Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ራሳችንን እንወቅ

በቤተልሔም መኰንን

በእንስሳት ዓለም አንድ ቀን አንድ የአንበሳ ግልገል በበጎች ሠፈር ተገኘ፡፡ በጎቹም ሲያዩት ወደዱትና አሳደጉት፡፡ ያ የአንበሳ ግልገልም ከበጎች ጋር በግን መስሎ፣ በግን ሆኖ እነሱ የሚግጡትን ሳር እየጋጠና የእነሱን የኑሮ ዘይቤ እየተከተለ አደገና ጎርምሶ ወጣት ሆነ፡፡ እናም ከዕለታት በአንዱ ቀን ሌላ አንበሳ ከበጎቹ መካከል ለማደን ወደ በጎች ሠፈር መጣ፡፡ ነገር ግን ያ አንበሳ በበጎቹ መሀል መሰሉ ጎረምሳ አንበሳ አብሯቸው ሳር ሲግጥ በማየቱ በጣም ተገረመ፡፡ አድኖ የመብላቱን ሐሳብ ተወና ያንን ወጣት አንበሳ ከእጁ ለማስገባት ብቻ በማሰብ አባሮ ያን የበግ አንበሳ ያዘው፡፡ እየጎተተ ወደ ወንዝ ወሰደው ያ የበግ አንበሳ ግን፣ ‹‹እባክህ አያ አንበሶ እኔን አትብላኝ፡፡ እኔ እኮ ምንም የማላውቅ ደካማ በግ ነኝ›› እያለ ይማፀነው ጀመር፡፡

አንበሳውም ወንዝ ዳር ከወሰደው በኋላ ፊቱን ወደ ወንዙ አዙሮ ወደ ወንዙ ውስጥ እንዲያይ አስገደደው፣ የበግ አንበሳውም ራሱን ወንዙ ውስጥ ሲያይ በጣም ደነገጠ፡፡ በጣምም ተገረመ ለካ እስካሁን እሱ አንበሳ እንጂ በግ አይደለም፡፡ ያ የበግ አንበሳ ማንነቱን ሲያውቅ ያጓራውን ማጉዋራት ከዚህ በፊት ሌሎች አንበሶችም አላጓሩትም፡፡

እኛም የሰው ልጆች ልክ እንደ ግልገሉ አንበሳ ማንነታችንን ብናውቅ ኖሮ ዓለማችን አሁን ያላትን ገጽታ አትይዝም ነበር፡፡

ለመሆኑ ስንቶቻችን አዕምሯችን ውስጥ ያለውን አቅም እናውቃለን? አብዛኞቻችን የአዕምሯችንን አቅም አናውቅም ማለት እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ የምድራችንን አምስት በመቶ የሚያህለው የሰው ልጅ የአዕምሮውን አቅም ቢያውቅ ኖሮ የምድር ሕይወት መንገድ የተቀየረ ይሆን ነበር፡፡

በእርግጥ እንደ እነ ንጉሥ ዒዛና በዘመናቸው በነበረው የምሕንድስና ጥበብ አክሱምን የመሰለ ድንቅ ሐውልት የሠሩ፣ ንጉሥ ላሊበላ አንድ አለት በመፈልፈል ዓለምን ጉድ የሚያስብሉ ድንቅ አብያተ ቤተ ክርስቲያን ያሠራ፣ ቅዱስ ያሬድ የዜማን ድርሰት ለመጀመርያ ጊዜ የፈጠረ፣ ብራይት ብራዘርስ በአየር ላይ መብረር እንደሚቻል ያሳዩ፣ ቶማስ ኤድሰን አምፖልን በመሥራት ለዓለም ብርሃንን የሰጠ፣ ሼክስፒርና ሊዮናርዶ ዳቪንቺ ያሉ አዕምሯቸውን መርምረው በጊዜ የተረዱና በተሰጣቸው መክሊት በዓለም ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ የሰው ልጆች አሉ፡፡

ስለነዚህ ሰዎች ስናስብ የሰው ልጅ ምን ያህል ዕፁብ ድንቅ ፍጥረት እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች ነጭ ብቻ ቢሆኑ የእነሱ የዘር ግንድ የተለየ ነው ልንል እንችል ነበር፡፡ ግን እነ ንጉሥ ኢዛናን፣ ንጉሥ ላሊበላንና ቅዱስ ያሬድን ስናይ ከእኛው ከጥቁሮች ሊያውም ቀደምትና ታላቅ በነበረችው የዛሬዋ ደሃዋ አገራችን ከኢትዮጵያ አብራክ የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡

ብዙ ጊዜ እኛ የሰው ልጆች ከፍጡራን ሁሉ የተለየንና ታላቅ ፍጥረት መሆናችንን በቲዎሪ ደረጃ እናውቃለን፡፡ ግን ወደ ራሳችን ስንመጣ ብዙ የምንሰጠው ምክንያት አለን፡፡ አስተዳደጌ፣ አካባቢዬ፣ አገሪቷ፣ ቤተሰቦቼ…፣ ወዘተረፈ፣ ከዘረዘርነው ብዙ የምናሳብባቸው ሰበቦች አናጣም፡፡ ግን እኮ ችግር አንዱና ዋነኛው ከአዕምሯችን ጋር የሚያስተዋውቀን መሣሪያ ነው፡፡ በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር ብዙ ጊዜ የሚሠራው ለሆነ ችግር መፍትሔ ለመስጠት እንደሆነ ተምረናል፡፡ ችግር ከሌለ ምርምርም ጥናትም የለም፡፡ ችግር አዕምሯችን ውስጥ ያለውን ታላቁ ኃይላችንን እንድናውቅበትና እንድንጠቀምበት ዓይናችንን የሚገልጥልን አንዱ በረከት ነው፡፡ እንዲያውም ከእነ አባባሉ ‹‹ያልገደለን ምንም ዓይነት ችግር የእኛ ጥሩ ዕድል ነው›› ይባላል፡፡ ምክንያቱም በሕይወት እስካለህ ድረስ ያ ችግር በሰጠህ ትምህርት ከበፊቱ የተሻለ ሰው የምትሆንበት ዕድል እየሰጠህ ነው ማለት ነው፡፡ ‹‹ራሳችንን እንወቅ›› የሚለውንም ርዕስ የመረጥኩት ለዚህ ነው፡፡

እኛ የሰው ልጆች በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ዕፁብ ድንቅ የሆንን ፍጥረቶች ነን እንጂ ችግረኛ አይደለንም፡፡ ይሁን እንጂ ችግር ደጋግሞ ሊያስተምረንና ከእኛነታችን ከሰውነት ልዩ የአዕምሮ ፀጋችን ጋር ሊያስተዋውቀን በተደጋጋሚ በበሽታ፣ በብቸኝነትና በድህነት መልክ ቢመጣም፣ እኛ ግን እየለመድነውና መቸገር የእኛ የጥቁሮችና የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩ ስጦታ አድርገን ተቀብለነው እንደሚሞቅ ጋቢ ተከናንበነው በመኖር፣ ፈጣሪያችን የሰጠንን ልዩ የአዕምሮ ብቃት እንዲሁ በጭንቅላታችን እንደተሸከምነው ማለፍ እየመረጥን ነው፡፡ ነገር ግን ራሳችንንና አፈጣጠራችንን ብናውቀው ኖሮ ምርጫችን መከራ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

በመሆኑም ካነበብኩት ስለታላቁና ረቂቁ አዕምሯችን አወቃቀር በጥቂቱ ማካፈል ፈለግሁ፡፡ የተለያዩ የአዕምሮ ኒውሮ ሳይንቲስቶች እንዳጠኑት የሰው ልጅ ሁለት የአዕምሮ ክፍሎች አሉት፣ ንቁ አዕምሮና ድብቁ አዕምሮ ይባላሉ፡፡ አንዳንዶች ይህን ድብቁ አዕምሯችንን ስድስተኛው የስሜት ህዋስ በማለት ይገልጹታል፡፡ ንቁ አዕምሯችንን አምስቱ የስሜት ህዋሶቻችንን ማለትም በማየት፣ በመዳሰስ፣ በመቅመስ፣ በመስማትና በማሽተት ተጠቅመን የምናስብበት፣ የተለያዩ ትምህርቶችን የምንማርበት፣ በአጠቃላይ ሕይወታችንን ንቁ ሆነን የምኖርበት ስንተኛ የሚተኛ፣ ስንነሳ የሚነሳ የአዕምሮ አካል ነው፡፡ ድብቁ አዕምሯችን ግን 24 ሰዓታት የማይተኛ በጣም ረቂቅ የአዕምሯችን ክፍል ሲሆን፣ እኛ የሰው ልጆችን ከዓለም ጋር የሚያገናኘንም ይህኛው የአዕምሯችን ክፍል ነው፡፡

የሚገርመው የሰው ልጅ ተምሮ ፕሮፌሰር፣ ዶክተርና ኢንጂነር ሆኖ ማግኘት ያለበትን ዕውቀት ቀስሞ የዕውቀት ጥግ ደርሻለሁ ይላል፡፡ ብዙ መጻሕፎች በማንበብና በተለያዩ ሙያ ዘርፎች በመሠልጠን ጥሩ ባለሙያ በመሆን የተሰጠውን አዕምሮ በአግባቡ እየተጠቀመበት እንዳለ ያስባል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ስለአዕምሮ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የሰው ልጅ በንቁ አዕምሮው በአምስቱ የስሜት ህዋሳቱ በመታገዝ፣ ከአጠቃላይ የአዕምሮ ክፍሉ የሚጠቀመው አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ያ ማለት 95 በመቶ የአዕምሯችን አቅም ያለው በድብቁ የአዕምሯችን ክፍል ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት እንግዲህ በትምህርትና በንባብ በተለያየ የአዕምሮ ልህቀት ላይ ደርሰዋል የምንላቸው ሰዎች የንቁ አዕምሮአቸውን አምስት በመቶ ብቻ ተጠቅመው ነው፡፡ ሆኖም ግን 95 በመቶ የአዕምሯቸው ክፍል ግን አሁንም ምንም ሳይነካ እንዳለ ነው፡፡

በእርግጥ ሁሉም በትምህርት የላቁ ሰዎች የንቁ አዕምሯቸውን ብቻ ነው የተጠቀሙት ማለት ላንችል እንችላለን፡፡ ቁጥራቸው ብዙ አይሁን እንጂ እንደ እነ ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ፣ እንደ እነ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማና ሌሎችም በንቁ አዕምሯቸውና በድብቁ አዕምሯቸውም ተጠቅመው በዓለም ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ጳውሎስ ኞኞ ያሉ ደግሞ በንቁው አዕምሯቸው የቀለም ትምህርት ብዙም ሳይዘልቁ ከአራተኛ ክፍል አቁመው፣ በድብቁ አዕምሯቸውን ብቻ ተጠቅመው ዩኒቨርሲቲ ገብተው ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎችን ሲያስተምሩ የነበሩ ሰዎችም እንዳሉ የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ አስባችሁታል ትምህርት እንኳን ሳንቀስም በድብቁ አዕምሯችን ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር እንደምንችል? አልገባንም እንጂ እኛ ሰዎች በመሆናችን ብቻ ተዓምር የሆንን ፍጥረቶች ነን፡፡

የተማሩ የምንላቸው አብዛኞቹ የአዕምሯቸውን አምስት በመቶ አቅም ብቻ እየተጠቀሙ ከሆነ፣ የሌሎቻችን ደግሞ ከአምስት በመቶ እንኳን አንድ በመቶ የተጠቀምን ራሳችንን የቻልንና ቤተሰቦቻችንን እያስተዳደርን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ግን ራሱን ማስተዳደር ያልቻለው ከሰዎች እጅ እየጠበቀ የሚኖረውን የሰው ልጅ ቁጥር ማሰብ ነው፡፡ በጥናቱ እንደተቀመጠው በንቁ አዕምሯችንን እንኳን የቱንም ያህል ብንማር የአዕምሯችንን አምስት በመቶ ብቻ የምንጠቀም ከሆነ፣ ሙሉውን ቀርቶ የአዕምሯችንን 25 በመቶ የምንጠቀም ቢሆን፣ ዓለም ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖራት እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የጠቀስናቸው ጥቂት ሰዎች ባበረከቱት አስተዋጽኦ ለዓለም ምን ዓይነት በረከት እንዳመጡ ማየት ችለናል፡፡

ፈጣሪ እሱ አንድ ሆኖ አንድ ሙሉ ዓለምን ፈጥሮ እኛን ደግሞ ሲፈጥረን እሱን ተክተን እሱን ሆነን ምድር እንድናስተዳድር የምድሩን ጣጣ ለእኛ ተወልን፡፡ ያ ማለት ከአገራችን አንፃር ብቻ ብናየው 120 ሚሊዮን ሕዝብ ማለት፣ ሌላ 120 ሚሊዮን አገር መፍጠር የሚያስችል አቅም አለው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በአምሳሉ ስለተሠራን! ያ በእሱ አምሳል የሰጠን መቼም ከላይ የምንታየውን መልክና ቁመናችንን ነው እንዳንል በአምሳሉ የተባለው ፈጣሪያችን ፆታው ወንድ ስለሆነ በአምሳሉ የሚለው ሴቶችንም አይወክልም ነበር፡፡

ስለዚህ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአምሳሉ የፈጠረው አጠቃላይ የሰውነት ክፍላችንን የሚቆጣጠረው አዕምሯችንን ነው፡፡ ስለዚህም ነው የአዕምሯችንን አቅም አውቀን እኛ ከችግራችን በላይ መሆናችንን ተገንዝበን ወደ ውስጥ ማየት ያለብን፡፡

በአንድ ወቅት አንድ ሰው እንዲሁ በችግር ይፈተንና በዚህ ቢለው በዚያ ሕይወት አልቃና ትለዋለች፡፡ እናም ጠዋትና ማታ እየተነሳ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ፈጣሪን ያማርራል ‹‹ምነው ረሳኸኝ እኔን? እኔስ የአንተ ፍጥረት አይደለሁም ወይ?›› ይላል፡፡ እናም ከዕለታት አንድ ቀን እንዲሁ ተነስቶ ቤተ ክርስቲያን ሄደና እንደለመደው ‹‹አንኳኩ ይከፈትላቹኋል ብለህ የለ እንዴ? ምነው ለእኔ ይኼው ከደጅህ ቆሜ ስንት ዘመን ሳንኳኳ ለምን አትከፍትልኝም አለ፤›› ፈጣሪም በዛበትና፣ ‹‹አንተ ሰው አሁንስ ጨቀጨቅከኝ ከውስጥ ሆነህ የምን በር ነው ክፈት የምትለኝ፤›› ብሎ መልስ ሰጠው፡፡ እኛ ሰዎች የጥያቄዎቻችን መልስ ሁሉ በአንገታችን በተሸከምነው ጭንቅላታችን ውስጥ ተቀምጦ ወደ ላይ እያንጋጠጥን ስንት አዕምሮዎችን እንዳባከንን እየኖርን ያለነው ሕይወት ይመሰክራል፡፡

ኤካርት ቶሌ የሚባል ደራሲ ‹‹ዘ ፓወር ኦፍ ናው›› በሚለው መጽሐፉ በጻፈው አንድ ታሪክ አንድ ለማኝ ሁልጊዜ አንድ ሳጥን ላይ ተቀምጦ ይለምናል፡፡ እናም አንድ ሰውዬ በዚያ ሲያልፍ ያየውና ‹‹እሱ የተቀመጥክበት ሳጥን ውስጡ ምንድነው ያለው?›› ይለዋል፡፡ የእኔ ቢጤውም፣ ‹‹አይ ዝም ብሎ ነው፡፡ 30 ዓመት የተቀመጥኩበት አሮጌ ሳጥን ነው፣ ከፍቼም አይቼው አላውቅም፤›› ይለዋል፡፡ ሰውየውም እንደ ዋዛ፣ ‹‹ለምን ከፍተህ አታየውም፤›› ይለዋል፡፡ የእኔ ቢጤውም በሰውየው ሐሳብ ይስማማና ይከፍተዋል ከዚያም ባየው ነገር በድንጋጤ ፈዞ ይቀራል፣ ሳጥኑ ሙሉ በወርቅ ሳንቲም የታጨቀ ነበር፡፡

እናም እኛም ውስጥ ፈጣሪያችን ገና ወደ ምድር ሲፈጥረን እዚህች ምድር ላይ ተዓምር ለመፍጠር የሚያስችለንን ሙሉ ትጥቅ አስታጥቆን ስለሆነ፣ አሁን ቆም ብለን መጀመርያ እኔ ማነኝ? ምንድነኝ? ለምን ዓላማ ነው ወደ እዚች ምድር የመጣሁት? ብለን ወደ ውስጣችን እንቆፍር፣ ፈጣሪን መጠየቅም ካለብን መጠየቅ ያለብን መንገዱን እንዲመራን፣ የተሸፈነብንን እውነት እንዲገልጽልን፣ ራሳችንን እንዲያስተዋውቀንና ዓይነ ልቦናችንን እንዲያበራልን ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ትንሽ ጊዜ ቆም ብለን ወደ ውስጣችን ከቆፈርንና ማንነታችንን ካገኘን የራሳችንን አይደለም የዓለምን ጥያቄ እንፈታለን፡፡ ስለዚህ ዓለምን የምናይበትን መነጽር ቀይረን ዓለማችንን ከውስጣችን እንፈልግ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles