የዕውቀትን ብርሃን በውስጡ ማየት ትችል ዘንድ ሆድክን ባዶ አድርገው፤ ከርስህ እስከ እልቀትህ ቢሞላ ጥበብ ትርቅሃለች፡፡ ምንም እንኳን ምግብ ለሕይወት የደስታ ምንጭ ቢሆንም ከመጠን በላይ ከተበላ ስቃይ ያመጣል፡፡ ሳይርብህ መዓዛው የሚያውድ ጤናማ ምግብ ብትበላ አውኮ ያስተፋሃል፡፡ በራበህ ጊዜ ደረቅ ዳቦ በመጠኑ ብትበላ ግን ልክ መዓዛው የሚያውድ ጣፋጭ ምግብ ሆኖ ይሰማሃል፡፡ ሰው መጥኖ የመብላት ልማድ ካለው በክፉ ቀን ርሀብን ይቋቋማል፡፡ በቅንጦት ጊዜ ለመብል የኖረ በችግር ቀን ቀድሞ ይሞታል፡፡ ምግብ የሚበላው ሕይወትን ለማኖርና አምላክን ለማመስገን ነው፤ አንተ ግን ሰው ለመብላት ብቻ የሚኖር ይመስልሀል፡፡
ለመኖር ብላ እንጂ ለመብላት አትኑር (ማርክስ ሲዘሮ)፡፡ ዘወትር ሲበላ የኖረ የከርስ ምድጃ በችግር ቀን መከራ ያወርዳል፡፡ ከርስ የእጆች መጠፈሪያ ሽቦ፣ የእግር ማሠሪያ ሰንሰለት ነው፡፡ ለሆዱ ተገዥ የሆነ ሰው ለአምልኮ ጊዜ የለውም፡፡ እስከ እልቅትህ ከልክ በላይ፣ በተቃራኒውም ከመጠን ያነሰ አትብላ፤ አንድም በቁንጣን ያለበለዚያም በድካም ትሞታለህና፡፡
ሆድ አምላኩ ለሁለት ሌሊቶች እንቅልፍ አይወስደውም፡፡ እነዚህም አንደኛው ሌሊት በበላው ምግብ ተጨንቆ ሲንፈራገጥ የሚያድርበት፤ ሁለተኛው ሆዱን እንዴት እንደሚሞላ ሲያሰላስል የሚያነጋበት ሌሊት ናቸው፡፡ ሆዳሞች ወጥ ቤታቸው ፀሎት ቤታቸው፣ ምግብ አብሳያቸው ነፍስ አባታቸው፣ ገበታቸው መቅደሳቸው፣ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፡፡ (ቻርልስ ባክ)
- ባይለየኝ ጣሰው (ትርጉም) ‹‹የሰዓዲ ጥበቦች፡ ጎለስታንና ቡስታን›› (2004)
***