Tuesday, October 3, 2023

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል አለ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የከፋ ቀውስ ውስጥ መሆኑንና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን ያስታወቀው ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የደረሰባቸውን ውሳኔዎች አስመልክቶ፣ ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም.  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ እስር፣ የሀብት ውድመት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር የዜጎች የደኅንነት ሥጋት፣ የእምነት ተቋማት ነፃነት ማጣት፣ የኑሮ ውድነት፣ አፈናና መሰወር የሚሉ በርካታ ችግሮች በአገሪቱ መንሰራፋታቸውን አመላክቷል:፡

በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተሄደበት ርቀት መልካም የሚባል ቢሆንም፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች ያለው የሰላም ዕጦት ግን አሳሳቢ መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ከሸገር ከተማ ጋር በተያያዘ በርካታ ቤቶች መፍረሳቸውንና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ለሰብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውን፣ በተመሳሳይ ከከተማው ግንባታ ጋር ተያይዞ በርካታ መስጅዶች መፍረሳቸውን፣ ድርጊቱን በመቃወም በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ድምፃቸውን ባሰሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የመንግሥት የፀጥታ አካላት በወሰዱት ዕርምጃ፣ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ መገደላቸውንና በርካቶች በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን እንዳረጋገጠ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች የገዥው ፓርቲ አመራሮች አባላት ከፍተኛ ጫና በማድረግ እስር፣ እንግልት፣ ግድያ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሮዎች እንዳይከፈቱ መደረጋቸውንም አስታውቋል፡፡

የዜጎች መሰወርና አፈና ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና በሰላም ወጥቶ መግባት አደጋ ውስጥ መግባቱን፣ በመንግሥት ተቋማት የታገዘ ዘረፋና ሕገወጥ እንቅስቃሴ መበራከቱን በመግለጫው አካቷል፡፡

ብልሹ አሠራር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ መባባሱን በመግለጫው የተመለከተ ሲሆን፣ ዜጎች በመደበኛ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ለእንግልት፣ ለብዝበዛና ለመጉላላት እየተዳረጉ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ ባለሀብቶችን በማስፈራራት ሕገወጥ ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ተቋማት መበራከታቸውንም አክሎ ገልጿል፡፡

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ‹‹ዜጎች ለዓመታት በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች እየተዳደሩ መቆየታቸው ኢሕገ መንግሥታዊ ነው›› ያለው ምክር ቤቱ፣ በአጠቃላይ አገሪቱ በዘርፈ ብዙ   የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ተረድተናል ብሏል፡፡

በመሆኑም  የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት እንዲከበር የመንግሥት አካላት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርጉትን ሕገወጥ ጫናን እንዲያቆሙና በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለው መስጅዶችን ማፍረስ  እንዲቆም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በዜጎች ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ሕገወጥ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በሙስናና በብልሹ አሠራር ሕዝቡን በኑሮ ውድነት እንዲሰቃይ የሚያደርጉ አካላትን በመለየት ተገቢውን የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስድ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ የአካባቢ፣ የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በፍጥነት እንዲካሄድና ሕዝብ በመረጣቸው ወኪሎች የመተዳደር መብቱ እንዲከበር ሲል ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -