንም ለመገንባት አራት ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ፣ ይህንን ገንዘብ ለማግኘት ከባለሀብቶች፣ ከዳያስፖራዎች፣ ከበጎ አድራጎት ተቋማት፣ ከአርቲስቶች እንዲሁም ከሌሎች ቦታዎች ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሚገነባውን ሆስፒታል ዲዛይን ለማውጣት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉም ተገንብቶ ሲያልቅ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች በነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሕክምና አገልግሎቱም አቅም ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ገንዘባቸውን ከፍለው የሚጠቀሙበት እንደሆነና ለሆስፒታሉም ግንባታ የሚሆነውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ከባለሀብቶች በተጨማሪ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ሆስፒታሉ በዋናነት ገቢ ኖሮት እንዲቀጥል የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን፣ ይህንን ለማድረግና ተፈጻሚ እንዲሆን ወጥ የሆነ አሠራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታውን በገንዘብ፣ በግብዓት፣ በሙያና በሌሎች ነገሮች ማኅበረሰቡ አቅሙ በፈቀደው ልክ በማገዝ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ሆስፒታሉንም ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ሦስት ዓመታት ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ግንባታውም በቅርቡ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት ችግር ለማቃለል ተቋሙ እየሠራ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ሰዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጋቸውንና ችግሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን አርቲስት ሰለሞን አስረድቷል፡፡
በተለይም በአገር ውስጥ ሕክምናውን የማያገኙ ለውጭ ሕክምና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ገልጾ፣ እነዚህንም ሰዎች ለመታደግ ይህ ፕሮጀክት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በቂ የሆነ ግብዓትና ምቹ ሆስፒታል ቢገነባላቸው ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ወደ ውጭ አገር ሄደው የሚታከሙ ወገኖችንም ሆነ ሌሎችን መታደግ እንደሚቻል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግሯል፡፡
በዚህ መሠረት በኅብረት ለበጎ የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩል ሊገነባ የታሰበው ሆስፒታል ከዳር ለማድረስ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አክሎ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ገንብቶ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት የለገጣፎና የለገዳዲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ አሰፋ ናቸው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተቋሞች ሲገነቡ ለመንግሥት ብቻ መተው ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንንም በመረዳት ሌሎችም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደ ኅብረት ለበጎ የኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡