ራስን መደለል በእንስሳትም መካከል በጥቂቶች ላይ የተደረገ ሆኖ፤ በምሳሌ ዓይነት እንደ ተረት የሚነገር ቃል እናገኛለን፡፡ ተረቱም እንደሚከተለው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የተራበች ጦጣ ባንድ የወይን ስፍራ አጠገብ ስታልፍ ቁመቷ ከማይደርስበትና ዘልላም ልታወርደው ከማይቻላት አስቸጋሪ ከሆነ ካንድ ከፍተኛ ስፍራ ላይ በስሎ መልኩ ብቻ እንኳን የሚያስጐመጅ አንድ የወይን ዘለላ ተንዠርጐ ተመለከተች፡፡ ለማውረድም ሞክራ ሳይሆንላት ስለቀረ ልቧ እያወቀ፣ ራሷን በማታለል ወይኑ እኮ እንደሆን በእውነቱ ገና አልበሰለም፤ ለጊዜው የደረሰ መሰለ እንጂ ጥሬ ነው፡፡ ስለዚህ ላንድ ጥሬ ለሆነ ላልበሰለ ወይን ይህን ያህል ምን ያደክመኛል? የሱን ዓይነት ከሌላስ ስፍራ አጥቼ ነውን? በማለት ራሷን ደልላ ይኸንኑ ቃል በመደጋገም ራሷን እየነቀነቀች ነገሩን አኳስሳ ትታው ሄደች ይባላል፡፡
እንደዚሁም አንዲት ሰጐን አንድ አዳኝ ጠመንጃውን ደግኖ ሊተኩስባት ሲያነፃፅርባት እያየች፣ ሮጣ ሕይወቷን ለማዳን ከመሞከር ይልቅ፣ እዚያው ሁና ተደፍታ ዓይኖቹዋ እንዳያዩ ወደታች አቀርቅራ፣ የት አለና ነው አዳኝ? ቢኖር ለምን አላየውም? ይኸው ምንም ነገር አላይም እያለች በሐሳቧ ራሷን ደልላ ከዚያው አንገቷን ደፍታ ተቀመጠች ይባላል፡፡
የቀድሞ አባቶቻችን፣ ሰው ያልኾነውን ነው በማለት ራሱን የሚደልል ከንቱ መኾኑን ተመልክተው፣ ‹‹እርኩምን ሊበሉ ጅግራ ነው አሉ›› ብለው ይተርኩት የነበረ ቃልም ይገኛል፡፡
ስለዚህ ሰው ራሱን በራሱ እንደ ሕፃን ልጅ በመደለል በሐሳቡ የተመኘውን ነገር ሁሉ ሲፈጽም መታየቱ የቆየ እንጂ አዲስ አይደለም፡፡
- የማነ ገብረማርያም (ዶ/ር) ‹‹የፍልስፍና ትምህርት›› (1955)